Public

Public

From

ጎበዝ ዶር ደረጃ ገረፋ የሚባል የኦሮሞ ብሔርተኛ አክቲቪስት የኦሮሞ ትግል ተቀልብሷል እያለ የኦሮሞን ሕዝብ የማይመጥን በበታችነት ሰሜት የታጫቀ አጭር ፅሁፍ አነበብኩና “የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ የሆነ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባቸውን ሶሰት ነጥቦች አስቀምጥ” ብዬ ጠየቅሁት፡፡ እንዲህ ብሎ አራት የሚሆኑ መልሶችን ለጠፈልኝ፤ 1. “በነገርህ ላይ ለኔ ቋንቋው (ኦሮሚፋ ማለቱ ነው) ቀላሉ እና አብዛኛውን ነገር መፍታት የሚቻል ነበር፡፡ ዶር አብይ በመጣ በስድስት ወር ውስጥ እሄንን ቢያደርገ አሁን ብዙ ነገር አይወሳሰብበትም ነበር፡፡” አለኝ፤ ደረጄ ገረፋ (ዶር)፡፡ ይህን መልስ ስመለከት ኦሮሚፋ ምን እንዲሆን ነው ደረጄና ጓዶቹ የሚፈልጉት? የሚል ጥያቄ መጣብኝ፡፡ በኦሮሚፋ መናገር መብት ነው፡፡ በኦሮሚፋ አግልግሎ ማግኘት መብት ነው፡፡ መቼም ሌሎች በግድ እንዲናገሩት ማድረግ አይቻልም፡፡ ሰዎች ቋንቋ የሚጠቀሙት ጥቅም መኖሩን ሲያውቁ ነው፡፡ በተለይ ኤኮኖሚያዊ ጥቅም፡፡ ብዙ ኢትዮጵያዊያን ልጆቻቸውን ቻይንኛ ያስተምራሉ፡፡ ቻይንኛ ከኦሮሚፋ ሰለሚቀርባቸው አይደለም፡፡ ማንም ኢትዮጵያዊ ኦሮሚፋ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ አይሁን የሚል የለም፡፡ ይህን ለማድረግ የሚያስፈልግ የመስረተ ልማት እና ሌሎች ዝግጅቶች ማድረግ፤ የህግ ማእቀፍ ማዘጋጀት የግድ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ የኦሮሞ ልጆች የሚሞቱበት በቂ ምክንያት ምንድነው? እባካችሁ የኦሮሞ ብሔረተኛ አክቲቪስቶች ይህን በቅጡ አስረዱን፡፡ ኦሮሚፋ የሚስፋፋው ኦሮሞ ያልሆኑት ሲናገሩት ነው፡፡ ይህ ደግሞ በፍላጎት የሚሆን ነው፡፡ 2. “ለብዙ ሰው ባይመስልም በአብዛኛው `class orientation` መፈታት የሚችል ነው፡፡ ከሌሎች ህዝቦች ጋር ተመሳሰሳይነት አለው ለማለት ነው፡፡ ለምሣሌ እራስን በራስ ማስተዳደር፣ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት፣ መልካም አስተዳደርና የዲሞክራሲ ጥያቄ ወዘተ ማለት ይቻላል” በሚል ሁለተኛ መልስ አስቀምጧል፤ ደረጀ ገረፋ (ዶር)፡፡ ልብ በሉ፤ እነዚህ ጥያቄዎች የሁሉም ሕዝብ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ የእኔ ጥያቄ የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ የሚል ነበር፡፡ ሰለዚህ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የጋራ ጥያቄ ካላቸው በጋራ መታገል ለምን አይቻለም? ዴሞክራሲ፣ መልካም አስተዳደር፣ ያልተማከለ አስተዳደር (ፌዴራሊዝም)፣ የኢኮኖሚ እኩል ተጠቃሚነት፣ ወዘተ.. የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ጥያቄ ከሆነ፤ የኦሮሞ ወጣቶች እንዲሞቱ የኦሮሞ ጉዳይ የበለጠ ያገባናል የሚሉ ሰዎች ለምን ይፈልጋሉ? በኦሮሞ ልጆች ደም ምን ማግኘት ነው የሚፈልጉት? የኦሮሞ ወጣቶች ነቅተው መጠየቅ እና መልስ ማግኘት ይኖርባቸዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ 3. “…ምንአልባትም የኦሮሞ ብቻም ባይሆን በሀገር ምስረታ ውስጥ የተፈጠሩ ኢፍትሃዊነቶች፣ በትግል ሂደት ውስጥ የተፈጠሩ እንግልቶች እና ማካካሻዎች፤ ወዘተ… ብዙም ከባድ አይደሉም፡፡” የሚል ሶሰተኛ ምላሽ ደረጄ ገረፋ (ዶር) አስነብቦኛል፡፡ መልሱን ግን ደረጀ አንጠልጥሎ ትቶታል፡፡ አንደኛ የኦሮሞ ብቻም አይደሉም ብሏል፤ ሲቀጥል ብዙ ከባድ አይደሉም በማለት ለማቃለል ሙከራ ያደርጋል፡፡ ማን ነው ግን ማካካሻ የሚሆን ካሳ የሚከፍለው? ትግል ደግሞ የሚደረገው፤ ለነፃነት እንጂ ካሳ ለማግኘት ነው ወይ? ሕይወቱን ለነፃነት ሲል ለገበረ ዜጋ ምን ዓይነት ዋጋ ሊከፈለው ይችላል? በእርግጥ የኦሮሞ ህዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ዜጋ ካሳ ይፈልጋል ወይ? እንደዚህ ግልፅ ባልሆነ ጉዳይ የኦሮሞ ወጣቶች ሕይወት እንዲቀጠፍ ለምን አስፈለገ? ግን ለምን? ማን ነው በዚህ ጉዳይ ለማትረፍ የሚሰራው? የሚሊዮን ዶላር ጥያቄ ነው፡፡ 4. “ የሀገር ምልክትነት እና የወደፊቷ ኢትዮጵያም የጉዞ አቅጣጫ የኦሮሞ ጥያቄ ብቻም ባይሆኑም የኦሮሞ ህዝብ በእጅጉ የሚያሳሰቡት ናቸው፡፡”ይላል፤ ዶር ደረጀ ገረፋ፡፡ የሀገር ምልክትነት የሚለው ባይገባኝም- የወደፊ የኢትዮጵያ የጉዞ አቅጣጫ የሁሉም ኢትዮጵያዊን የጋራ ጉዳይ ሆኖ ሳለ ለኦሮመ ህዝብ የበለጠ ያሳሰበዋል መባሉም ግርታ ፈጥሮብኛል፡፡ ደግሜ ላስታውሳችሁ- የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ በሚል ነው ማብራሪያ የጠየቅሁት፡፡ መልሱ ግን እንዳያችሁት ነው፡፡ በኢትዮጵያ የወደፊት ጉዞ ላይ በጋራ ተመካክረን፣ ዴሞክራሲያዊ በሆነ ሥርዓት ውስጥ ማስተካከል በሚገባን ነገር፤ ለኦሮሞ ልጆች በተለየ እየተባለ ወጣቶች ለአመፅ የሚጠሩበት ምክንያት አልታይ ብሎኛል፡፡ ከላይ ያቀርብኳቸው ጥያቄዎች እዚህም ሊጠየቁ ይገባል፡፡

ሲጠቃለል፡፡ እንደ ዶር ደረጀ ገረፋ ቱሉ የተማሩ ንቁ የፖለቲካ አክቲቪስቶች፤ የኦሮሞ ጥያቄ በዚህ ደረጃ ከሆነ የሚገለፀው፤ የኦሮሞ ህዝብ ከቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተለየ ምንም ጥያቄ እንደሌለው የሚያሳይ ነው፡፡ ዕጣ ፋንታችንም አብሮ የተጋመደ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በተለየ ሁኔታ መስዋዕትነት የሚከፍልበት ምክንያት አይታየኝም፡፡ ይህ ጥያቄ ለሌሎች በድጋሚ ይቅረብ፤ የኦሮም ህዝብ ከኢትዮጵያ ህዝብ የተለየ ጥያቄ ካለ አስረዱን፤ ጥያቄው ከገባን አብረን እንቆማለን፡፡ ለሰለጠነ ውይይት እራሳችንን እናዘጋጀ …. ሰድብ ማስብ የማይችሉና የሰነፎች ሰለሆነ ከእነርሱ ጋር ላለመደመር ከስድብ ታቀቡ፡፡ ስድብ የኦሮሞን ሕዝብ አይመጥነውም!

Report Page