telecom

telecom


ሁለት የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪዎችን ለማስገባት ዓለም አቀፍ ጨረታ ሊወጣ ነው



የቴሌኮሙዩኒኬሽንና ፖስታ አገልግሎት ዘርፍን እንዲቆጣጠር መንግሥት እንደ አዲስ ያቋቋመው የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለስልጣን የቴሌኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ በውድድር መርህ እንዲመራ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት፣ ሁለት ዓለም አቀፍ የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሰጪ ኩባንያዎች መርጦ ለማስገባት የሚያስችለውን ጨረታ ለማውጣት በዝግጅት ላይ እንደሆነ አስታወቀ፡፡


የኮሙዩኒኬሽን ባለስልጣን ስለተቋቋመበት ዓላማና እስካሁን ስላከናወናቸው ሥራዎች ማክሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. መግለጫ የሰጡት ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ባልቻ ሬባ (ኢንጂነር)፣ ሁለት የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ኩባንያዎች ወደ ገበያው እንዲገቡ መንግሥት ባሳለፈው የፖሊሲ ውሳኔ መሠረት ጨረታ ለማውጣት አስፈላጊውን ዝግጅት በማከናወን ላይ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡


ባለስልጣኑ ረቂቅ የፈቃድ አሰጣጥ ማዕቀፍ አዘጋጅቶ ባለድርሻ አካላት አስተያየት እንዲሰጡበት በድረ ገጹ ይፋ አድርጓል፡፡ ማንኛውም ፍላጎት ያለው አካል የሚሳተፍበት ሕዝባዊ የምክክር መድረክ ኅዳር 2 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደሚዘጋጅ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸው፣ የፈቃድ አሰጣጥ ማዕቀፉ ከባለድርሻ አካላት በሚሰነዘሩ አስተያየቶች ዳብሮ ሥራ ላይ እንደሚውል አስረድተዋል፡፡ ረቂቅ የፈቃድ አሰጣጥ ማዕቀፉ ለአራት ሳምንታት ለሕዝብ አስተያየት ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ አክለዋል፡፡


ዓለም አቀፍ ጨረታው ሌላ ችግር ካልተፈጠረ በቀር እስከ ታኅሳስ 30 ቀን እንደሚወጣ፣ ሁለቱ ፈቃድ ለቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ኩባንያዎች እስከ መጋቢት ወር መጨረሻ እንደሚሰጥ ባልቻ (ኢንጂነር) ተናግረዋል፡፡ ‹‹ከሚያዝያ 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ኢትዮ ቴሌኮምን ጨምሮ ሦስት የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ኩባንያዎች ይኖሩናል ማለት ነው፤›› ብለዋል፡፡


ለፈቃድ አሰጣጥ ሒደቱ አማካሪ ኩባንያ እንደሚቀጠር የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ሞገድ የሚሰጠው በግልጽ ውድድር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የጨረታ አሸናፊዎች የሚለዩት ከፍተኛ ገንዘብ በማቅረብ ብቻ ሳይሆን በቴሌኮም አገልግሎት ዘርፍ ልምድ፣ ብቃትና በቂ ካፒታል እንዳላቸው የተመሰከረላቸው እንደሚሆኑ አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ ውጪ ባለስልጣኑ ገለልተኛ ሆኖ ሥራውን ማከናወን ያለበት በመሆኑ ከማንኛውም ኩባንያ ጋር በተናጠል ውይይት እንደማያደርግ፣ እስካሁን ምንም ዓይነት የተደረገ ድርድር እንደሌለ አረጋግጠዋል፡፡


‹‹እስካሁን የጠየቀን ኩባንያ የለም፡፡ ሊጠይቁንም አይችሉም፤›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች፣ ማንኛውም ፍላጎት ያለው የኅብረተሰብ አካልና መንግሥት በሚዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ ጥያቄ በማቅረብ ማብራሪያ ማግኘት እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ኅዳር 2 ቀን በሚካሄደው የሕዝብ ምክክር መድረክ ላይ ለሁሉም ኩባንያዎች እኩል መረጃና ማብራሪያ እንሰጣለን፤›› ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ባለድርሻ አካላት በባለስልጣኑ ድረ ገጽ አስተያየት መስጠት እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡


የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለስልጣን ላለፉት 126 ዓመታት በብቸኝነት የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሲሰጥ ለቆየው ኢትዮ ቴሌኮም ፈቃድ እንደ አዲስ እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡ ‹‹ነባር ኩባንያ ቢሆንም የሚያሟላቸው የአገልግሎት ጥራት ደረጃዎች ይኖራሉ፡፡ የሚጠቀምባቸው ማመላከቻዎች፣ በየጊዜው ለተቆጣጣሪ ባለሥልጣኑ ማቅረብ ያለባቸው ሪፖርቶች፣ የተጠቃሚዎችን ቅሬታ የሚያስተናግዱበት አሠራር ይኖራል፡፡ እነዚህን በሙሉ አክብረው መሥራታቸውን የምናረጋግጥበት አባሪ ሰነድ ተያይዟል፤›› ብለዋል፡፡


በአዋጅ ቁጥር 1148/2011 ተቋቁሞ በመስከረም ወር ሥራ የጀመረው የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለስልጣን አዳዲስ ፈቃዶች መስጠት፣ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ኩባንያዎችን መቆጣጠር፣ የአገልግሎት ታሪፍ ቁጥጥር ማድረግ ዋና ዋና ሥራዎቹ ናቸው፡፡ የሬዲዮ ሞገድ፣ ዶሜን ኔም፣ አይፒ አይድሬስ ማስተዳደር የባለስልጣኑ ኃላፊነቶች ናቸው፡፡ባለስልጣኑ የቴክኒክ ደረጃዎች ያወጣል፣ ወደ አገር በሚገቡ የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት መሣሪያዎች ደረጃ ያወጣል፣ የብቃት ማረጋገጫ ይሰጣል፡፡


ባለስልጣኑ ሰባት አባላት ያሉት የሥራ አመራር ቦርድ ያለው ሲሆን፣ ሦስት አባላት ያሉት ቅሬታ ሰሚ ችሎት እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡ በቅሬታ ሰሚ ችሎት ውሳኔ ያልረካ ተቋም ጉዳዩን ወደ ፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት መውሰድ እንደሚችል ተነግሯል፡፡


via Reporter

@YeneTube @FikerAssefa

Report Page