የዓለማችን ቁጥር አንድ ሃቀኛዋ ሃገር ማን ትሆን?

የዓለማችን ቁጥር አንድ ሃቀኛዋ ሃገር ማን ትሆን?

t.me/etads


እንኳን ቦርሳና ዋሌት፣ የእጅ ስልክና የመገበያያ ካርድ፤ ሃሳብ እንኳ አንዴ ከአፍ ከወጣ በማይመለስበት ዘበን የአንዲት ሃገር ዜጎች የጠፋ ንብረት በመመለስ የሚደርስባቸው አልተገኘም።

የዚህች ሃገር ዋና ከተማ 14 ሚሊዮን ሰዎች አቅፋና ደግፋ ይዛለች። ሆኖም በፈረንጆቹ 2018 ከጠፉ 545 ሺህ መታወቂያዎች መካከል ሳይምለስ የቀረ የለም። ሁሉም ባለቤቶቻቸው ጋር በድጋሜ ተገናኝተዋል። እና መታወቂያ ምን ዋጋ አለው? ሊሉ ይችላሉ። 130 ሺህ ስልኮች የጣሉ ሰዎች ከእጅ ስልካቸው ጋር በሰላም ተገናኝተዋል። አሁንስ? ምን ይሄ ብቻ 240 ሺህ ዋሌት ቦርሳዎች የጣሉ ግለሰቦች ቤሳ ቢስቲን ሳይነካባቸው ተመልሶላቸዋል።

ምን ልባችንን አንጠለጠላችሁት ሃገሪቱን ንገሩን እንጂ እያሉ እንደሆነ እንገምታለን - ጃፓን ናት። ጃፓን ውስጥ የጠፋ ይገኛል፤ የተረሳ ይታወሳል። ሌላ ቦታ ዜና የሚሆነው የጠፋ ተመለሰ ነው። ፓጃን ግን ተቃራኒው ነው።

የስነ-ልቡና ባለሙያው ካዙኮ በርኸንስ 'እኔ ሳን ፍራንሲስኮ ስኖር አንድ ግለሰብ ዋሌት መለሰ ተብሎ ቴሌቪዥን ላይ ሳይ ነበር' ይላሉ። ባለሙያው እውነት ብለዋል። የጠፋ የመለሰ የዜና ሲሳይ መሆኑ አይቀርም። ጃፓን ውስጥ ዜና መሆን ከፈለጉ የጠፋ አይመልሱ የሚል ምክር መስጠት አንሻም።

ካዙኮ፤ እምብርታቸውን የቀበሩት፤ ጥርሳቸውን የነቀሉት ጃፓን ነው። ሃቀኝነት ምን ያክል ቦታ እንዳለው አይዘነጉም። ጃፓኖች የጠፋ የሚመልሱት ወረታ ፈልገው አይደለም። እንደውም የጠፋ ዕቃ ሲያገኙ ለፖሊስ አስረክበው እነሱ ወደ ሥራ ያመራሉ።

ፖሊስ ያገኛቸውን ንብረቶች ባለቤቱን አፈላልጎ ያስረክባል። ባለቤቱ ካልተገኘ ይጠብቃል። ተጠብቆ ካልመጣ ዕቃ ከጥቅም ውጭ እንዲሆን ይደረጋል።

አጭር የምስል መግለጫ
ኮባን በመባል የሚታወቁት የቶኪዮ አነስተኛ ፖሊስ ጣብያዎች

ቶኪዮ ውስጥ በየመቶ ስኩዌር ኪሎሜትር ርቀት 97 አነስተኛ ፖሊስ ጣብያዎች አሉ። ጣብያዎቹ ኮባን ይባላሉ። ይህ ማለት ጠፋብኝ ወይም አገኘሁ ብሎ ለማመልከት እጅግ ቀላል ነው። ሎንዶን ብትገቡ የምታገኙት 11 ብቻ ነው።

የቶክዮ ፖሊስ መኮንኖች በትህትናቸው ይታወቃሉ። አዛውንትን መንገድ በማሻገርም የሚደርስባቸው የለም። ዜጎችም ወድቆ ያገኙትን ንብረት ለፖሊስ እንዲያስረክቡ ይበረታታሉ። ይህ ገና ከልጅነት የሚማሩት ሥነ-ምግባር ነው።

አንዳንድ ንብረቶች ለፖሊስ ከተሰጡ በኋላ የንብረቱ ባለቤት ካልተገኘ ላመጣው ሰው በሽልማት መልክ ይበረከታል። የፖሊስ መኮንኑ ማሳሂሮ ታማሩ 'አንድ ታዳጊ አንዲት ሳንቲም ቢያገኝ ወደ ፖሊስ ይዞ ይመጣል፤ ፈላጊ ካለ [ምንም እንኳ አንዲት ሳንቲም ፈልጎ የሚመጣ ባይኖርም] ይመለሳል፤ ካልሆነ ግን ላመጣው ሰው በሽልማት መልክ ይሰጣል።'

ይህን ፅንሰ-ሐሳብ ለማረጋገጥ የተሰማሩ አጥኚዎች እንደ ጠፉ አስመስለው ቶኪዮ መንገድ ላይ ከጣሏቸው ስልኮች መካከል 88 በመቶው ተመልሰዋል። መሃል ኒው ዮርክ ከተጣሉት መካከል ግን 6 በመቶ ብቻ ናቸው ሊገኙ የቻሉት። ቶኪዮ ውስጥ ከሚጠፉ ዋሌቶች 80 በመቶ ይገኛሉ፤ ኒው ዮርክ ውስጥ ደግሞ 10 በመቶ ብቻ።

ቶኪዮ ውስጥ ቢጠፋም የማይፈለገው አንድ ንብረት ዣንጥላ ይመስላል። 338 ሺህ ዣንጥላዎች የጠፉባት ከተማ 1 በመቶ ብቻ ናቸው ጥላዬን ብለው የመጡት። ቶኪዮ ውስጥ የፕላስቲክ ዣንጥላዎች ርካሽ ከመሆናቸው የተነሳ በነፃ የሚቀመጡበት ሥፍራም አለ።

ምንም እንኳ ጃፓን የጠፋ የሚመለስባት ይሁን እንጂ የግልፅነት ችግር እንዳለ የሥነ-ልቡና ባለሙያው ያወሳሉ። ይህ ደግሞ የባሕል ተፅዕኖ ነው። ሰዎች ባሕል አክባሪና ፈሪ ናቸው ይላሉ። ነገር ግን ነገሮች እየተቀየሩ እንደሆነ ባለሙያው ያሰምራሉ።

ካዙኮ የጃፓናውያንን ሃቀኝነት ከቡድሃ እምነት ጋር ያይዙታል። ሃገሪቱ በሱናሚ በተናጠች ጊዜ እንኳን ያላቸው ለሌሎች ሲያካፍሉ ታይተዋል። ጃፓናውያን ለባሕላቸው ያላቸው አክብሮትም ለዚህ አስተዋፅዖ እንዳለው ይታመናል። ከግላዊ አስተሳሰብ ይልቅ አብሮነት ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል።

BBC Amharic

Report Page