Passport

Passport


መታወቂያ እና የልደት ሰርተፊኬት ለሚያቀርቡ ፓስፖርት መስጠት ተጀመረ

ፓስፖርት ለመስጠት የድጋፍ ደብዳቤ መጠየቅን በማቆም በመታወቂያ እና ልደት ሰርተፊኬት ፓስፖርት መስጠት መጀመሩን የኢሜግሬሽን፣ ዜግነት እና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

ኤጀንሲው ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ፓስፖርት ለመውሰድ ጥያቄ የሚያቀርቡ አካላት ህጋዊ መታወቂያ እና የልደት ሰርተፊኬት ማቅረብ አለባቸው ብሏል፡፡

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በኢሜግሬሽን፣ ዜግነት እና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ተገኝቶ ባደረገው ምልከታ፤ አዲስ ፓስፖርት የሚጠይቁ እና የእድሳት አገልግሎቱን የሚፈልጉ ዜጎች በረጅም ሰልፍ ተራቸውን ሲጣባበቁ ተመልከቷል።

የዚህ ምክንያትም ከዚህ ቀደም ፓስፖርት ለማደስም ሆነ ለማውጣት ሲጠየቅ የነበረውን የድጋፍ ደብዳቤ በመቆሙ መሆኑን በኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነት እና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ ተሬሳ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

ሰሞኑን በመታወቂያ ብቻ በአስቸኳይ ለሚፈልጉ ከ3 እስከ 5 ቀናት ውሰጥ ፓስፖርት እየሰጠን ነው ብለዋል አቶ ደሳለኝ፡፡

ከቀጣዩ ሳምንት ጀምሮ ግን በመደበኛም ሆነ በአስቸኳይ ፓስፖርት ለማደስ እና አዲስ ለመጠየቅ ህጋዊ መታወቂያ እና የልደት ሰርተፊኬት መያዝ ግደ እንደሚል አንስወዋል።

የልደት ሰርተፊኬት መጠየቁ ማንኛውም ዜጋ የልደት ሰርተፊኬት እንዲኖረው እና ህገወጥ መታወቂያን ለመከላከል እንደሚያግዝ ነው ዳይሬክተሩ ያብራሩት።

በኤጀንሲው 9 የክልል ቅርንጫፎች፣ በአዲስ አበባ እና ሌሎች ከተሞች በቀላሉ የልደት ሰርተፊኬት ማግኘት እንደሚቻል ገልፀዋል።

ኤጀንሲው የመስሪያ ቤት የድጋፍ ደብዳቤ መጠየቁ በርካቶች በፈቀዱ ጊዜ እንደ መታወቂያ በቀላሉ ሊያገኙት የሚገባውን ፓስፖርት የማግኘት እድላቸውን ሲያጠብ ቆይቷል።

አሁን በመታወቂያ እና ልደት ሰርተፊኬት ብቻ ፓስፖርት ለመውሰድ ማመልከት ወይም ማደስ ይቻላል ከተባለ ወዲህ ሰሞኑን የታየው አይነት በጣም ረጅም ሰልፍ እንዳይከሰት ምን ዝግጅት ተደርጓል ለሚለው አቶ ደሳለኝ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በምላሻቸውም የሰው ሀይላችንን በሙሉ አቅማችን አሟጠን እየተጠቀምን ነው ያሉ ሲሆን በቀጣይ የኤጀንሲው አደረጃጀት ሲስተካከል የሰው ሀይል እጥረቱ ይቀረፋል ብለዋል፡፡

ከፓስፖርት ጋር ተያይዞ የሚነሳው ችግር ዋነኛ መንስኤው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ቢሆንም በ2011 ዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ ከ361 ሺህ በላይ ፓስፖርቶችን ለዜጎች መሰጠቱን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ ደሳለኝ ገልጸዋል።

በ2011 በጀት አመት 1 ሚሊየን ፓስፖርት ቢታዘዝም እስካሁን ወደ ሀገር ውስጥ የገባው 200 ሺህ ገደማ ነው።

እየገቡ የሚገኙ ፓስፖርቶች አሉ ያለው የኢሜግሬሽን፣ ዜግነት እና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ፤ ፓስፖርቱ ገብቶ ሲጠናቀቅ ችግሩ ይቃለላል ብሏል፡፡

-fana

@YeneTube @Fikerassefa

Report Page