Racism

Racism

ገራዶ ሚዲያ

በአንድ ጥቁር አሜሪካዊ ግድያ የተሳተፉ 4 ፖሊሶች ከስራ ተሰናበቱ!

በአሜሪካ ጥቁር አፍሮ አሜሪካውያን ኢፍትሀዊ በሆነ መንገድ በፖሊስ ሲገደሉ መስማት የተደጋገመ እና የተለመደ ክስተት ሆኗል፡፡ ይሄው የተለመደ የወንጀል ድርጊት ቀጥሎ ከትናንት በስቲያ ሰኞ እለት ጆርጅ ፍሎይድ የተባለ የ46 ዓመት ጥቁር አሜሪካዊ በሚኒያፖሊስ በ 4 ፖሊሶች ትብብር ህይወቱ አልፏል፡፡

ፖሊሶቹ፣ ጆርጅ ሰነድ አጭበርብሯል በሚል በሚኒያፖሊስ ከተማ አደባባይ ላይ ይዘውት ከመኪናው በማውረድ ሊያስሩ ትከእነርሱ መኪና በታች አስፓልት ላይ ያስተኙታል፡፡ ታዲያ በተኛበት ከፖሊሶቹ አንዱ ጉልበቱን በጆርጅ አንገት ላይ በማሳረፍ ያስጨንቀዋል፡፡ በአካባቢው ሆነው ክስተቱን በሚከታተሉ ግለሰቦች ተቀርጾ የተለቀቀው ቪዲዮ እንደሚያሳየው ጆርጅ ‘’መተንፈስ አልቻልኩም’’ እያለ ፖሊሶቹን በተደጋጋሚ ይማጸናል፡፡ ይሁን እንጂ አንገቱን ከአስፓልት አጣብቆ የተጫነው ፖሊስ ጉልበት ከአንገቱ አልተነሳም፡፡ የፖሊሶቹ ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ቀጠለ፡፡ ከ 4 ደቂቃዎች በኋላ ጆርጅ ራሱን ሳተ፡፡ ይሁን እንጂ ከዚህ በኋላም ቢሆን ፖሊሶቹ አልራሩለትም የሲቢኤስኤን ዘገባ እንደሚለው የጆርጅን አንገት ከአስፓልቱ ጋር አላትሞ እስትንፋስ የከለከለው የአንደኛው ፖሊስ ጉልበት በትንሹ ለ8 ደቂቃዎች ያህል አንገቱ ላይ ቆይቷል፡፡ ከዚህ በኋላ መንቀሳቀስ ተስኖት በቃሬዛ ወደ ህክምና ማዕከል ሲወሰድ ጆርጅ ህይወቱ አልፏል፡፡

በአካባቢው የነበሩ ግለሰቦች የጆርጅ አሟሟት እጅግ አሰቃቂ እንደነበር እና ፖሊሶቹን ቢለምኗቸውም ሊሰሟቸው እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡ ጆርጅን ለመታደግ ለእርዳታ ጥሪ ለፖሊስ ደውለው እንደነበርም እንዲሁ፡፡

ይህ የጆርጅ አሰቃቂ ሞት ብዙዎችን ያነጋገረ ፣ ያሳዘነ እና ያስቆጣ ክስተት ሆኗል፡፡

የሚኒያፖሊስ ከንቲባ ጃኮብ ፍሬይ እምባ እየተናነቃቸው ባደረጉት ንግግር “ቪዲዮውን ተመልክቻለሁ፤ ድርጊቱ በምንም መስፈርት ተቀባይነት የሌለው ነው” ብለዋል፡፡ “የፖሊስ ዲፓርትመንት ዓላማ ሰዎችን መግደል አይደለም” ያሉት ጃኮብ “ፖሊሶቻችን የሚሰለጥኑት ወንጀል ለመስራት አይደለም” በማለት ስሜታቸውን ገልጸዋል፡፡ “በአሜሪካ ጥቁር መሆን የሞት ቅጣት የሚያስከትል መሆን የለበትም” ሲሉም ከንቲባው ተናግረዋል፡፡

ምንም መሳሪያ ባልታጠቀው በጆርጅ ግድያ ተሳትፎ ያላቸው አራቱም ፖሊሶች ከስራቸው ተሰናብተው፣ ክስ ሊመሰረትባቸው በኤፍቢአይ ምርመራ እየተደረገባቸው ነው፡፡

ለቀጣዩ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የዲሞክራቶቹ እጩ ጆ ባይደን እና ሌሎች በርካታ ስመጥር ሰዎችም ድርጊቱን በመኮነን በፖሊሶቹ ላይ አስፈላጊው ምርመራ በፍጥነት ተደርጎ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ጠይቀዋል፡፡ “ጆርጅ ፍሎይድ እና ቤተሰቦቹ ፍትህ ያስፈልጋቸዋል” ያሉት ጆ ባይደን ፖሊሶቹ ከስራቸው እንዲሰናበቱ መደረጉንም አድንቀዋል፡፡

በተፈጸመው የግድያ ወንጀል ምክንያት በሚኒያፖሊስ ከተማ እና በአካባቢው ህብረተሰቡ አደባባይ በመውጣት እና መንገዶችን በመዝጋት ተቃውሞውን በማሰማት ላይ ነው፡፡

[አል ዓይን]

Report Page