SK

SK

ዘ ልዑል Ⓜዲያቆን ዘልዑል ምናሉ

ስንክሳር ዘሰኔ ፳

✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ          አሜን

✍"ችግር ለራሳችን እንድንጸልይ ያነቃቃናል፤ ፍቅር ደግሞ ለሌሎች ሰዎች እንድንጸልይ ያስገድደናል"      

   📚ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ       

  ቀናችንን በጸሎት እንጀምር


አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ሰኔ 21- ለአዳም ዘር ሁሉ ድኅነት የተደረገባት አምላክን የወለደች ንግሥተ ሰማይ ወምድር ድንግል ማርያም ዓመታዊ በዓሏና በዓለም ሁሉ የቤተ ክርስቲያን መታነጽ መታሰቢያ ታላቅ በዓል ነው፡፡

❖ ዳግመኛም በዚሀች ዕለት እመቤታችን ለቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ ከተገለጠችለትና ሥዕሏን እንዲያሠራላት ከነገረችው በኋላ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን አደረገች፡፡

❖ አስቀድሞ ከከሃዲውና ከጨካኑ መኮንን ከአርያኖስ ጭፍሮች ውስጥ አንዱ የነበረው ታላቁ ሰማዕት ቅዱስ ጢሞቴዎስ ተጋድሎውን በድል ፈጸመ፡፡

❖ ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ በመሸታ ቤት ባረዷት ሴት ላይ ላደረገው ታላቅ ተአምር መታሰቢያ ሆነ፡፡

❖ ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ ያጠመቀውና በኋላም ዲቁናና ቅስና የሾመው አባ ከላድያኖስ ዕረፍቱ ነው፤ እርሱም አባ ሜልዮስ ባረፈ ጊዜ ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት 4ኛ የሆነ ነው፡፡   

✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

የእመቤታችን ዓመታዊ በዓልና በዓለም ሁሉ አብያተ ክርስቲያናት ስለመታነጻቸው  

 ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

❖ ይኽም በዓል ከእመቤታችን 33ቱ በዓላት አንዱ ነው፤ጨ‹‹ህንጸተ ቤተ ክርስቲያን›› ይባላል፤ የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን የታነጸችው በሰኔ 20 ቀን ነው፤ አናጺውም እራሱ ባለቤቱ መድኀኔዓለም ክርስቶስ ነው፤ ቦታው ፊልጰስዩስ ነው፤ ቤተክርስቲያኗ የተሰየመችው ደግሞ በእመቤታችን ስም ነው፡፡

❖ እመቤታችን ካረገች በ4ኛ ዓመት ጳውሎስና ባርናባስ በፊሊጲስዮስ ገብተው አስተምረው ሕዝቡን አሳምነው ካጠመቁ በኋላ ‹‹እንግዲህ ወደ ቤተ ጣዖት አትሂዱ›› አሏቸው፡፡

❖ አሕዛብ የነበሩትና አምነው የተጠመቁትም ‹‹የለመድነውን ከከለከላችሁን መካነ ጸሎት ስጡን›› አሏቸው፤ የከበሩ ሐዋርያትም ወደ ጴጥሮስና ዮሐንስም መልእክት ላኩባቸው፡፡

❖ ጴጥሮስና ዮሐንስም ‹‹ያለ ጌታችን ፈቃድ አንዳች ልታደርጉ አይገባምና ጸልዩ እኛም እንጸልያለን›› ብለው መለሱላቸው፤ ሁሉም ሱባኤ ይዘው በጸሎት ተጉ፡፡

❖ ጸሎትና ሱባኤያቸውን ከጨረሱ በኋላ ጌታችን በሞት ያረፉትን አስነሥቶ በሕይወት ያሉትንም ደቀመዛሙርቱን በደመና ጠቅሶ ፊልጵስዩስ ሰበሰባቸው፡፡

❖ ጌታችን በኪሩቤል ጀርባ ላይ ሆኖ እልፍ አእላፍ መልአክትን አስከትሎ ይወርዳል እመቤታችን በቀኙ ነበረች፤ ቅዱስ ዮሐንስም ‹‹ጌታዬ ለምን ሰበሰብከን›› ብሎ ጠየቀ፡፡

❖ ጌታችንም ‹‹በእናቴ ስም ከጽንፍ እስከ ጽንፍ አብያተ ክርስቲያናት እንዲታነጹ ፈቃዴ ነውና ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ላሳያችሁ ሥርዓት ላስተምራችሁ ነው›› አለው፤ ይህንን ብሎ ወደ ምሥራቅ ወሰዳቸው፡፡

✍‹‹የክርስቶስ አካሉና ሙላቱ ናት››

❖ ከዚህ በኃላ ሐዋርያት ከጌታችን እንዳዩት በዓለም ዞረው ቤተ ክርስቲያን አንጸዋል፤ ከዚያ በፊት የነበረው የእነ ሰሎሞን ቤተ መቅደስ፣ የአይሁድ ምኩራብ፣ የአይሁድ ሥርዓተ አምልኮ መፈጸሚያ እንጂ የአዲስ ኪዳን የቁርባንም ሆነ የጥምቀት ሥርዓት መፈጸሚያ አልነበረም፡፡

❖ ሰኔ 20 ቀን ህንጸተ ቤተክርስቲያን (የቤተ ክርስቲያን መታነጽ) ታላቅ በዓል ነው፤ ቤተክርስቲያን እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሻሽ የመጣችና ሩቅ ብእሲ የመሠረታት ሳትሆን እራሱ ጌታችን አምላካችን በገዛ ደሙ የመሠረታት ናት፡፡

❖ ዳግመኛም በዚህች ዕለት በቂሣርያው በቅዱስ ባስልዮስ ዘመን እንዲህ ሆነ ቅዱስ ባስልዮስ የእመቤታችንን ቤተ ክርስቲያን ከሠራ በኋላ በውስጧ የሚያኖረውን የእመቤታችንን ሥዕል ሊያሠራ መሳያ ሠሌዳ ፈለገ፡፡

❖ ሰዎችም በአንድ ባለጸጋ ቤት ጥሩ ሠሌዳ እንዳለ ነገሩትና ሄዶ ባለጸጋውን ሠሌዳውን እንዲሰጠው ለመነው፤ ባለጸጋውም ‹‹የልጆቼ ነው አልሰጥም›› አለው፡፡

❖ በትዕቢትም ሆኖ በታነጸቸው ቤተ ክርስቲያን ላይ የስድብን ነገር ተናገረ፡፡ ወዲያውም ወድቆ ክፉ አሟሟት ሞተና ልጆቹ ፈርተው ሠሌዳውን አምጥተው ለባስልዮስ ሰጡት፡፡

❖ እርሱም ያንን ሠሌዳ የእመቤታችንን ሥዕል አሳምሮ ይስልበት ዘንድ ለሰዓሊ ወስዶ ሰጠው፡፡ በዚህም ጊዜ እመቤታችን በራእይ ለቅዱስ ባስልዮስ ተገለጠችለትና ከአመፀኛ ሰው የተገኘ ነውና በዚያ ሰው ሠሌዳ ሥዕሏን እንዳያስል ከለከለችው፡፡

❖ የእመቤታችን ሥዕሏ የተሳለበትን ሠሌዳም የት እንደሚገኝ ነገረችውና ባስልዮስ ሄዶ በታላቅ ክብር አምጥቶ በቤተ ክርስቲያኑ አስቀመጠው፤ ከሥዕሏም ሥር ድውያንን ሁሉ የሚፈውስ የዘይት ቅባት መፍሰስ ጀመረ፡፡   

✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

ሰማዕቱ ቅዱስ ጢሞቴዎስ  

 ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

❖ ይህም ቅዱስ ጢሞቴዎስ ከምስር የተገኘ ታላቅ ሰማዕት ነው፤ እርሱም አስቀድሞ ከእንዴናው ገዥ ከአርያኖስ ጭፍራዎች ውስጥ አንዱ ነበር፡፡

❖ ሰው ሁሉ ጣዖትን እንዲያመልክ የሚያዝ የከሃዲው ንጉሥ የዲዮቅልጥያኖስ ትእዛዝ በግዛቱ ሁሉ በተነበበ ጊዜ ይህ ቅዱስ ጢሞቴዎስ ከሕዝቡ መካከል ተነሥቶ የንጉሡን የአዋጅ ደብዳቤ ቀደደው፡፡

❖ ደብዳቤውን ከቀደደው በኋላ በሕዝቡ ሁሉ ፊት ‹‹ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር አምላክ የለም›› ብሎ መሰከረ፡፡

❖ የንጉሡ የዲዮቅልጥያኖስ ባለሟል የሆነው መኰንን ይህንን የቅዱስ ጢሞቲዎስን ድፍረት በተመለከተ ጊዜ ይዞ ክፉኛ አስደበደበው፡፡

❖ ዳግመኛም ሰውነቱ ሁሉ እስኪደቅ ድረስ እንዲደበድቡት አዘዘ ነገር ግን ጌታችን መልአኩን ልኮ ፈውሰው፤ ከሥቃዩም ድኑ ፍጹም ጤነኛ ሆኖ አደረና በቀጣዩ ቀን ወደ መኰንኑ ቀርቦ አሁንም በድጋሚ ‹‹ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር አምላክ የለም አንተ ከሃዲ እፈር›› ብሎ መሰከረ፤ መኰንኑም ይዞ እጅግ አሠቃየው፡፡

❖ ሰውነቱንም በመጋዝ ቆራርጦና ሰነጣጥቆ ሰቀለው፤ በብረት ምጣድም አድርጎ ሥጋው እንደ ሰም እስኪቀልጥ ድረስ በእሳት አበሰለው፤ ከከተማ ውጪም አውጥቶ ጣለው፤ አሁንም ጌታችን ፍጹም ጤነኛ አድርጎ ፈወሰውና ወደ መኰንኑ ተመልሶ ሄዶ ‹‹ከሕያው እግዚአብሔር ልጅ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር አምላክ የለም አንተ ከሃዲ እፈር›› ብሎ ድጋሚ መሰከረ፡፡

❖ ይህንንም ድንቅ ተአምር አይተው በዙያው የነበሩ በጣም ብዙ አሕዛብ በጌታችን አምነው በሰማዕትነት ሞቱ፤ መኰንኑም ቅዱስ ጢሞቴዎስን ማሠቃየቱ በሰለቸው ጊዜ ሰኔ 21 ቀን አንገቱን በሰይፍ አስቆረጠውና የሰማዕትነት አክሊልን እንዲቀዳጅ አደረገው፡፡

ረድኤት በረከቱ ይደርብን፤ በጸሎቱ ይማረን

📌 ሰኔ 21 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1. እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም

2. ቅድስት ቤተ ክርስቲያን

3. ቅዱሳን ሐዋርያት

4. ቅዱስ ዼጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት

5. ቅዱሳን ዻውሎስና በርናባስ

6. ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ

7. ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ

8. ቅዱስ ጢሞቴዎስ ዘምስር (ሰማዕት)

📌 ወርኃዊ በዓላት

1. አበው ጎርጎርዮሳት

2. አባ ምዕመነ ድንግል

3. አባ ዓምደ ሥላሴ

4. አባ አሮን ሶርያዊ

5. አባ መርትያኖስ

6. አቡነ በጸሎተ ሚካኤል

✍ "ዘአቅረብኩ ማኅሌተ አዘኪርየ አእላፈ እምእለ ተጸምዱከ ዘልፈ ለእለ አነብብ ተወከፍ ዘንዴትየ መጽሐፈ እንተ ረሰይከ እግዚኦ ጸሪቀ መበለት ውኩፈ እም እለ አብኡ ብዑላን ዘተርፈ ነቢያት ቅዱሳን ወሐዋርያት ሰባክያን ሰማዕታት ወጻድቃን ወመላእክት ትጉሃን ዓዲ ወመነኮሳት ሔራን ባርኩ ባርኮ ጉባኤ ዛቲ መካን እስከ አረጋዊ ልሒቅ እምንዑስ ሕጻን ለዘጸሐፎ በክርታስ ወለዘ አጽሐፎ እንዘ ይደርስ ለዘአንበቦ ወለዘተርጐሞ በልሳን ሐዲስ ወለዘሰምዐ ቃሎ በዕዝነ መንፈስ በጸሎተ እሙ ማርያም አራቂተ ኩሉ እምባዕ ስኅቡረ ይምሐረነ ኢየሱስ ክርስቶስ ወይፈኑ ለነ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ እምይእዜ ወእስከ ለዓለም" ✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝ ✍"ልብህን በእርጋታ አኑረው፤ የሁሉም መጨረሻ እና የሁሉም አገልጋይ ለመሆን በጣም ትጋ ለከንቱ ንግግር ዘገምተኛና ሰነፍ ሁን፤ ነገር ግን የቅዱሳት መጻህፍትን ቃል በማወቅ በመስማት ድኅነትን የሚሰጡ ናቸውና ብልህ ሁን" 📚ታላቁ ባስልዮስ ዘቂሳሪያ             

ወስብሐት ለእግዚአብሔር         

                     ይቆየን

ቻናላችንን ይቀላቀሉን ለሌሎችም ሼር ያድርጉ

https://t.me/Finote_Abew1 https://t.me/Finote_Abew1

የተለያየ ጽሁፍ ያላቹ፣ መተረክ እንችላለን የምትሉ ቻናሉንና ግሩፑን በተለያየ አገልግሎት ማገዝ የምትፈልጉ በውስጥ መስመር አናግሩኝ።

 📩Coment- Telegram ላይ @Kibreleul @Mesikel_bot @Channal_Admin

አዘጋጅ ዲያቆን ዘልዑል ምናሉ 

Report Page