#WG

#WG


ትናንት በወንዶ ገነት ከተማ በተነሳ ተቃውሞ ላይ በፀጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት የሦስት ወጣቶች ሕይወት ማለፉን የአካባቢው ባለስልጣናት ለቢቢሲ ገለጡ።

የወንዶ ገነት ከተማ ከንቲባ አቶ ዓለሙ ጉበሌ ተቃውሞው የጀመረው ትናንት ከሰዓት መሆንን ጠቅሰው፤ በተቃውሞው ላይ የተሳተፉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሲመጣና ግርግሩ ያልተፈለገ አቅጣጫ ሊይዝ ሲል መከላከያ ሠራዊት ገብቷል ብለዋል።

የወንዶ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ሌዳሞ በበኩላቸው ለግጭቱ መነሻ የሆነው በሐዋሳና በሌሎች አካባቢዎች የተነሱ ተቃውሞዎች መሆናቸውን ገልፀዋል።

በከተማዋ የተቃጠለ ንብረትም ሆነ የወደመ ሀብት አለመኖሩን የተናገሩት አቶ ዳዊት፤ አስር ግለሰቦች በተቃውሞው ላይ በደረሰ ግጭት ተጎድተው በሆስፒታል ህክምና እያገኙ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የተጎዱት ወጣቶች ህክምና እያገኙ ያሉት በሐዋሳ ሪፈራል ሆስፒታልና አዳሬ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ከንቲባው ናቸው። በተጨማሪም ወንዶ ገነት በንግድ እንቅስቃሴዋ የምትታወቅ ከተማ መሆኗን ጠቅሰው፤ ከተማዋን በማረጋጋት ወደነበረበት ለመመለስ ከአገር ሽማግሌዎችና ከሐይማኖት አባቶች ጋር እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ትናንት ተቃውሞ ከነበረባቸው የሲዳማ ዞን ወረዳዎች መካከል አንዷ የሆነችው የሀገረ ሰላም ከተማ የገቢዎች ባለሥልጣን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ መኮንን፤ በከተማዋ በነበረው ተቃውሞ የሞቱና የቆሰሉ ሰዎች መኖራቸውን አረጋግጠው፤ ቁጥራቸውን ይፋ ለማድረግ መረጃው በእጃቸው እንደሌለ ገልጠዋል።

ትናንት ማታ 3 ሰዓት ላይ ወደ ከተማዋ የመከላከያ ሠራዊት መግባቱን ያረጋገጡት ኃላፊው፤ አሁን የተዘጉ ሱቆችን ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን የማስከፈት ሥራ እየሠሩ እንደሆነና የአከባቢውን ሰላም ወደ ነበረበት ለመመለስ ከአገር ሽማግሌዎች ጋር እየተወያዩ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ከሲዳማን የክልልነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ከሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ. ም ጀምሮ በሐዋሳ፣ አገረ ሰላም፣ አለታ ወንዶ፣ ይርጋለም፣ ለኩና ሌሎችም ከተሞች ግጭቶች ተቀስቅሰው እንደነበረ ይታወሳል።

በግጭቶቹ ሳቢያ የሞቱ ሰዎች መኖራቸው በተለያዩ ወገኖች ቢነገርም፤ እስካሁን ትክክለኛውን ቁጥር ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

Via #BBC

@tsegabwolde @tikvahethiopia

Report Page