Notes

Notes

Yo na

ግርግር ፣ ሃገር እና የአንድ ጎረምሳ ህልም



በቀደም ‘ለት በሬን ከፍቼ ቤቴ ስገባ አንዲት ገብስማ ግልገል እባብ ወለሉ ተጣጥፋ ላይ አገኘሁ። መጀመሪያ ሳያት ደነገጥኩ። ቀጥሎ ትንፋሼን ሰበሰብኩና መጥረጊያ አንስቼ አናቷ ላይ ነካኋት። አትንቀሳቀስም። ተደፋፍሬ በእግሬ ስነካት ግን እንደሞተች አወቅኩ። 


ተረጋጋሁ።


ጠርጌ ካወጣኋት በኋላ ሌላ ጥያቄ ደግሞ መጣ። 

‘እኔ ካልገደልኳት እንዴት ሞተች?’  

‘ሌላ እባብ ቤቴ ውስጥ ይኖር ይሆን?’

‘ማታ እንደተኛሁ ቢነድፈኝስ?’


ፍርሃቴ ሁለት ቀን ፈጀ። 


ከዚህ ሃሳብ ሳገግም፥ በውድም በግድም፥ የድርጊቱን ቅደም ተከተልና ውጤቱን ማጤን ጀመርኩ። እኔ አንድ ላጤ፣ የካርቦን መሰረት ካላቸው ማማልስ የምመደብ ከፍተኛና ውስብስብ ፍጡር ህይወቴ ውስጥ ድንገት በተከሰተች በመጠን አነስተኛ፥ ምናልባት ከእኔ ጋር ስትነፃፀር በሺህ እጥፍ የምታንስ፥ እና ከባቢ ሲሞቅ የምትሞቅ፣ ሲቀዘቅዝ የምትቀዘቅዝ ንዑስ ፍጡር ምክንያት የእለት ተእለት ኑሮዬ ሊስተጓጎል ችሏል። 


ሃገር ብሆን ምናልባትም ይሄው የግለሰብ የግርግር ታሪክ የሀገር ታሪክ ነው። “በጥባጭ ካለ ማን ጥሩ ይጠጣል” ይላል ያገር ሰው።



አንድ ወዳጃችን የነገረን ታሪክ ትዝ አለኝ። ሌላም አይነት ግርግር ደግሞ አለ። 


ሁለት ጓደኛማቾች ሩቅ መንገድ ይሄዳሉ። ሁለቱም ቁምጣ ሱሪ ያደረጉ ሲሆን የሚጓዙት ደግሞ አሸዋ ባለበት የበረሃ መንገድ ነው። 

ከፊትና ከኋላ ሆነው ሲራመዱ ከኋላ ያለው ከፊት ያለው ጓደኛውን ጊንጥ ሲነድፈው ያያል። የተነደፈው ጓደኛው ግን እግሩ በብርድ ይደንዝዝ ወይ በበሽታ አላወቅንም ሲነደፍ አልተሰማውም። ከኋላ የሚራመደው ሊነግረው ካለ በኋላ ይደነግጥ ይሆናል ብሎ አመንትቶ ሳይነግረው መንገዳቸውን ቀጠሉ። 


እንዲህ እያመነታ ብዙ መንገድ ከተጓዙ በኋላ ያሰቡበት ሲደርሱ ከኋላ ሲራመድ የነበረው ጓደኛውን ጠርቶ፥ ሳቅ እያለም ይሆናል አናውቅም፥ ቅድም እኮ አልተሰማህም እንጂ ባለሰባት ክርክር ጊንጥ ነድፎሃል አለው።

ዝቅ ብሎ እግሩን ቢያይ አብጧል። 

ራሱን ስቶ ወደቀ። 

አልተነሳም። 


የመንና ሶማሊያን እንደዚህ ሳይሆን አይቀርም ያስደነገጧቸው። ቀሩ ቀሩ።



እርግማን እንኳን ቢደርስ ሃገር የሚራገም ያለ አይመስለኝም። ግን ተረግመናል። 


እንዴት ሺህ አመት በየተራ እንገዳደላለን? 



ባለፈው ጠጥቶ የሚያሽከረክር ጎረምሳ ሊገለብጠን ሲታገል በአንዳች ተዓምር ተረፍንበት። 


ልጁ ሌላ ቀን ሲያገኘኝ እንደማፈር እያለ ገለፈጠ። 


ሁለት ስሜት ተሰማኝ። 


አንድ፡ ሐዘን።

ሁለት፡ ሐዘን።


Pic credit: © [?] on Twitter

Report Page