#SH

#SH


በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የጨበጡትን እውቀትና ክህሎት ለወገኖቻቸው እንዲያሸጋግሩ ተጠየቀ፦

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር፣ UCodeGirl እና አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በትብብር ከሐምሌ 24 እስከ ሐምሌ 28 /2011 ዓ.ም ያዘጋጁት የኮዲንግ ስልጠና የመክፈቻ ስነስርዓት ትናንት ሐምሌ 23 ቀን 2011 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ተካሂዷል፡፡

ከ23 የመንግስት ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ከ9ኛ-12ኛ ክፍል ተማሪ የሆኑ 100 ሴት ተማሪዎች የሚሳተፉበት ስልጠና የመክፈቻ ፕሮግራም ሲካሄድ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ እንዳሉት በውጭ አገራት ያሉ ዲያስፖራዎች በተሰማሩበት መስክ ያካበበቱትን እውቀትና ክህሎት ከተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ጋር በመነጋገር ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚኖሩ ወገኖች የማስተላለፍ ስራ ቢሰሩ መልካም ነው ብለዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም በታዳጊ ሴቶች ላይ ከልጅነታቸው ጀምሮ በመስራት በቴክኖሎጂ ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ ማሳደግ ይገባል ብለዋል፡፡ ፕሮፌሰር አፈወርቅ እንዳሉት በተለይ ሴቶች በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግና ሂሳብ (STEM) ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግና ውጤታማነታቸውን ለማጠናከር በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ስቲም ሴንተሮችን በመክፈት እየሰራን እንገኛለን ብለዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም ወጣቶች ወደ ትምህርት አለም ሲገቡ ከዓለም አገሮች አንፃር ሲታይ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ሁኔታ በማገናዘብ ለአገሬ አንድ ነገር አበረክታለሁ በሚል መነሻነት ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

UCodeGirl በአሜሪካን አገር በትውልደ ኢትዮጵያዊት የተቋቋመ ታዳጊ ሴቶችን በኮዲንግ የሚያሰለጥን ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ነው፡፡ የዚህ ድርጅት መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ ቤተልሔም ግሮነ በርግ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ያቀረበላትን ጥሪ ተከትሎ ወደ ትውልድ አገሯ በመምጣት Crack the Code: Sky High Coding with Drones for Girls በሚል ርዕስ ስልጠና ለመስጠት ዝግጅቷን ማጠናቀቋን ገልጻለች፡፡

በዝግጅቱ በአገራችን ጊዜና ገንዘብ ቆጣቢ በሆነ መልኩ የታክሲ አግልግሎት የሚሰጥ ራይድ የተባለ ድርጅት መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ ሳምራዊት ፍቅሩ እንዳለችው ችግር መውደቂያ ሳይሆን እድል ነው፡፡ ችግሮችን እንደ እድል በመቁጠር ልክ እንደኔ ለራስና ለአገር የሚጠቅም ህብረተሰቡ የሚገለገልበት ነገር መፍጠር ይቻላል ብላለች፡፡

በመድረኩ የተለያዩ አስተያየቶች የተንሸራሸሩ ሲሆን አብዛኞቹ አስተያየት ሰጪዎች ይህ መሰል ስልጠናዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው እና ስራ ፈጣሪዎችን የሚያበረታታ የፖሊሲ ማዕቀፍም እንዲኖር ጠይቀዋል፡፡ ከተማሪዎቹ መካከልም እንዲህ አይነት ድጋፎች መልካም መሆናቸውን ጠቅሰው በቀጣይም ለሌሎች እድሉን እንዲሰጥም ጠይቀዋል፡፡

በፕሮግራሙ የማጠቃለያ መልዕክት ያስተላለፉት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወ/ማርያም በበኩላቸው አሁን ወደ አራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት እየገባን ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ሳይንስና ዲጅታል ቴክኖሎጂን ግድ የሚል ነው፡፡

ስለዚህ ወጣቶቻችን ላይ ፈጠን ብለን በመስራት ለዚያ ልናዘጋጃቸው ይገባል እንደዚያ ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ ዜጎቹን ማፍራት እንችላለን ብለዋል፡፡ በዚህ ዘመን ቴክኖሎጂ ገዝቶ መጠቀም ብቻ ሳይሆን የቴክኖሎጂ አፍላቂ ለመሆንም ልንሰራ ይገባል ሲሉም አክለዋል፡፡

የሚጨበጥ ተስፋ እንዲኖረን ታዳጊዎች ላይ መስራትና ወጣቶችን ማሳተፍ አስፈላጊ ነው፡፡ የቴክኖሎጂ አቅማችንን ለማጎልበት ደግሞ አቅሙና ልምዱ ያላቸውን በተለያየ ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ብናሳትፍ እድገቱን ያፋጥነዋል ብለዋል ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም፡፡

ለዚህም እንዲረዳን በሌላ ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ምሁራን የሚሳተፉበት የምክክር ካውንስል አቋቁመን እየሰራን እንገኛለን ቤተልሔምም የዚህ ካውንስል አባል ነች ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ፖሊሲና የህግ ማዕቀፍ ቢዘጋጅ ለተባለውም ምላሽ ሲሰጡ የተጀማመሩ ነገሮች አሉ፡፡ ፍኖተ ካርታ እያዘጋጀን ነው፡፡ ፍኖተ ካርታው እነዚህን ጥያቄዎች ይመልሳል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ነገር ግን አይተን ክፍተትም ካለ አዲስ ነገር መፈጠር ያለበት ከሆነም ጥናት አድርገን ጥያቄዎችን ለመመለስ እንሰራለን ብለዋል፡፡

በመጨረሻም ቤተልሔም ግሮነ በርግ ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ያቀረበላትን ጥሪ ተቀብላ ወደ አገሯ በመምጣት ለታዳጊ ሴት ልጆች ያዘጋጀችውን ስልጠና አድንቀው ለሰልጣኝ ተማሪዎቹም በርትተው በዓላማና ለዓላማ እንዲማሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ስልጠናው ከሐምሌ 24 እስከ 28/2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቴክኖሎጂ ፋከልቲ የሚቀጥል መሆኑን ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

Via #EPA

@tsegabwolde @tikvahethiopia

Report Page