ለቅዱስ ላሊበላ የተሰጡት ቃልኪዳኖች

ለቅዱስ ላሊበላ የተሰጡት ቃልኪዳኖች

https://t.me/Ethiopiabarbara

ያነጽካቸውን ቤተ መቅደሶች የተሳለመውን ኢየሩሳሌምን እንደተሳለመ አደርግለታለሁ፤ መታሰቢያህን ያደረገውን፣ ገድልህን የጻፈውን ያጻፈውን፣ በዚህ ቦታ ላይ መጥቶ አማልደኝ ያለውን፣ በአማላጅነትህ የተማጸነውን ሁሉ እስከ 15 ትውልድ ምሬልሃለሁ››

ቅዱስ ላሊበላ እንደ ዮሐንስና እንደ ኤርምያስም በእናቱ ማኅፀን ሳለ ነው መንፈስ ቅዱስ የሞላበት ስለሆነ ንቦች የከበቡት ቅዱስ ነው።

ንቦቹ ግን ሥጋዊ ንቦች ሳይሆኑ በንብ የተመሰሉ መላእክት ናቸው፡፡ ንጉሥ መሆኑን እያመለከቱ የሃይማኖትና የምግባር ማር ከእርሱ ይቀዳል ሲሉ በንብ ሠራዊት ተመስለው ሰውነቱን ላሱት፡፡

ጻዲቁ ንጉሥ ቅዱስ ላሊበላ ቅድስናን ከንግሥና፣ ክህነትን ከንጽሕና፣ ጥበብ መንፈሳዊን ከጥበብ ሥጋዊ ጋር አንድ አድርጎ አስተባብሮ የያዘ በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ፣ ቅዱሳን መላእክትም ይራዱት እንደነበርና ጌታችንም ትልቅ ቃልኪዳን እንደሰጠው ከቅዱስ ገድሉ ላይ እናገኛለን፡፡

ከጌታችን ዘንድ የተሰጠውንም ቃልኪዳን በሦስት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ በዚህም መሠረት፡-

1ኛ.

መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ቅዱስ ላሊበላን እየመራው ከላስታ ወደ አክሱም ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም አድርሶ በዚያ የሚገኙትን ቅዱሳት መካናት ሁሉንም ካሳየው በኋላ ‹‹ወደ ሀገርህ ሮሐ ተመልሰህ በእነዚህ ምሳሌ ታንጻለህ›› ብሎታል፡፡ ወደ ሀገሩም ተመልሶ በአሽተን ማርያም ተራራ ላይ ሱባኤ ይዞ በጾም ጸሎት ተወስኖ ሳለ እግዚአብሔር የሚሠራቸውን መቅደሶች በግልጽ በራእይ አሳይቶታል፡፡

2ኛ.

ከላይ እንዳየነው ለሞት ተብሎ የተሰጠው መርዝ ለሕይወት ሆኖለት በመሬት ላይ ወድቆ ሳለ በነፍስ መልአክ ነጥቆት እስከ ሰባተኛው ሰማይ ጽርሐ አርያም ድረስ ደርሶ በጌታ ፊት ቀርቦ ከጌታ ዘንድ ‹‹እኔ አከበርኩህ ቃሌ አይታበይም፣ ከአንድ ቋጥኝ እነዚያን በራእይ ያሳየሁህን አብያተ ክርስቲያናት ታንጻለህ›› የሚል ቃልኪዳን ተቀብሏል፡፡

3ኛ.

ከኢየሩሳሌምም ተመልሶ የንግሥናውን ዙፋን ከቅዱስ ገብረ ማርያም ከተረከበ በኋላ በተሰጠው መንፈሳዊ ሀብትና ባየው ራእይ መሠረት አብያተ ክርስቲያናቱን አንጾ ከጨረሰ በኋላ በቀኝና በግራው ዓሥር ዓሥር ኪሎ የሚመዝን የዓለት ድንጋይ ተሸክሞ ለ7 ዓመት ሲጾም ሲጸልይ ጌታችን ተገልጦለት

‹‹…ያነጽካቸውን ቤተ መቅደሶች የተሳለመውን ኢየሩሳሌምን እንደተሳለመ አድርግለታለሁ›› የሚለውን የመጨረሻውን ቃልኪዳን ሰጥቶታል፡፡ (ይህን ቃልኪዳኑን መጨረሻ ላይ በዝርዝር እናየዋለን)

4ኛ.

መድኃኔዓለም ክርስቶስ ለቅዱስ ላሊበላ ስለ ቤተመቅደሶቹ አሠራር በዝርዝር እንዳስረዳው፡- በተራ ቁጥር ሁለት ላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው በቅዱስ ገድሉ ላይ ከገጽ 117-127 ድረስ በጣም በስፋትና በዝርዝር እንደተጠቀሰው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ላሊበላን እስከ ሰባተኛው ሰማይ ድረስ በመላእክት ተነጥቆ በፊቱ እንዲቆም ካደረገው በኋላ ቤተ መቅደሶቹን እንዴት እንደሚያንጽ ቃል በቃል ነግሮታል፡፡

እግዚአብሔር ለኖህ መርከቡን እንዴት እንደሚሠራ ከነልኬቱ ጭምር በዝርዝር እንደነገረው ሁሉ ለቅዱስ ላሊበላም ዝርዝር ሁኔታዎችን ጭምር እንዲህ በማለት ትእዛዝ ሰጥቶታል፡-

‹‹መልአኩም ክብሩ ከሰማያት ሁሉ ክብር ወደሚበልጥ ወደ ሰባተኛው ሰማይ አደረሰው፣ ቅዱስ ላሊበላም ይህንን አይቶ በግንባሩ ተደፋ፣ ከኪሩቤል ዘንድ ይነሳ የሚል ቃል ተሰማና አንዱ ሱራፌል መጥቶ አነሣው፡፡ ልቡንም አጽንቶ አቆመው…

እግዚአብሔርም ተናገረው፡- ‹በምድር ላይ ቤተመቅደስ ትሠራልኝ ዘንድ የማሳይህን አስተውል፤ እዝነ ልቡናህንም ግለጥ፡፡ ከሰው ጋር ስለምኖር በሰማያት የምትኖር አባታችን እያሉ ከሚጠሩኝ በሃይማኖት ከተጎናፀፈኝ ስሜን ከሚያመሰግኑ ከመረጥኳቸው ከሕዝብ አንደበት በምመሰገንበት ገንዘብ እኔ ፈጥሬያቸዋለሁና፡፡

ከመጀመሪያይቱ ድንኳን ውስጥ በተሣለው ላይ ምስላቸው የተሠራ ከሚንቀሳቀሱ ከኪሩቤል አምሳል ለሙሴ እንደተናገርኩት አይደለም፡፡ ወዳጄ ሙሴ የመጀመሪያይቱን ድንኳን አርአያ በደብረ ሲና እንዳሳየሁት ድንኳንን እንደሠራ ሁሉ እንደሁ አንተም እንዳሳየሁህ ትሠራ ዘንድ ዕወቅ፣ አስተውል፣ ተጠንቀቅም፡፡ የማሳይህ ግን ለሙሴ እንዳሳየሁት አይደለም፤ መቅደሴን የምትሠራልኝም ሙሴ እንደሠራው አይደለም።

ሙሴስ ከተፈተለ ልብስና ከእንጨት ድንኳን ሠራ፤ አንተ ግን ለምሰሶውም ሆነ ለመቀኑ ለመድረኩ እንጨትን የምትፈልግ አይደለህም፤ ለጠፈራቸው መማገሪያ ገመድ የምትሻ አይደለህም፣ እንጨትንም ለማገር፣ ለምሰሶዋቸውም ገበታ፣ ለዙሪያቸውም ለማያያዣ ጭቃን የምትፈልግ አይደለህም፡፡ የቤተመቅደሶችን ፈቃድ ሁሉ ከአንድ ቋጥኝ ድንጋይ ትፈጽማለህና፡፡

የማሳይህ እኚህ የቤተ መቅደሶች አኗኗር ከምድር ልብ ውስጥ እስከዛሬ አለ፡፡ ከአሁን ጀምሮ በእጅህ እስኪገለጡም ድረስ በምድር ልብ ይኖራሉ፡፡ በሰው ልጅ ጥበብ ያይደለ በእኔ ሥልጣን ከምድር ልብ ውስጥ ታወጣቸው ዘንድ መረጥሁህ፡፡

ሕዝቦቼ ተወልጄ አድጌ ሞቼ ተቀብሬ ከሞትም የተነሳሁባትን ሀገር ለማየት ኢየሩሳሌም በመሄድ ግማሹም በበረሃ ይቀር ነበር። አሁን ግን አንተ ኢየሩሳሌምን በሀገርህ ትሠራለህ፡፡ በማንም እጅ ዳግመኛ ሊሠሩ የማይችሉ ቤተ መቅደሶቼን እንዳሳየሁህ ትሠራለህ፡፡

አንተም እንዳሳየሁህ በልብህ ውስጥ አኑራቸው፡፡ ስትሠራቸውም በየልካቸው ይሁን፤ ከእርዝመታቸውም በላይ ቢሆን፣ ከወርዳቸውም በላይ ቢሆን፣ በመወጣጫቸውም ላይ ቢሆን አንዳች እንዳትጨምር፡፡ ያሳየሁህ እሊህ ዐሥሩ መቅደሶች ከአንዲት ቋጥኝ ድንጋይ ሲወጡ አይተሃልና….› እያለ ጌታችን ሲነግረው ጻዲቁ ንጉሥ “ይህ እንዴት ይሆናል?” በማለት ይጠይቃል፡፡

ጌታም እውነት እልሃለሁ እነዚህ ያሳየሁህ መቅደሶች በሰው ኃይል የሚሠሩ ሆነው አይደለም፤ ጀማሪያቸው ሠሪያቸውና ፈጻሚያቸው እኔ ነኝ። ነገር ግን ኃይሌ በአንተ እጅ እንዲገለጽ ለምክንያት ተልከሃል፤ አንተ አነጽካቸው እየተባለ እስከ ዕለተ ምፅዓት ድረስ ስምህ ይጠራባቸዋል…›› እያለ ይቀጥላል የቅዱስ ላሊበላ ገድል፡፡

ዓሥሩን ቤተ መቅደሶች ሲሠራ እርሱ አንድ ክንድ ሠርቶ እንደሆነ ሌሊቱን አድሮ በቀጣዩ ቀን አሥር ክንድ ሆኖ ያገኘው ነበር፣ ቀንም በማይታወቁ ሰዎች አምሳል እየተገለጡ መላእክት ይራዱት ነበር፡፡

5.

መድኃኔዓለም ክርስቶስ ለቅዱስ ላሊበላ የገባለት ልዩ ቃልኪዳን፡-

5.1. ወደ ሰማይ ነጥቆ ወስዶት በዙፋኑ ፊት የሰጠው ቃልኪዳን፡-

‹‹ዛሬ በዚህች ቀን ከአንተ ጋር እነሆ ኪዳኔን አጸናሁ፡፡ በጸሎትህ ኃይል ታምኖ በውስጣቸው የሚያመሰግን ትሠራቸው ዘንድ ያላቸው አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የደረሰ ሁሉ አንተን አስቦ ‹አቤቱ ፈጽመህ ይቅር በለኝ› የሚለኝ፣ ‹ይህን የሚያስደንቅ ሥራ በእጁ ስለገለጥክለት ስለ ባሪያህ ስለ ቅዱስ ላሊበላ ብለህ ይቅር በለኝ› እያለ የሚጸልየውን በዚያ ጊዜ እኔ ጸሎቱን እሰማዋለሁ፡፡

ከሕፃንነቱ ጀምሮ የሠራውን ኃጢአት ሁሉ አስተሠርይለታለሁ፤ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ እንደ እንደተወለደባት ቀን የነፃ አደርገዋለሁ፡፡ የዕዳ ደብዳቤውንም በእጅህ ትቀደው ዘንድ ለአንተ እሠጥሃለሁ፤ ዕድሜውንም በምድር ላይ አረዝምለታለሁ፤ ቤቱንና ንብረቱን ሁሉ እባርክለታለሁ፤ በተንኮል የሚከራከረው ቢኖር ድል እንዳይነሣው አሠለጥነዋለሁ።

እግሮቹ እየተመላለሰ ወደ ቤተክርስቲያን የገሠገሠ ሁሉ በኢየሩሳሌም ሰማያዊት በኤዶም ገነት ውስጥ እንዲመላለስ አደርገዋለሁ፤ መባዕ የሚያገባ ሁሉ ጥቂትም ቢሆን ብዙም ቢሆን በእጅህ ከምሠራው ከቤተ መቅደሴ የሚያመጣውን መባዕ ሁሉ ቀኝ እጄን ዘርግቼ ከእጁ ፈጽሜ እቀበለዋለሁ፡፡

ከዕጣንም ወገን በየአይነቱ ያገባ ቢኖር እንደሰው ልማድ ሥጋዬን እንደቀባበት እንደ ኒቆዲሞስ ሽቱ እቀበለዋለሁ፣ በቢታንያ እንደቀባችኝ እንደ ማርያም እንተ ዕፍረት ሽቱ መዓዛውን አሸትለታለሁ፤ ስለ ማርያም እንተ ዕፍረት እስከ ዓለም ዳርቻ ሁሉ የመንግሥቴ ወንጌል በተሰበከበት ስሟን ይጠሩ ዘንድ እንዳዘዝኩ ሁሉ ትጉኀን በሚሆኑ በሰማያውያን መላእክት ከተሞች ስሙን ይጠሩት ዘንድ አዛለሁ፡፡

ለመብራት የሚሆን ዘይት ቢያገባ በይቅርታዬ ዘይትነት ራሱን አወዛዋለሁ፣ ሰውነቱ ለዘለዓለሙ አይሻክርም፣ ከፊቱም የብርሃን መብራት አይጠፋም፡፡ ወደ ሠርግ ቤት ከሚገቡ መብራታቸው ካልጠፋባቸው ከልባሞች ደናግል ጋር በመጣሁ ጊዜ በደስታ ይቀበለኛል፡፡››

5.2. በኢየሩሳሌም ሳለ ጌታችን የስቅለቱን መከራ በራእይ ካሳየው በኋላ የሰጠው ቃልኪዳን፡-

‹‹ለሌሎቹ ጻድቃን ከዚህ ዓለም በሞት በሚለዩበት ወቅት በፍጹም ልቡናቸው እንደሚገባ ያገለገሉኝን ዋጋቸውን ሰጠኋቸው።

ለአንተ ግን በሞት የምትለይበት ጊዜ ሳይደርስ በሕይወትህ ሳለህ ኪዳንን ሰጠሁህ፡፡

ማደሪያህ ከጳውሎስና ከጴጥሮስ ጋር ይሆናል፡፡ አቀማመጥህ በቀኜ ነው። ደቀ መዛሙርቴን በ12 ወንበር ተቀምጣችሁ በ12ቱ ነገደ እስራኤል ትፈርዳላችሁ እንዳልኳቸው አንተም ወንበርህ ከወንበራቸው አያንስም፤ ብርሃንህ ከብርሃናቸው፣ ክብርህ ከክብራቸው አያንስም፤ ኪዳንህም ከሰጠኋቸው ኪዳን አያንስም፤ ርስትህ ዕድል ፈንታህ ከእነርሱ ጋር ነው፡፡

የሰጠሁህን ቃልኪዳንና ገድልህን የሚያቃልል ሁሉ ዕድል ፈንታው ከአንተ ጋር አይሁን፣ ርስት ጉልቱም ከአንተ ርስት ጉልት አይገኝም፤ ያጸናሁልህን ቃልኪዳን የማያምን ያ ሰው እኔን ክርስቶስን እግዚአብሔር አይደለም እሩቅ ብእሲ ነው እንጂ እንደሚለኝ ሰው ይሁን፡፡

መጽሐፍህን ሰምቶ የተቀበለ ሁሉ የመንግሥቴን ወንጌል እንደተቀበለ ይሁን፤ አንተን ያከበረ እኔን እንዳከበረ ይሁን፡፡ ደቀ መዛሙርቴን 'እናንተን የሰማ እኔን የሰማ ነው፣ እናንተን የካደ እኔን የካደ ነው' እንዳልኳቸው አሁንም አንተን የሰማ ቃልኪዳንህንም ያመነ እኔን ጌታህን የሰማ ነው እልሃለሁ፡፡

መከራህንና ቃልኪዳንህን የካደ ሰው ቢኖር እኔ በምድር የተቀበልኩትን መከራ እንደ ካደ ሰው ነው፡፡ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በጸሎትህ ኃይል የታመኑ ሁሉ ማደሪያቸው ከአንተ ጋር ይሁን፤ ለቤተክርስቲያኖችህ አምኃ የሰጠ ቢኖር እንደ ደሜ ፍሳሽ እንደ ሥጋዬ ቁራሽ አድርጌ እቀበለዋለሁ፡፡››

5.3. ቤተ መቅደሶቹን ሠርቶ ከጨረሰ በኋላ ጌታችን የሰጠው ቃልኪዳን፡-

ቅዱስ ላሊበላ ጌታችን ባሳየውና ባዘዘው መሠረት አብያተ ክርስቲያናቱን አንጾ ከጨረሰ በኋላ በቀኝና በግራው ዓሥር ዓሥር ኪሎ የሚመዝን የዓለት ድንጋይ ተሸክሞ ለ7 ዓመት ሲጾም ሲጸልይ ከኖረ በኋላ ጌታችን ተገልጦለት በፊት የገባለትን ቃልኪዳን በዚህም ጊዜ በድጋሚ አረጋግጦለታል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ‹‹…ወደ ደጅህ የመጡት ሁሉ አስራት ይሁኑልህ፣ አንተ ከገባህበትም ይግቡ፣ አንተንም ከ12ቱ ሐዋርያት ጋር በፍርድ ቀን 13ኛ አደርግሃለሁ፡፡ ያነጽካቸውን ቤተ መቅደሶች የተሳለመውን ኢየሩሳሌምን እንደተሳለመ አደርግለታለሁ፤ መታሰቢያህን ያደረገውን፣ ገድልህን የጻፈውን ያጻፈውን፣ በዚህ ቦታ ላይ መጥቶ አማልደኝ ያለውን፣ በአማላጅነትህ የተማጸነውን ሁሉ እስከ 15 ትውልድ ምሬልሃለሁ›› ብሎ የመጨረሻውን ቃልኪዳን ሰጥቶታል፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን! እኛንም በአማላጅነታቸው የምንታመን ሁላችንን የመላእክት አለቃ የቅዱስ ሚካኤልን እና የቅዱስ ላሊበላን በረከታቸውን ያድለን በጸሎታቸው ይማረን አሜን!!!

(ምንጭ፡- ገድለ ቅዱስ ላሊበላ፡- የቅዱስ ላሊበላ ደብር በ2003 ዓ.ም ያሳተመው፣ ስንክሳር ዘወርሃ ሰኔ)

https://t.me/Ethiopiabarbara

Report Page