“ልዩ ኃይል” የደህንነት ዋስትና ወይስ ፈተና

“ልዩ ኃይል” የደህንነት ዋስትና ወይስ ፈተና



ክልሎች ከአስር ሺዎች እስከ መቶ ሺዎች የሚቆጠር ልዩ ሃይል እንዳላቸው የተለያዩ መረጃዎች ያመላክታሉ። የተወሰኑ ምሁራንና የፀጥታ ባለሙያዎች ልዩ ሃይሎቹ”ለአገሪቱ የፀጥታ ችግርና ለአገር መበትን መንስዔ ሊሆኑ ይችላሉ” ሲሉ ይሞግታሉ። ሌሎች ባለሙያዎች ደግሞ የክልል ልዩ ሃይሎች “ለሕገ መንግሥቱና ለአገሪቱ ፀጥታ መጠበቅ ዋስትና ናቸው” ይላሉ።

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት የፌዴራሊዝምና ሕገ መንግሥት መምህሩ አቶ ደሳለኝ ጥጋቡ፤ የፌዴራሊዝምን ሥርዓት የተገበሩ አገራት የውስጥ ፀጥታቸውን ለማስጠበቅ በፌደራልና በክልሎች ባልተማከለና ወጥ በሆነ አስተዳደር እንደሚያዋቅሩ ይገልፃሉ።

ምሁሩ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 52 ንዑስ አንቀጽ 2 (ሰ) ክልሎች “የክልላቸውን ፖሊስ ያደራጃሉ ይመራሉ” የሚለውን አንቀጽ በመምዘዝም ኢትዮጵያ የውስጥ ፀጥታዋን ባልተማከለ አስተዳደር እንደምትመራ ያመላክታሉ። ሕገ መንግሥቱ ክልሎች የሚያዋቅሩትን የፀጥታ ሃይል ስያሜውን በትክክል ባይናገርም የፀጥታ ሃይል እንደሚያደራጁ መብት ሰጥቷቸዋል።

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ክልሎች እየጠነከሩ ነው። በዚህም የፌዴራል ሥርዓቱእየተፈታ ሲሆን፤ በተለይም ትላልቆቹ ክልሎች የፀጥታ መዋቅራቸውን ፉክክር በሚመስል መልክ እያጠናከሩ መጥተዋል። ክልሎች በሕገ መንግሥቱ የተሰጣቸው ሥልጣን የውስጥ ፀጥታቸውን ለማስጠበቅ ነው። ያለው አዝማሚያ ግን ለአገር ሥጋት በሚሆን ደረጃ ነው። ይህን የፌዴራል መንግሥት ልጓም ማበጀት አለበት። በሕገ መንግሥቱ በተሰጣቸው ሥልጣን ብቻ መሥራት እንዳለባቸው ምሁሩ ይገልፃሉ።

በአንዳንድ አገራት የክልል ፀጥታዎች የሚይዙት መሣሪያና የሰው ሃይላቸው ጭምር የተወሰነ ነው። በኢትዮጵያም የፌዴራል መንግሥት ይህን የመወሰን ሥልጣን አለው። ይህን ለማድረግ አዋጅ የማርቀቅ ሂደት ላይ ይገኛል። ይህን ተግባራዊ ማድረግ አለበት ሲሉም ይመክራሉ።

የቀድሞው ሠራዊት አባል ጀነራል ዋሲሁን ንጋቱ ‹‹የአገሪቱን የውስጥ ፀጥታ ለማስጠበቅ ወጥ የደህንነት መዋቅር መዘርጋት አለበት። የዕዙ ሰንሰለት፣ የሥልጣን ተዋረድ፣ የሰው ሃይልና የመሣሪያ መጠንን በየደረጃው መወሰን ያስፈልጋል። በየደረጃው ያሉ ሃላፊዎችም ተጠያቂነትና ሃላፊነት እንዲኖራቸው ሁሉንም በእኩል የሚያገለግል መዋቅር መዘርጋት ያስፈልጋል›› ይላሉ።

በኢትዮጵያ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ግን የፀጥታ ክፍሉ የሚመራው በክልሎች በተበጣጠስ የዕዝ ስንሰለት ነው። የሚተገብሩትም እንደየፍላጎታቸው ነው። በየደረጃው ያሉ ሃላፊዎች ሃላፊነት የማይወስዱና ተጠያቂ ካልሆኑ፣ ፍላጎታቸውን በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ እንዲሁም በመደራደርና በመነጋገር ከመፍታት ይልቅ እንደፈለጉ የሚያዝዟቸው ከሆነ ዜጎችን ከመጠበቅ ይልቅ የዜጎችን መብት ይነጥቃሉ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ክልሎች ለመዋጋት በሚመስል ሁኔታ እየተዘጋጁ ናቸው። በአንዳንድ ክልሎች የክልሉን መንግሥት ከማገልገል ወጥተው የግለሰቦችን ፍላጎት ጭምር ተግባራዊ ሲያደርጉ ይታያል።ይህ ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለ ሁሉም የሚጎዳ በመሆኑ መንግሥት መዋቅሩን ማስተካከል እንዳለበት ጀነራል ዋሲሁን ያስረዳሉ።

የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ሃይል ዋና አዛዥ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የደህንነት፣ ሕግና ፌደራሊዝም መምህር የነበሩትና በአሁኑ ወቅት የደህንነትና የፖለቲካ ተንታኙ ሜጀር ጀነራል አበበ ተክለሃይማኖት ‹‹በአገሪቱ እየታየ ያለው ችግር የፌዴራል ሥርዓቱና ሕገመንግሥቱ በትክክልተግባራዊ ባለመሆኑ እንጂ ክልሎች የፀጥታ መዋቅር ወይም ልዩ ሃይል ስላላቸው አይደለም።

የኢትዮጵያ የፌዴራል አወቃቀር ዘመናዊና የአገሪቱን ችግር የሚፈታ ነው። ክልሎች የእራሳቸው የፀጥታ ሃይል እንዲኖር መፍቀዱም እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው።የክልል ልዩ ሃይሎች የውስጥ ፀጥታን ለመፍታት ተብሎ የሚዘጋጁ ናቸው። የህዝቡን ባህልና አካባቢውን ስለሚያውቁት ችግሮችን መፍታት ይችላሉ። ክልሎች እራሳቸውን ያስተዳድሩ ከተባለ በውስጣቸው ያለውን ፀጥታ ማስከበር ያለባቸው ክልሎች መሆን ይኖርባቸዋል›› ይላሉ።

ሜጀር ጀነራሉ ፀጥታቸውን ማስጠበቃቸው እንዳለ ሆነ በዴሞክራሲዊነትናበሕግብቻ የሚመሩ የክልል መንግሥታት መኖር አለባቸው። የክልል የፀጥታ ሃይሎች ከተሰጣቸው ሃላፊነት ባለፈ ችግር ሲፈጥሩ የፌዴራል መንግሥት የማስቆም መብቱን ተጠቅሞ ጉዳት ሳይደርስ ማስቆም አለበት። ለምሳሌ በኦሮሚያና በሱማሌ ክልሎች መካከል የተፈጠረውን ችግር የፌዴራል መንግሥት ማስቆም ነበረበት። የወቅቱ መንግሥት ግን ልፍስፍስ ስለነበረ ማስቆም ባለመቻሉ ለዜጎች ሞትና መፈናቀል ምክንያት መሆኑን ያብራራሉ።

ሜጀር ጀነራል አበበ የክልል ልዩ ሃይሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚያደርሱ የጀነራል ዋሲሁንን ሀሳብተጋርተው፤ በክልል ብቻ ሳይሆን የፌዴራል የፀጥታ ሃይልም ጥሰት እንደሚያደርስ እና ዜጎችን እንደሚያጠቁ አክለው ገልፀው፤ ይህ የሚፈታው በክልልና በፌዴራል በመሆኑ ሳይሆን አሰራሩና ተጠያቂነቱን ማስተካከል እንደሚያስፈልግ፣ የክልሎችን ልዩ ሃይል ማፍረስ ሌላ ችግር ይዞ ከመምጣት ውጭ የአገሪቱን ችግር እንደማየፈታ፣ የፖለቲካ ብልሽቱንና አሰራሮችን በማስተካከል፣ ሌብነትን በማጽዳትና ተጠያቂነት በማጠናከር ማስተካከል እንደያስፈልግ ያሰምሩበታል።

ጀነራል ዋሲሁን በተለያየ ወቅት በልዩ ሃይሎች የተፈፀሙ የዜጎችን ህይወት መጥፋት፣ መብት በፍትሃዊነት የማስጠበቅ ችግርና መፈናቀልን በመጥቀስእልባት ካልተደረገለት በቀጣይ ለአገር መበተን ምክንያት ሊሆን እንደሚችል፤ የፖለቲካው ብልሽት እንዳለ ሆኖ መሰረታዊ ችግሩ የፀጥታውን መዋቅር አድርጎ መውሰድ ተገቢ እንዳልሆነ፣ እሳት የሚተፋ መሣሪያ የተጠቁ አካላትን በመዋቅር፣ በተጠያቂነትና በስልጠና የበቁ ካልሆነ ለአገሪቱም አደጋ ለዜጎችም ሰቆቃ መሆናቸው እንደማይቀር ይናገራሉ።

ጀነራል ዋሲሁን በኦሮሚያና በሱማሌ ክልሎች መካከል በተፈጠረው ግጭት በልዩ ሃይሎች የሞቱና የተፈናቀሉ ዜጎች፣ በጋምቤላ ክልል በልዩ ሃይል አባላት መካከል በተፈጠረው የርዕስ በርዕስ ግጭት ትጥቅ እስከመፍታት መደረሱ። ሰሞኑን በአማራ ክልል የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ መካሄዱ።

ከዚህ በተጨማሪ በክልሎች ወስጥ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መድረሱ። ክልሎች የልዩ ሃይል ቁጥር በመጨመር የፌዴራሉን መንግሥት የፀጥታ ሃይል ወደ ሚገዳደር ደረጃ እየሄዱ መሆናቸውን በማሳያነት በመጥቀስ መዋቅሩንና አሠራሩን ማስተካል እንደሚገባ ያስጠነቅቃሉ።

ሜጀር ጀነራል አበበ ‹‹ በአገሪቱ ቀደም ሲል በስፋት የማይታዩ የፀጥታ ክስተቶች ችግር ሆነው የመጡት ከአገሪቱ የፖለቲካ መበላሸት ጋር ተያይዞ ነው። ሁሉም የፀጥታ ችግሮች መነሻና መድረሻ የፖለቲካ ብልሽት፣ ሌብነትና የመልካም አስተዳደር ችግር ነው። ከዚህ ሲያልፍም የፌዴራል መንግሥት ሃላፊነቱን በተገቢው ሁኔታ አለመወጣቱ ነው። በጥቅሉ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ሕገ መንግሥቱና ሌሎች ሕጎችን ተግባራዊ ማድረግ አልቻሉም፡፡እነዚህን በማስተካክል ችግሩን መፍታት ይቻላል›› ሲሉ ይመክራሉ።

የትግራይ ክልል ፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬከተርና በጉዳዩ ዙሪያ ምርምራቸውን ያደረጉት ፍስሃ ሀፍተፅዮን (ፒ.ኤች.ዲ.) የኢትዮጵያ የአገር ውስጥ ፀጥታ ጉዳይ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት የጋራ ሥልጣን እንደሆነ ያመላክታሉ።

የተዘረጋው የፀጥታ ሥርዓት ጥቅምና ጉዳቱ ከአገሪቱ የፖለቲካ ነባራዊ ሁኔታ እንደማይለይ የሚያነሱት ዋናዳይሬክተሩ የፖለተካ ችግር በፀጥታው ላይ እንደሚታይና ችግሩ ሳይኖር ደግሞ ሥርዓቱ ፀጥታውን ለማስጠበቅ አወንታዊ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ይናገራሉ።

ፖለቲካዊ መግባባት ከተፈጠረ በኋላ የፌዴራልና የክልል የፀጥታ ሃይልን የጎንዮሽና የተዋዕረድ አሠራሮችንና የሕግ ጉድለቶችን በመፈተሸ ማስተካከል እንደሚገባ፣የፖለቲካ መተማመንና የመተጋገዝ መንፈስ ከተፈጠረ በኋላም የፖሊስ ሃይሎች የሚይዙትን መሣሪያ መወሰንም ተገቢመሆኑን፣ ከሁሉም በፊት ግን የፖለቲካውን ችግር መፍታት የፀጥታውን ጉድለት ለመፍታት ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ዋና ዳይሬክተሩ አመላክተዋል።

የፌዴራል ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ጀይላን አብዲ፤ በሕገ መንግሥቱ ክልሎች እራሳቸውን የማስተዳደር ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል። የፖሊስ ሃይል እንዲያቋቁሙ ሕገ መንግሥቱ ነው የፈቅደላቸው። ጥያቄም ቢነሳ በሕገ መንግሥቱ መሰረት ነው ያቋቋምነው ስለሚሉ በትብብር አብሮ ከመሥራት ውጭ ምንም ማድረግ አንችልም ይላሉ።

የፌዴራል ፖሊስ በሕግ ክልሎች የሚይዙትን መሣሪያ የመቆጣጠር ሥልጣን ባይሰጠውም የክልሎች ልዩ ሃይል ምን አይነት መሣሪያ ነው የሚታጠቀው የሚለው ግን አሳሳቢ ነው የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ በክልሎች በልዩ ሃይል ስም የተቋቋመው ፖሊስ ሳይሆን ከፖሊስ በላይ ነው። ‹‹ዙ››ና መትረየስ እንዲሁም ሌሎች ከባድ መሣሪያዎችን በመታጠቅ ከመከላከያ ጋር በዕኩል ደረጃ ላይመሆናቸውን አቶ ጀይላን ተናግረዋል።

ችግሩን ለማስተካከል ፖሊስ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚይዘውን ለመቆጠጣር የሚያስችል የመሣሪያ ደረጃ ለማውጣት የፌዴራል ፖሊስ መተዳደሪያ ረቂቅ አዋጅ በሰላም ሚኒስቴር እየታየ መሆኑና ከፀደቀ የፈዴራል ፖሊስ የሚያዘውን መሣሪያ በአገር አቀፍ ደረጃ መቆጣጠር እንደሚችል አመላክተዋል።

ይህ ካልሆነ ግን የክልሎች የፀጥታ ሥልጣን ለፌዴራል አስፈሪ መሆኑን፤ በተለያዩ ክልሎች በሚፈጠሩት ግጭቶች ዜጎች የሚሞቱትና ሰቆቃዎችም የሚደርሱት በክልል ልዩ ሃይሎች መሆኑን አቶ ጀይላን ገልፀዋል።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ከሚሽነር ጀነራል ክፍያለው ተፈራ፤ በክልላቸው አድማ በታኝና መደበኛ ፖሊስ መዋቅር ሲኖር ልዩ ሀይል የሚባል መዋቀር አለመኖሩን ያነሳሉ። የክልሉ የጸጥታ አካል በየትኛውም ክልል ላይ ተደራጅቶ የወሰደው የጸጥታ እርምጃ የለም ይላሉ።

በኦሮሚያና በሱማሌ ክልሎች መካከል በተፈጠረው ግጭትም ተወሰደ የተባለው እርምጃ በሱማሌ ክልል ልዩ ሀይል እንጂ በአሮሚያ በኩል የተወሰደ አርምጃ የለም። ነገሩ ሲድበሰበስ ነው በሁለቱ ክልሎች ልዩ ሀይል የሚባለው ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል መንግስት በአገራዊ አሰራር የሚመራነው ያሉት ኮሚሽነሩ እንደ አገር የሚሻሸሉ የጸጥታ አሰራሮች ክልሉን አሳታፊ በሆነ መልኩ በማከናወን ጥያቄ ካለን እንዲካተት ማድረግ እንጂ በሚወጣው አሰራር ለመገዛት ዝግጁ ነን። ኦሮሚያ የፌዴራል መንግስት አንዱ አካል እንጂ ብቻውን መንግስት አይደለም ይህን የመቀበል ግዴታም አለብን ብለዋል።

የአማራ፣ የትግራይ እና የደቡብ ክልሎችን የፀጥታና ደህንነት ቢሮዎችና የፖሊስ ኮሚሽነሮች በጉዳዩ ዙሪያ መረጃ እንዲሰጡን ያደረግነው ጥረት አንዱ ሃላፊ ለሌላው መረጃ እንዲሰጠን በማስተላለፍ መረጃውን ይሰጣሉ የተባሉት ሃላፊዎች ጋ ደጋግመን ብንደውልም ስልካቸውን ባለማንሳታቸው በጉዳዩ ዙሪያ ሃሳባቸውን መካተት አልቻልንም፡፡

ምንጭ፦አዲስ ዘመን

@tsegabwolde @tikvahethiopia

Report Page