Read more

Read more

ተጨማሪ ለማንበብ

ማንኛውም ዕጩ ለመመዝገብ ያለደመወዝ ፍቃድ እንደማያስፈልገው ምርጫ ቦርድ አስታወቀ

በዕጬዎች ምዝገባ ሂደት ያጋጠሙ ችግሮችን መነሻ በማድረግ ነው ቦርዱ በአስቸኳይ ስብሰባ ውሳኔ ያሳለፈው

አል-ዐይን 2021/2/25 10:16 GMT







የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አዲስ ውሳኔ አሳለፈ

ቦርዱ በምርጫ ወቅት ለመንግስት ሰራተኛ ዕጩዎች የተቀመጠውን መመሪያ ቁ. 7/2013 አ. 16 (2) እንዲሰረዝ ወስኗል

በአዋጅ 1162/2011 እንዲሁም በዕጩ ተወዳዳሪዎች ምዝገባ ድጋፍ ፊርማ አሰባሰብና የመለያ ምልክት አመራረጥ መመሪያ ቁጥር 7/2013 አንቀጽ 16(1) መሰረት የመንግስት ሰራተኛ ዕጩዎች ስራቸውን መልቀቅ ሳያስፈልጋቸው በዕጩነት ለመወዳደር እንደሚችሉ ይደነግጋል። እንዲሁም እጩ ከሆኑ በኋላ በምርጫ ወቅት ያለደመወዝ ፈቃድ የማግኘት መብታቸውም በሕግ የተሰጠ ነው።

ቦርዱ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ፣ የዕጩዎች ምዝገባን በሚያከናውንበት ወቅት በዕጩ ተወዳዳሪዎች ምዝገባ ፣ የድጋፍ ፊርማ አሰባሰብና የመለያ ምልክት አመራረጥ “መመሪያ ቁጥር 7/2013 አንቀጽ 16(2) ትርጉም ተዛብቶ በመወሰዱ” የተለያዩ የምርጫ ክልሎች ፣ የመንግስት ሰራተኛ ዕጩዎችን ያለደመወዝ ፈቃድ የተወሰደበትን ሰነድ እንዲያቀርቡ መጠየቃቸውን ተረድቻለሁ ብሏል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ የተፈጠረውን መምታታት ለመፍታት የዕጩ ተወዳዳሪዎች ምዝገባ ድጋፍ ፊርማ አሰባሰብና የመለያ ምልክት አመራረጥ መመሪያ ቁጥር 7/2013 አንቀጽ 16 (2) እንዲሰረዝ ወስኗል፡፡ ይህንን ተከትሎ ማንኛውም ዕጩ ለመመዝገብ ያለደመወዝ ፍቃድ የማያስፈልገው መሆኑን አጽንኦት በመስጠት የዚህን የአሰራር ክፍተት ለመድፈን ለምርጫ ክልል ጽ/ቤት አስፈጻሚዎች ይኸው መልእክት እንደሚተላለፍ ቦርዱ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ6ተኛው ጠቅላላ ምርጫ የዕጩዎች ምዝገባን እያከናወነ እንደሆነ ይታወቃል። የዕጬዎች ምዝገባ ሂደቱን በመገምገም እንዲሁም ከፓለቲካ ፓርቲዎች የሚቀርቡ አቤቱታዎችን በማገናዘብ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት እየሰራ መሆኑንም ነው ቦርዱ የገለጸው፡፡


Report Page