ሆሣዕናና መስቀሉ

ሆሣዕናና መስቀሉ

ዳረጎት ዘተዋሕዶ


ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ በመስቀል ላይ ከመዋሉ በፊት በዕለተ ሆሣዕና ሕዝቡ ሁሉ የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው በእልልታ “በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረከ ነው” እያሉ በክብር ዘምረውለት ነበር፡፡ ክርስቶስን የማእዘን ራሷ ያደረገችው ኩላዊት ቤተክርስቲያንም በተመሳሳይ የሆሣዕናው ክብርና የዕለተ ዓርቡ መከራ ሲፈራረቅባት መመልከት የተለመደ ቢሆንም  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ጉዳዩ አሳሳቢ ሆኗል፡፡

በሆሣዕና ዕለት ለጌታችን እንደቀረበው ምስጋና ክብር ዛሬም ቤተክርስቲያን በየመድረኩና ዝግጅቱ በአንደበታቸው ምስጋናን ያቀርቡላታል፡፡ ኦርቶዶከስ ሀገር ናት፣ የቅርሳችን፣ የታሪካችን መሠረት ናት እያሉ ያንቆለጳጵሷታል፡፡ ስለ ሰላም፣ ስለጤና፣ ስለልማት በሚደሰኮርባቸው መድረኮች ሁሉ የክብር እንግዳ ነች ነገር ግን ቤተክርስቲያን ዓርብ ላይ ስትሆን ግን ፍርድ ይገባታል የሚሉት እኚሁ በዕለተ ሆሣዕና ያመሰገኑ አንደበቶች ናቸው፡፡ 

በዕለተ ዓርብ ሁሉም ዝምታን ይመርጣል፡፡ ምዕመኖቿ ሲገደሉ፣ ካህናት ሲሰደዱ፣ ንዋያተ ቅድሳቶቿ ሲቃጠሉ እሷም ስትነድ ሀገር ነሽ የተባለችውን ያክል ሀገር ተቃጠለች፣ ሀገር መከራ ደረሰባት፣ ለማለት ቀርቶ የደረሰባትን ግፍ እንኳን በቅጡ ለመጥራት አንደበታቸው ይለጎማል::

ዛሬ በሚከበረው የደመራ ክብረ በዓልም በተለያዩ አከባቢዎች ቤተክርስቲያን በመንግሥት መዋቅርና በመንግሥት መዋቀር በሚደገፉ አካላት በዓሉን እንዳታከብር ፍቃድ በመንፈግ፣ ረጅም ጊዜ በዓሉን የምታከብርበትን ቦታ በመንጠቅና አገልግሎቷን እንዳትፈጽም መከራዋን እያበዙባት ይገኛሉ፡፡ መቼም የመስቀሉ ቀባሪዎች ሀሳባቸው ተሳክቶላቸው አያቅም ዛሬም የምናከብረው በዓል ይህንኑ የምንማርበት ነውና ጥላቻን በመስቀሉ እናሸንፈዋለን፡፡

በአሁን ሰዓት ከበዓል አከባበሩ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ጫና እየተደረገበት የሚገኘው የስልጤ፣ ሃዲያና አህጉረ ስብከት ሲሆን የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ "ጊዜያዊ ማረጋገጫ የተሰጠንን እጅግ አስቸጋሪና ቆሻሻ ቦታ ለፍተን አፅድተንና ደልድለን አስተካክለናል ይሁንና ሀይማኖታችን ላይ ጫና ለማሳደር የፈለጉ አመራሮች በግፍ እየነጠቁን ነው።" ሲሉ ያለውን ጫና ያስረዳሉ፡፡

በሌላ በኩል በደቡብ ክልል ጋሞ ዞን የመሎ ላኅ ኦርቶዶክሳውያን ለሁለት ዓመት ያለመታከት ከፌዴራል መንግሥት እስከ ቀበሌ ሊቃነ መናብት ድረስ ፍትሕ ይሰጣቸው ዘንድ መጮኽ ከጀመሩ ሰነባብተዋል። ፍትሕ የጠየቁም ምዕመናን ከአከባቢው እንዲሰደዱ የክስ ዶሴ እንዲከፈትባቸው ሆኗል።

በተመሳሳይ በምሥራቅ ሸዋ ዞን ሀገረ ስብከትም ተመሳሳይ የመንግሥት ባለሥልጣኖች የሚሰጡት ምላሽና የሃይማኖት አባቶችን የሚያስተናግዱበት መንገድ እጅግ አሳዛኝ ነው፡፡ የሀገረስብከቱን ሊቀ ጳጳስ እንዲህ የሚያጉላሉ ከሆነ በገጠር ያሉትንማ እንዴት ያደረጓቸው ይሆን?

መስቀሉ የሰላም ምልክታችን ነው፣ ዲያብሎስን ድል የነሳንበት ዓርማችን ነው፣ የመስቀል በዓልም የቀበሩት ያፈሩበት፣ ምንም ቢደብቁት ክብሩ እንደማይቀንስ ያየንበት ነውና ጠላቶቻችን ለመውጋት የምንይዘው አሁንም መስቀሉንና በመስቀሉ የተሰቀለውን ነውና ከቶ አናፍርም፡፡

Report Page