News

News

John

19 hrs ·

ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ

*********************************************

(ኢ.ፕ.ድ)

የአማራ ሕዝብ አንድነት ለሀገር ዋስትና ሆኖ በታሪክ ደምቆ የሚታወቅ እንጅ በየወቅቱ በሚከሰቱ ችግሮች የሚበተን አይደለም።

በክልሉ ውስጥ የተለየ ቡድንተኝነት እንዳለ ተደርጎ አመራሩንና ሕዝቡን ከፋፍሎ ለሌላ የችግር አዙሪት ለመዳረግ በጠላት ረጃጅም ክ

ንዶች ተለክተው የሚለቀቁ መሠረተ ቢስ ወሬዎችን በመስማት ቅንጣት ልንጠራጠርም ሆነ ልንደናገር አይገባንም።

የሰኔ 15ቱ አሰቃቂ ክስተት ከተፈጸመ ጀምሮ የክልሉ ሕዝብ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ በከፍተኛ ስክነት አካባቢውን በመጠበቅ ሁኔታው በአጭር ሰዓታት ውስጥ እንዲረጋጋ አስችሏል፡፡

የአማራ ሕዝብ ትናንትም ዛሬም በመከራም በደስታም ጊዜ አብሮ የሚዘምት አብሮ የሚኖር ሕዝብ ነው። አማራ በክልሉ ውስጥ ጎጥና ወንዝ ለይቶ ሊለያይ ይቅርና በየትኛውም ቦታ ከየትኛውም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ ጋር በፍቅርና በአንድነት ተጋብቶና ተዋልዶ በመኖር የሚታወቅ፣ በአንድነት ኃይልነቱ የሚታወቅ ታላቅ ሕዝብ ነው።

የአማራ ሕዝብ በየትኛውም የከፋ የፈተና ወቅት የራሱን የውስጥ ሕብረት ብቻ ሳይሆን የሀገርን አንድነት አስጠብቆና ሁሉንም ከዳር ዳር አስተባብሮ በጽናት የሚቆም፣ ሀገርን በመከራ ዘመን የሚያሻግር፣ የተበተነን የሚሰበስብ፣ የላላን ግንኙነት የሚያጠናክር የማዕዘን ድንጋር፣ የሀገር ምሶሶና ወጋግራ ነው፡፡

ይህን ሐቅ የማያውቁና ማንነቱን የማይረዱ ዘመን የወለዳቸው ደካማዎች ችግር በተፈጠረ ቁጥር የውስጥ አንድነቱን ለመፈተንና የውጭ ሰላሙን ለመንሳት በሬ ወለደ አጀንዳ እየፈጠሩ፣ ማሩን እያመረሩና ወተቱን እያጠቆሩ እንደሚፈታተኑትም እሙን ነው።

እነዚህ የአማራን ሕዝብ አንድነትና መልካም እሴት በውል የማይረዱ ኃይሎች ግን ትናንት አፍረውና ተሸማቀው እንደከሰሙት ሁሉ ዛሬም የውርደት ካባን ተከናንበው ይመለሳሉ እንጅ የአማራን የሺህ ዘመናት እሴት በተራ አሉቧልታ የሚፈትኑት አይሆንም፤ ፈጽሞም አይሳካላቸውም።

የአማራ ሕዝብ መሪዎቼ ሞቱ ብሎ የሚበተን ዝርው ሕዝብ አይደለም። መሪን አምጦ መውለድ ብቻ ሳይሆን ኮትኩቶ ማሳደግም ያውቅበታልና በዚሁ የዳበረ ልምዱ መሪ ቢሞት መሪን ተክቶ የሀገርን አንድነት አጽንቶ ይቀጥላል። ሕዝባችን ዘመነ መሳፍንትን የተሻገረ የተበተነን መሰብሰብ የተቀደደን መስፋት የሚችል ልባምና ባለ ራዕይ ሕዝብ ነው። በውስጡ ባሉ ደካሞች ስንፍናም ሆነ በዘመን ጠላቶቹ ሴራ አይበተንም።

የሩቅ ዘመን ታሪኩን ትተን የቅርብ ጊዜ ሕዝቡ የገጠመውን ፈተና ብናነሳ አማራ ለዘመናት በተሰራበት ሴራ ሲፈናቀልም ሆነ ሲገደል የአንዱ ሕመም ሌላውን እያስለቀሰው የሚቆዝምና አንገት ደፍቶ የሚያለቅስ ሕዝብ አለመሆኑን በተግባር አረጋግጧል።

ጎንደር ሲከፋ ጎጃም ፈጥኖ ይደርሳል፣ ወሎ ይዘምታል፣ ሸዋ ይቆጣል። ወሎ ሲፈተን ጎንደር ጎጃም ሸዋ ይነቃነቃል። በጎጃም ኮሽ ሲል ጎንደር ወሎ ሸዋ እንደ "አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ" ይነሳል።

እንኳን ጎጃም ለጎንደር፣ ሸዋ ለወሎ ይቅርና፣ በየትኛውም አካባቢ ያለው አማራ ለየትኛውም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ ለመከራው ፈጥኖ ደራሽ ለደስታው ደጋሽ ነው። ይህን የዘመናት እሴትና መሬት ላይ ያለ ነባራዊ ሐቅ መዘንጋት ለስህተት ይዳርጋል።

ይህ ሕዝብ አላዋቂዎች በሚፈጥሩት ስህተት የሚሳሳት፣ ደካሞች በሚደነቅሩት እንቅፋት የሚደናገር፣ ሴረኞች በሚያጠምዱት ወጥመድ የሚጠለፍ ድንጉጥ ሕዝብ አይደለም። ሁሉንም ባለ እኩይ አላማዎችን በየአግባባቸው ማረምና መቅጣት የሚያውቅበት ብልህና አዋቂ ሕዝብ ነው። ይህ ሕዝብ ምንም ዓይነት ፈተና ቢገጥመው መሻገርን ያውቅበታል።

የክልሉ መንግሥት ትልቁ ስንቁና የሁልጊዜም መተማመኛውም ይህ የሕዝቡ ታላቅነት ነው። አማራ በታናናሾች ሴራ የማያንስ በደካሞች ስንፍና የማይፈተን ሕዝብ መሆኑን አሳምሮ ስለሚያውቅና በውል ስለሚረዳም ይህን መሪዎቹን ያጣበትን ወቅት እንደሚሻገረውና ነገን በድል እንደሚኖር እምነቱ የጸና ነው።

የሁልጊዜም መተማመኛችን የሕዝባችን ታላቅነት ነው!

የአማራን የፈተና ወቅት ማንም የከረመ ሒሳቡን የሚያወራርድበት እንዲሆንም ፈጽሞ አንፈቅድም!

ሐምሌ 1 ቀን 2011 ዓ.ም.

ባህር ዳር

Report Page