#NA

#NA


እፅ በማዘዋወር ተጠርጥራ ቻይና ጉዋንዡ እስር ቤት የምትገኘው ኢትዮጵያዊቷ ናዝራዊት አበራ ከወር በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት መቅረቧንና የመጨረሻውን ፍርድ እየተጠባበቁ እንደሆነ እህቷ ቤተልሔም አበራ ለቢቢሲ ገለፁ።

ናዝራዊት አበራ በቻይና በእፅ ዝውውር ተጠርጥራ በቁጥጥር ሥር መዋሏ ከተሰማ ስድስት ወራቶች አልፈዋል።

አንድ ሰው እፅ ሲያዘዋውር ከተገኘ የሞት ፍርድ እንዲበየንበት የሚያዘው የቻይና ህግ በናዝራዊት ላይ ተግባራዊ ይሆናል በሚል በቤተሰቦቿ፣ በቅርብ ዘመዶቿ እንዲሁም በበርካታ ሰዎች ዘንድ ጋትን አሳድሯል።

ጉዳዩንም ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እንዲሁም ታዋቂ ግለሰቦች በቅርበት እየተከታተሉት እንደሆነም መገለፁ ይታወሳል።

በቻይና ጉዋንዡ እስር ቤት የምትገኘው ናዝራዊት ባለፈው ወር ሰኔ 20 ቀን 2011 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርባለች። 5.2 ኪሎግራም የሚመዝነውን በሻምፖ መልክ የተያዘጋጀ ኮኬይን የተሰኘ እፅ ማን እንደሰጣትና እንዴት ልትያዝ እንደቻለች ለአገሪቱ ፍርድ ቤት አስረድታለች።

የቻይና መንግሥት ያቆመላት ጠበቃም ናዝራዊት ከአገር ወጥታ እንደማታውቅ የሚያሳይ የጉዞ ታሪክ ማስረጃ፣ ከወንጀል ነፃ መሆኗን፣ የትምህርቷንና የሥራዋን ሁኔታ -ኢንጂነር እንደሆነች የሚያመለክት ማስረጃ መቅረቡን እህቷ ቤተልሔም አበራ ገልፀዋል።

እህቷ ማስረጃዎቹን የቀረበባትን ክስ ለመከላከል የላኩት መሆኑን በመጥቀስ "የቻይና ሕግ ከባድ ሳይሆን አይቀርም፤ እንዳሰብነው እየሄደ አይደለም ግን ተስፋ አንቆርጥም" ብለዋል።

በሌላ በኩል አቃቤ ሕግ ሆነ ብላ ድርጊቱን እንደፈፀመችና የተማረች ሆና ሳለ በስህተት ይህን መቀበል አልነበረባትም ሲል ክሱን ማሰማቱን ነግረውናል።

"በድጋሚ መቼ ፍርድ ቤት እንደምትቀርብ ቁርጥ ያለ ቀን አይታወቅም" የሚሉት እህቷ ቤተልሔም በቻይና ሕግ መሠረት አንድ ሰው ፍርድ ቤት ከቀረበ ከሃያ ቀናት አሊያም ከወር በኋላ የመጨረሻው ብይን እንደሚሰጥ መረጃ እንዳላቸው ይናገራሉ።

በዚህም መሠረት የናዝራዊትን የመጨረሻ ብይን በተስፋ እየተጠባበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እርሳቸው እንደሚሉት በእስር ላይ ያለችውን ናዝራዊትን በአካል መጎብኘት ባይቻልም ሁለት ጊዜ ደብዳቤ ልካላቸዋለች።

"መጀመሪያ አካባቢ የጉዳዩ ክብደት አልገባትም ነበር፤ እመጣለሁ ነበር የምትለው። አሁን ላይ ክብደቱም ገብቷት ጭንቀቷ ጨምሯል" ሲሉ ናዝራዊት ስላለችበት ሁኔታ ያስረዳሉ።

በደብዳቤዋ ላይም 'የተሳሳተ ሰው በማመኔ ቤተሰቦቼንም እኔንም ብዙ መስዋዕትነት አስከፈልኩ፤ ወጥቼ አኮራችኋለሁ' የሚል ሃሳብ አስፍራለች።

እንደ ቤተሰብ አሁንም በወር የተወሰነ ገንዘብ እንደሚልኩላትና ቻይና ያለው የኢትዮጵያ ኤምባሲም ዲፕሎማቶች በወር አንድ ጊዜ እንደሚጎበኟት፤ አስፈላጊ በሆነበት ጊዜም እንደሚሄዱ ገልፀዋል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

@tsegabwolde @tikvahethiopia

Report Page