#SUD

#SUD


በሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት እና በተቃዋሚዎች መካከል ሥልጣን ለመጋራት የተደረሰው ስምምነት የተራዘመ ቀውስ አገሪቱን ወደ የርስ በርስ ጦርነት ሊመራት ይችላል የሚል ሥጋት ያደረባቸው አሜሪካ እና የአረብ ሃገራት ባሳደሩት ጫና መሆኑን አራማጆች እና ባለሥልጣናት ተናገሩ።


ሁለቱ ወገኖች በሱዳን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓተ-መንግሥት ለማቆም ያስችላል ተብሎ ተስፋ ከተጣለበት ሥምምነት የደረሱት ተቃዋሚዎች በኻርቱም እና ሌሎች አካባቢዎች ሰልፍ ካካሔዱ በኋላ ነበር።


ድርድሮቹን በቅርብ የሚያውቁ ወገኖች እንደሚሉት ግን የሽግግር ምክር ቤቱን የሚመሩት ወታደራዊ መኮንኖች እና የተቃውሞ መሪዎች ከሥምምነት የደረሱት ከአንድ ቀን በፊት በተካሔደ ምሥጢራዊ ስብሰባ ላይ የአሜሪካ፣ የብሪታኒያ፣ የሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ዲፕሎማቶች ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ሕብረት ያቀረቡትን ምክረ-ሐሳብ እንዲቀበሉ ካሳደሩት በጫና በኋላ ነው።


ከመጋረጃ ጀርባ የተደረገውን ስብሰባ በቅርብ የሚያውቁ አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የለውጥ አራማጅ «እጅግ ውጥረት የተሞላበት ነገር ግን ወሳኝ ስብሰባ ነበር» ሲሉ ለአሶሲየትድ ፕሬስ ተናግረዋል። እኚሁ አራማጅ እንደሚሉት በዕለት ዓርብ ይፋ ለሆነው የሁለቱ ወገኖች ስምምነት ከመጋረጃ ጀርባ የተደረገው ስብሰባ የጀርባ አጥንት ሆኗል።


የሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት እና ተቃዋሚዎች ምርጫ እስኪዘጋጅ ሦስት ዓመታት ከሦስት ወር በሥልጣን የሚቆየውን ሉዓላዊ ምክር ቤት በጥምረት ለመምራት ከሥምምነት ደርሰዋል። ሉዓላዊውን ምክር ቤት ለመጀመሪያዎቹ 21 ወራት በወታደራዊ መኮንኖች ቀሪ 18 ወራት በሲቪል ሰዎች ይመራል። 


ሁለቱ ወገኖች ባለፈው ግንቦት በኻርቱም ከተማ ለተቃውሞ በወጡ ዜጎች ላይ የተወሰደው እርምጃ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ ከሥምምነት ደርሰዋል።

#DW

Report Page