#M

#M


የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ አርብ ሐምሌ 26 ቀን 2011 ዓ.ም የሕግና የፍትህ ግንዛቤ ማስጨበጫ ጉባዔ ላይ የጠቀሱት ምሳሌ መነጋገሪያ ሆኗል።

ፕሬዝዳንቷ ምሳሌውን የሰጡት አንድ ግዛት የፍርድ ቤት ውሳኔን አልቀበልም ካለ በኃይል ማስከበር እንደሚያስፈልግ ለመግለፅ ከወደ አሜሪካ አንድ ተሞክሮ በመምዘዝ ነበር።

ምሳሌው፤ በአሜሪካ በ1950ዎቹ የነጮችና የጥቁሮች የትምህርት እድልን አስመልክቶ ከጥቁሮች የቀረበውንና ፍርድ ቤት የወሰነውን ግዛቷ አልቀበልም በማለቷ በወቅቱ አገሪቷን ያስተዳድሩ የነበሩት ፕሬዚደንት ድዋይት አይዘንአወር ውሳኔውን ለማስፈፀም ኃይል መጠቀማቸውን የሚገልፅ ነበር።

ታዲያ ይህ የፕሬዚደንቷ ንግግር የትግራይ ክልል ላይ ያነጣጠረ ነው ያሉ ወገኖች ነበሩ።

በወቅቱ በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የትግራይ ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ አቶ አማኑዔል አሰፋ ጉባዔው የተጠራው የፍትህ አካላት፤ ፖሊስ፣ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ማረሚያ ቤትና ከፍትህና ከሕግ ዘርፍ ተያያዥ ጉዳዮች የሚሰሩ አካላት የያዘ እንደነበር ያስታውሳሉ።

በተለያየ ጊዜ በክልልም ሆነ በፌደራል ደረጃ እየተገናኙ የሚሰጠውን የፍትህና የሕግ ዘርፍ አገልግሎት እንደሚገመግሙና እቅድ እንደሚያወጡ የሚናገሩት አቶ አማኑኤል የአሁኑ መድረክ ግን ፖለቲካዊ ሃሳቦች የተነሱበት ነው ይላሉ።

የሰብዓዊ መብት ጥሰት አለ፤ ዜጎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ በሰላም መስራት አይችሉም፤ የሕግ የበላይነት አይከበርም፤ በመሆኑም የራሳችን ሥራ ላይ ትኩረት አድርገን እንወያይ የሚል ሃሳብ ቢቀርብላቸውም ፕሬዚዳንቷ ለመቀበል ዝግጁ እንዳልነበሩ አቶ አማኑኤል ይናገራሉ።

"እንደውም በውይይቱ ላይ መገኘት የሌለባቸው አካላትም ተገኝተዋል" ሲሉ ጥያቄ ሲያቀርቡ ያዩዋቸውን ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ የሚመሩትን ግደይ ዘርዓፂዎንን ይጠቅሳሉ።

"መድረኩ የፖለቲካ ስለነበረ መቅረት የነበረብን እኛ ነን እነሱ አልነበሩም" ሲሉ የውይይት መድረኩ ገለልተኛ በሆኑ የፍትህ አካላት መካከል የተደረገ እንዳልነበር ያስረዳሉ።

አቶ አማኑዔል እንደሚሉት በዚህ መልኩ የቀጠለው ውይይትም በ1950ዎቹ የነበረ የነጮችና የጥቁሮችን የትምህርት እድል አስመልክቶ፤ ነጮችና ጥቁሮች እኩል መማር አለባቸው በሚል የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ፤ ግዛቷ ውሳኔውን ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆኗ በወቅቱ የነበሩት የአሜሪካ ፕሬዚደንት አይዘን አወር ወታደራዊ ኃይል ተጠቅመው ውሳኔው እንዳስፈፀሙ ገልፀው፣ ኢትዮጵያ ከዚህ እንድትማር ምክረ ሃሳብ ሰጥተው ከእኩለ ቀን በፊት የተካሄደው ውይይት መጠናቀቁን ያስታውሳሉ።

በወቅቱ በርካታ ጥያቄዎች ሲነሱ ስለነበር ፕሬዝዳንቷ ያነሱትን ምክረ ሃሳብ ለመደገፍም ለመቃወምም ጊዜ አልነበረም የሚሉት አቶ አማኑዔል ከሰዓት በኋላ በነበረው ቆይታ ዋናው ጉዳዩ ሌላ በመሆኑና የመሩትም ሌሎች በመሆናቸው ይህንን ሃሳብ መልሶ ለማንሳት የፈቀደ አልነበረም ብለዋል።

ይሁን እንጂ በምሳ እረፍት ወቅት በተሳታፊዎች መካከል የተለያዩ ሃሳቦች ሲንሸራሸሩ እንደነበር አልሸሸጉም።

እርሳቸው እንደሚሉትም ሲነሱ ከነበሩት ሃሳቦች መካከልም ገለልተኛ ከሆነ የፍትህ አካል እንዲህ ዓይነት ሃሳብ መነሳቱ አግባብ አይደለም የሚል ነበር።

"መልዕክቱ ለማንም ይሁን ለማን፤ በኢትዮጵያ ያሉ ችግሮች መፈታት ያለባቸው ሕገ መንግሥቱን መሰረት በማድረግ መሆን አለበት፤ ካልሆነ አገሪቷን ወደ ሌላ አቅጣጫ ሊያመራት ይችላል" ሲሉ አቶ አማኑኤል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

አክለውም "ሃሳቡ ከፍተኛ አደጋ የሚያስከትል፣ ተገቢነት የሌለው፣ ሕገ መንግሥታዊ ያልሆነ፣ ገለልተኛ በሆነው የፌደራል ፍርድ ቤት መነሳት ያልነበረበት ነው" ሲሉ ኮንነውታል።

ጉዳዩን አስመልክተን ለመጠየቅ ወ/ሮ መዓዛ ጋር ደጋግመን ስልክ ብንደውልም ልናገኛቸው ስላልቻልን የፌደራል ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሰለሞን እጅጉን በጉዳዩ ላይ ሃሳብ እንዲሰጡን ጠይቀናቸው ነበር።

እርሳቸው እንደሚሉት የውይይት መድረኩ በዚህ በሽግግር ወቅት ፍርድ ቤቶች የሚያጋጥሟቸው ችግሮች ምንድን ናቸው? በሚል ከተወያዮች የተለያዩ ሃሳቦች የተነሱበት ነበር።

ከዚህም ባሻገር የፍርድ ቤት ውሳኔዎች በየአካባቢው እየተከበሩ አይደለም፤ ፍርድ ቤቶች የሚሰጧቸው ውሳኔዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ ፍርድ ቤቱ ምን እየሰራ ነው የሚሉ አበይት ጥያቄዎች ተነስተውበታል።

ፕሬዚዳንቷም እነዚህን ጥያቄዎች በሚመልሱበት ወቅት በአገሪቱ ውስጥ የተለያዩ ክልሎች መካከል መስማማት አለመኖሩን ፣ ችግሮች መኖራቸውን፣ የፍትህ አካላትም መውሰድ የሚገባቸውን እርምጃ መውሰድ በሚችሉት መጠን እየወሰዱ አለመሆኑን መጥቀሳቸውን አቶ ሰለሞን ይናገራሉ።

አቶ ሰለሞን እንደሚሉትም ምሳሌው የፍርድ ቤት ውሳኔዎች በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ተፈፃሚ መሆን አለባቸው፤ እንዲፈፀሙ የሁሉም አካላት ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ ለመናገር የመዘዙት ምሳሌ ነው- የአሜሪካው ተሞክሮ።

መንግሥታት የፍርድ ቤት ውሳኔዎችን ለማስፈፀም እስከምን ድረስ መሄድ እንደሚችሉ ፕሬዝዳንቷ በምሳሌው ለማስረዳት መሞከራቸውን ይናገራሉ።

ንግግራቸው ትግራይ ክልል ላይ ያነጣጠረ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ለሚሰጡ ሰዎችም "ንግግሩ ሌሎችንም የተመለከተ ነበር" ሲሉ ምላሽ ሰጥተውናል። በንግግራቸውም በተለያዩ ክልሎች እየተፈፀሙ ያሉ ድርጊቶችን ሲያነሱ እንደነበርም ገልፀዋል።

የምሳሌው አግባብነትን በተመለከተ ያነሳንላቸው አቶ ሰለሞን "የፍርድ ቤት ትዕዛዝና ውሳኔን ለማስፈፀም ሊደረጉ ከሚገባቸው ነገሮች መካከል አንዱ ማሳያ ተደርጎ ነው የተወሰደው፤ ዲሞክራሲያዊ የሆነ የፍትህ ሥርዓት ሰፍኖባቸው የሚታዩ አገራት በእንደዚህ ዓይነት ተግዳሮት ውስጥ አልፈው ነው እዚህ የደረሱት ለማለት እንደማሳያነት መጠቀሱ አግባብነት የለውም የሚል ሃሳብም አቋምም የለኝም" ሲሉ የግል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

"የትኛውም የፍርድ ቤት ውሳኔ የማይፈፀም ከሆነ ፍርድ ቤት የለም ማለት ነው" የሚሉት አቶ ሰለሞን አስፈፃሚው አካል የፍርድ ቤት ውሳኔን የማስፈፀም ኃላፊነቱን መወጣት አለበት ይላሉ።

ይህ ካልሆነ ግን ትርጉም እንደሌለው ከማስረዳት በዘለለ ፕሬዝዳንቷ ያነሱት ምሳሌ እንዲህ ዓይነት ውዝግብ ያመጣል ብለው እንደማያምኑ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

Via ቢቢሲ አማርኛ

@tsegabwolde @tikvahethiopia

Report Page