News

News



የቀድሞ የማሌዥያ ጠቅላይ ሚኒስትር ናጂብ ራዛቅ በተከሰሱበት የሙስና ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል።

ባለስልጣኑ በሚሊዮኖች ዶላር ጋር በተገናኘ ሰባት ክሶች ቀርበውባቸው የነበረ ሲሆን በሁሉም ጥፋተኛ ሆነው መገኘታቸው ተዘግቧል።

ስልጣናቸውን ያላግባቡ በመጠቀም፣ ገንዘብ በማዘዋወርና እምነትን ጥሰዋል በተባሉት ክሶች ላይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ፍፁም ውንጀላ ነው ብለው ተከራክረዋል።

ሙስናን እዋጋለሁ ብላ በተነሳችው ማሌዥያ ባለስልጣኗን መክሰሷ አገሪቷ ምን ያህል በህግ የበላይነት ታምናለች የሚለውን ማሳያ እንደሆነ በርካቶች ተናግረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሙስና ቅሌት እሳቸውን ብቻ ሳይሆን ከአለም አቀፉ ማጭበርበርና ሙስናንም ያጋለጠ ነው ተብሏል።

በዛሬው ዕለት በተደረሰው የፍረድ ቤት ውሳኔም 1 ማሌዥያ ዴቨሎፕመንት በርሃድ ከተባለው ተቋም አስር ሚሊዮን የሚገመት ዶላር በወቅቱ በስልጣን ላይ ወደነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር የባንክ አካውንት ውስጥ ገብቷል ተብሏል።

1 ማሌዥያ ዴቨሎፕመንት በርሃድ የተባለው ተቋም በጎርጎሳውያኑ 2009 የተቋቋመ ሲሆን አላማውም የአገሪቱን ልማት ለማሳደግ በሚልም ነው። በጎርጎሳውያኑ 2015ም ተቋሙ ለባንክና አንዳንድ ክፍያዎችን አለመፈፀሙ ጥያቄን አጫረ።

የማሌዥያና የአሜሪካ ባለስልጣናት 4.5 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ከተቋሙ ተወስዶ ግለሰቦች ኪስ ውስጥ ገብቷል ይላሉ።

ይህ ጠፋ የተባለው ገንዘብ ቅንጡ መኖሪያ ቤቶችን ከሚገነባ ድርጅት፣ የግል አውሮፕላን እንዲሁም ታዋቂዎች ስዕሎች ቫንጎግና ሞኔት እንዲሁም ከፍተኛ ገንዘብ የወጣበት የሆሊውድ ፊልም ተሰርቶበታል ተብሏል።

ባለፈው ሳምንት የአሜሪካው ባንክ ጎልድማን ሳክስ በዚህ የሙስና ቅሌት ውስጥ በነበረው ሚና ነፃ ለመውጣት 3.9 ቢሊዮን ዶላር ስምምነት ከማሌዥያ ባለስልጣናት ጋር ፈርሟል።

ባንኩ ኢንቨስተሮች በተቋሙ ላይ መዋዕለ ንዋይ እንዲያፈሱ በሚል 6.5 ቢሊዮን ዶላር ያህል ገንዘብ ማሰባሰብ ችሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስልጣን ላይ እያሉ ከነዚህ ጥፋቶች በሙሉ በባለስልጣናቱ ነፃ ቢደረጉም ከሁለት አመታት በፊት በነበረው ምርጫም እንዲሸነፉ ምክንያት ሆኗል። ባለስልጣናቱም ምርመራቸውን ከፍተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ለዘጠኝ አመታት ያህል፣ በጎርጎሳውያኑ 2009-2018 ድረስ ስልጣን ላይ ነበሩ።

ናጂብ ራዛቅ በበኩላቸው ምንም ጥፋት አላጠፋሁም ብለው የተከራከሩ ሲሆን የገንዘብ አማካሪዎቻቸው እንዳወናበዷቸው አስረድተዋል። በተለይም በግዞት ላይ ያለው ጆ ሎውን የጠቆሙ ሲሆን ግለሰቢ በአሜሪካና በማሌዥያ ክሶች ተመስርተውበታል።

ናጂብ ራዛቅ ጥፋተኛ ሆነው የተገኙባቸው ወንጀሎች እያንዳንዳቸው ከ15-20 አመታት እስር የሚያስፈርዱ ናቸው።

ከእስሩ ውሳኔ በፊትም ይግባኝ እንደሚጠይቁ አስታውቀዋል።

ባለቤታቸው ሮስማህ ማንሶር በበኩሏ ህጋዊ ካልሆነ የገንዘብ ዝውውር፣ ግብር ማጭበርበር ጋር በተያያዘ ክስ ተመስርቶባቸዋል።


Report Page