#SRS

#SRS


የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ ህዝበ ውሳኔ ያለበትን ሂደት አስልክቶ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ መግለጫ፦

የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት በህዳር 12 ቀን 2011 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄን ህዝበ ውሳኔ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዲያስፈጽምለት መጠየቁ ይታወሳል፡፡ በዚህም መሰረት ቦርዱ አመራሮች ከተሟሉለት በኋላ ባደረገው ውይይት የተለያዩ ውሳኔዎችን ያሳለፈ ሲሆን በሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ቦርዱን ጨምሮ የክልሉ ምክር ቤት እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ማድረግ የሚገባቸውን ዝግጅቶች በዝርዝር አሳውቋል፡፡

በዚህም መሰረት ቦርዱ ለምክር ቤቱ በላከው ደብዳቤ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት እስከ ሐምሌ 19 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ፦

1. በአሁኑ ወቅት የክልሉም የዞኑም አስተዳደር ዋና ከተማ ሆና የምታገለግለው የሃዋሳ ከተማን አስመልክቶ የህዝበ ውሳኔው ውጤት የሲዳማን ክልላዊ መንግስት መቋቋም የሚያረጋግጥ ቢሆን ከተማዋን አስመልክቶ ሁለቱ አካላት የሚኖራቸውን መብቶችና ግንኙነቶች ከዚህም ጋር በተያያዘ የሚነሱ የሃብት ክፍፍል ጥያቄዎችን የሚያስተናግዱበትን አሰራር ዘርግቶ ለቦርዱ በጽሁፍ እንዲያሳውቅ

2. የህዝበ ውሳኔው ጸጥታና ደህንነት ማስጠበቅን አስመልክቶ የፌደራል የክልል እና የዞኑ ፓሊስ በትብብር የሚሰሩበትን ሁኔታ የሚያመቻች የስራ እቅድ አዘጋጅቶ ለቦርዱ እንዲያሳውቅ

3. የደቡብ ክልል ምክር ቤት በሲዳማ ዞን የሚኖሩ የተለያዩ የሌሎች ብሄር ብሔረሰብ አባላት ከህዝበ ውሳኔው በኋላ የሚኖራቸውን ህጋዊ የመብቶች ጥበቃን በተመለከተ ግልጽ አስተዳደራዊና ህጋዊ ማእቀፍ እንዲያዘጋጅና እንዲያሳቅ መጠየቁ ይታወሳል፡፡

የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች የክልል ምክር ቤት በበኩሉ ሐምሌ 19 ቀን 2011 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ምላሹን ለቦርዱ አቅርቧል፡፡ በምላሹም ክልሉ ካለበት ሁኔታና የስራ ጫና አንጻር የሲዳማ ዞን ክልላዊ መንግስት ሆኖ ቢቋቋም ከሃዋሳ ከተማ ጋር የተገናኙ ጉዳዮች የሚስተናገዱበት ህጋዊ ማእቀፍና እና በዞኑ የሚኖሩ ሌሎች የብሔር ብሔረሰብ አባላት ስለሚኖራቸው የመብት ጥበቃ ጊዜ ወስዶ መወያየት እንደሚገባው፣ ህግ ማውጣት ድረስ የሚደርስ ስራ መሆኑን ህግ ማውጣት ደግሞ፣ ማርቀቅ፣ ህዝብ አስተያየት መሰብሰብ እንዲሁም ማጽደቅን የሚጨምር ስራ በመሆኑ በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት ክልሉ በኮማንድ ፓስት ስር የሚተዳደር በመሆኑ የተጠቀሱት የአሰራርና የህግ ማእቀፎችን የሚፈልጉ ጉዳዮችን ለማቅረብ ተለዋጭ ጊዜ እንዲሰጠው ጥያቄ አቅርቧል፡፡

በዚህም መሰረት ቦርዱ የተለያዩ ውይይቶችን ካደረገ በኋላ ምክር ቤቱ ምላሹን እስከ ነሃሴ 15 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ እንዲያሳውቅ በሐምሌ 30 ቀን 2011 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ጠይቋል፡፡

የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት በነሃሴ 16 ቀን 2011 አ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ህዝበ ውሳኔው የሲዳማን ክልል መሆን ቢያረጋግጥ የሃዋሳ ከተማን አስመልክቶ ሁለቱ አካላት ስለሚኖራቸው ግንኙነትና የሃብት ክፍፍል ህግ ለማውጣትና ህጋዊ ማእቀፍ ለማዘጋጀት እንዲሁም በዞኑ የሚኖሩ ሌሎች ብሔረሰብ አባላትን ስለሚኖራቸው መብትና ጥበቃ ከህገ መንግስቱ በተጨማሪ አስተዳደራዊና ህጋዊ ማእቀፎችን ለማዘጋጀት ጊዜ ስለሚያስፈልግ አሁን ማቅረብ እንደማይችል ገልጾ ነገር ግን ከህዝበውሳኔው አስቀድሞ የህግ እና አስተዳደራዊ ማእቀፎቹን በማጽደቅ እንደሚያቀርብ አረጋግጧል፡፡ በመሆኑም ቦርዱ ባደረገው ውይይት የሚከተሉትን ዋና ዋና ውሳኔዎች አስተላልፎ ለሚመለከታቸው አካላት አሳውቋል፦

1. ቦርዱ ከነሃሴ 20 ቀን 2011 አ.ም እስከ ህዳር 10 ቀን 2012 ድረስ የሚቆይ የህዝበ ውሳኔውን የድርጊት መርሃ ግብር እና በጀት አዘጋጅቶ ለደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት እና ለሚመለከታቸው አካላት የላከ ሲሆን በእቅዱ መሰረት የህዝበ ውሳኔው ድምጽ መስጫ ቀን ህዳር 03/2012 አ.ም ይሆናል፡፡

2. ቦርዱም በድርጊት መርሃ ግብሩ መሰረት፣ የባለድርሻ አካላትን ማስተባበር እና የአፈጻጸም ውይይት የማድረግ ስራውን ከነሃሴ 30 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በተከታታይ ባሉት ሳምንታት የሚያከናውን ሲሆን ከዚህም ተጨማሪ የ 8,460 (ስምንት ሺህ አራት መቶ ስልሳ) ምርጫ አስፈጻሚዎችን መመልመል 1,692 ( አንድ ሺህ ስድስት መቶ ዘጠና ሁለት) የድምጽ መስጫ ጣቢያዎችን ማደራጀት፣ የህዝበ ውሳኔ መመሪያዎች የማውጣትና የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ህትመት የመሳሰሉትን ስራዎች ያከናውናል፡፡

3. ቦርዱ በተጨማሪም ከመስከረም 07 ቀን 2012 አ.ም ጀምሮ የህዝበ ውሳኔውን ጸጥታና ደህንነት ጥበቃ የእቅድ ዝግጅት ለማከናወን ከፌደራል፣ ከክልል እና ከዞን የጸጥታ አካላት ጋር የጋራ እቅድ የማውጣት ውይይቶችን ያደርጋል፡፡

4. የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት የሀዋሳን ከተማ የወደፊት ሁኔታ፤ የሀብት ክፍፍል እና የሌሎች ብሄረሰብ አባላትን የመብቶች ጥበቃ አስመልክቶ ህጋዊ እና አስተዳደራዊ ማእቀፎችን ማውጣት ስራ እስከ መስከረም 22 ድረስ ያጠናቀቃል፡፡

5. የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት ቦርዱ ባቀረበው ዝርዝር የበጀት እቅድ መሰረት ህዝበ ውሳኔን ለማፈጸም የሚያስፈልገውን 75,615,015.00 (ሰባ አምስት ሚልዮን ስድስት መቶ አስራ አምስት ሺህ አስራ አምስት) ብር በጀት እስከ መስከረም 12 ቀን 2012 አ.ም ድረስ ወደ ቦርዱ የባንክ አካውንት ያስተላልፋል፡፡

በመሆኑም ቦርዱ የቴክኒክ ጉዳዮች በቀሪው ጊዜ ሲያጠናቅቅ ባለድርሻ አካላትም በተሰናዳው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት በመወጣት ሕዝበ ውሳኔው በታቀደለት ጊዜ መሰረት እንዲከናወን የበኩላቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ ያስታውቃል፡፡

ነሃሴ 23 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

@tsegabwolde @tikvahethiopia

Report Page