#SRS

#SRS


የሲዳማ ህዝብ ላቀረበው የክልልነት ጥያቄ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፈጣን ምላሽ ሊሰጥ እንደሚገባ በብሄሩ ስም የሚንቀሳቀሱ ሶስት የፖለቲካ ፓርቲዎች አስታወቁ።

የሲዳማ አርነት ንቅናቄ/ሲአን/፣የሲዳማ ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ/ሲብዴፓ/ እና የሲዳማ ሀድቾ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት/ሲሀዴድ/ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ቦርዱ የህዝበ ውሳኔ ማድረጊያ ቀኑን ቆርጦ እንዲያሳውቅ ጠይቀዋል።

የሲአን ሊቀመንበር አቶ ዱካሌ ላምቢሶ እንዳስታወቁት በህገ-መንግስቱ አንቀጽ 47 በንዑስ አንቀጽ ሁለትና ሶስት ላይ የተቀመጡት መብቶች እንዲተገበሩ የፓርቲያቸው ፍላጎት ሲሆን የሲዳማ ህዝብም ክልል ሆኖ የመደራጀት መብቱን ሲጠይቅ ቆይቷል።

የሲዳማ ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ይስሀቅ ካያሞ በበኩላቸው “የክልል እንሁን ጥያቄውን በተደጋጋሚ ሲያቀርብ የነበረው የሲዳማ ህዝብ ለጥያቄው ምላሽ ለማግኘት መክፈል የማይገባውን መስዋዕትነት ከፍሏል”ብለዋል።

የህዝቦች የነጻነትና የመብት ጥያቄ የማያቋርጥ ሂደት በመሆኑም ጥያቄው ህገ-መንግስቱን መሰረት ባደረገ መልኩ ለሲዳማ ዞን ምክር ቤት ሀምሌ 10/2010 ዓ.ም ቀርቦ እንደነበር አስታውሰዋል።

የዞኑ ምክር ቤትም በሙሉ ድምጽ በማጽደቅ ለክልሉ ምክር ቤት እንዲተላለፍ መደረጉንና የክልሉ ምክር ቤትም ለምርጫ ቦርድ ህዝበ ውሳኔ እንዲያካሂድ ደብዳቤ መጻፉን ጠቁመዋል።

የሲዳማ ሀዲቾ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ሊቀመንበር አቶ ሰለሞን ቦወዳም በተመሳሳይ ምርጫ ቦርድ የውስጥ አደረጃጀቱ አለመሟላቱንና ቦርዱ ሲሰየም የመጀመሪያ ስራው የሲዳማ ብሄር የክልልነት ጥያቄ ህዝበ ውሳኔ እንደሚሆን ገልጾ እንደነበር አስታውሰዋል።

“ይሁን እንጂ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ህዝበ ውሳኔ በማድረግ የክልልነት ጥያቄው ምላሽ ማግኘት እንዲችል ማድረግ ሲገባው ይህን ሳያደርግ እስካሁን መቆየቱ አሳስቦናል” ብለዋል።

ጉዳዩ ያሳሰበው የሲደማ ብሄርም በሰላማዊ ሰልፍና በተለያዩ መንገዶች ጥያቄውን ማቅረቡን ገልጸው “እኛ በሲዳማ ውስጥ እየተንቀሳቀስን ያለን ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች የህዝባችን ህገመንግስታዊ ጥያቄ የሁላችንም መሆኑን እንገልጻለን” ብለዋል።

ፓርቲዎቹ በትላንቱ የጋራ መግለጫቸው እንዳመለከቱት ምርጫ ቦርድ በጉዳዩ ዙሪያ ከምሁራን ጋር በአዲስ አበባ በሚደረግ ውይይት እንዲሳተፉ የተጠሩ ቢሆንም ጥያቄያችው በህገመንግስቱ እንጂ በውይይት አይምለስም በሚል እራሳቸውን ማግለላቸውን አመልክተዋል።

ምርጫ ቦርድም የውስጥ አደረጃጀቱ የተሟላ በመሆኑ የህዝበ ውሳኔውን ጉዳይ ጊዜ የማይሰጥ ስራው አድርጎ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ ሳይጠናቀቅ በአምስት ቀናት ውስጥ የህዝበ ውሳኔውን ቀን ይፋ አንዲያደርግ ጠይቀዋል።

ምንጭ፦ ኢዜአ

@tsegabwolde @tikvahethiopia

Report Page