#Kira

#Kira

KIRA


ሕዝብ አራቋቹ ቁማር- "ቤቲንግ"


ዶ/ር ኤልያስ ገብሩ አዕምሮ 


‹ቢ.ቢ.ሲ አፍሪካ› ከጥቂት ወራት በፊት በኡጋንዳ፣ ካምፓላ ከተማ አንድ ጥናታዊ ፊልም ሰርቶ ነበር፡፡ ታዲያ ጥርሶቹን ሰግስጎ አፍሪካን ስለነከሳት የኳስ ቁማር (ቤቲንግ) ቢዝነስ የሰራውን ይህንን ጥናት የተመለከተ ሁሉ ክው ማለቱ አልቀረም፡፡ ኢትዮጵያችንን ጨምሮ በሌሎችም የአፍሪካ አገራት የኳስ ቁማር (ቤቲንግ) የብዙዎችን ህይወት እያመሰቃቀለ ይገኛል። ታዳጊዎችን ጨምሮ ሌሎችም የኳስ ጨዋታ ተመልካቾች እንደቀልድ የሚጀምሩት ይህ ቁማር ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታቸው እያስቀረ፣ ወጣቶች የሌላቸውን ፍራንክ እንዲያጡ፤ ትዳር አፍርሶ ቤተሰብ እየበተነ፣ አልፎም አደገኛ ሱስ ሆኖ ለአዕምሮ ህመም እየዳረጋቸው እንደሆነ አሳይቶናል ። በሌሎች አገራት ብዙዎችን አክስሯል፣ አሳብዷል፣ አንዳንዶችን ራሳቸውን እስከማጥፋት አድርሷል፤ እኛም ጋር መሰሪ ተልዕኮው ስር እየሰደደ ይገኛልና ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ ዝምታው በጊዜ መሰበር እንዳለበት አምናለሁኝ።


እግር ኳስና ቁማር? (ለካምፓኒዎች ምርጡ የመዝለቂያ በር)


እግር ኳስ ምድር ላይ ከተፈለሰፉ የሰው ልጅ የውድድር መድረኮች እጅግ ማራኪ፤ የተጫዋቹንና የተመልካቹን ልብ ከፍና ዝቅ የሚያደርግ፤ በሰላማዊ ጦርነት የተለያዩ አገራትንና ቡድኖችን የሚያገናኝ፣ የራሱ ስርዓትና ደንብ ያለው ስፓርታዊ ጨዋታ ነው። ሰዎች የሚወዱትን ቡድን ደግፈው ይመለከታሉ፥ መለዮውን ለብሰው ይደምቃሉ፥ በስሜት ይዘምራሉ፥ በቡድናቸው ድል ይፈነድቃሉ፣ ኮከቦቻቸውን እያደነቁ ጮቤ ይረግጣሉ፥ በሽንፈቱ ጊዜ ደግሞ በሀዘን ያነባሉ፣ ከቡድናቸው ጋር አብረው ይቆዝማሉ። ይህ ሁሉ ድጋፍ፤ የአብሮነት መንፈስ፤ ሰላማዊ የውድድር መድረክ ደስ የሚል፣ ልብን የሚገዛ ትልቅ አንድምታ አለው። ይሄ ነፃ የውድድር መድረክ የቁማር አውድማ ሲሆን፣ ንጹሁ ስፖርታዊ ፍቅር ወደ ተስፋ መቸብቸቢያ፣ ትርፍ ማግኛና ያልሰሩበትን ብር መሰብሰቢያ መሳሪያነት ሲቀየር ግን ያሳዝናል። 


ሳይኮሎጂስቶች ሰዎችን ማሳመንና መጠቀም ከፈለግኸ በሚወዱት፣ በደካማ ጎናቸው መምጣት ወደር የሌለው አማራጭ ነው ይላሉ፡፡ እናም እግር ኳስ በሚሊዮኖች ልብ ውስጥ ነግሶ የተቀመጠ፣ ግዙፍ ተከታታይና ደጋፊ ያለው በመሆኑ አቋማሪዎች ለኣላማቸው እጅግ ተመራጭ አውታር ሆኖ አግኝተውታል፡፡ ይህንን መጥፎ ድርጊት የሚቃወመው የቀድሞ የአርሴናል ተጫዋችና የእንግሊዝ ብሔራዊ-ቡድን አንበል የነበረው ቶኒ አዳምስ እንዲህ ይላል፡-


“እግር ኳስ በራሱ በቂ የሆነ ውድድር ነው፤ በታዳጊዎች ላይም ግዙፍ ተቀባይነት አለው፡፡ ነገር ግን እግር ኳስና ቁማርን አንድ ላይ አድርጎ ማቅረብና መተግበር በተለይ በትናንሽ ልጆች ላይ መጥፎ ተጽእኖ አለው፡፡ ቁማርን እንደ መልካም የሚቀበል ትውልድ በቴክኖሎጂው እድገት እጁ ላይ ባለው ሞባይልና ኢንተርኔት ታግዞ መክሸፉ አይቀርም፡፡” 

ይብስ ክፋቱ ከ50 በመቶ በላይ የእንግሊዝ ፕርሚየር ሊግ ቡድኖችና ከ30 በመቶ በላይ የቻምፒዮንስ ሊግ ቡድኖች በቤቲንግ ካምፓኒዎች ስፖንሰር መደረጋቸው ነው፡፡ አሁን ደግሞ ካምፓኒዎቹ የአህጉራችን አፍሪካ ቡድኖችንም ስፖንሰር በማድረግ በማንኪያ ሰጥቶ በአካፋ የመውሰድ መንገዱን ተያይዘውታል፡፡ እናም ቀድሞ በተዘጋጀላቸው ነፃና ሰፊ የኳስ ሜዳ ትርፋቸውን እያካበቱ እንደልባቸው ሊፈነጩበት ጉዞ ጀመረዋል፡፡ 


‹ቤቲንግ› ከኛ አገር ነባራዊ ሁኔታና ባህል አንጻር


ከጥንት ከመሰረቱም የኛ ሰው “የቆጡን አውርድ ብላ የብብቷን ጣለች” እያለ አጉል ምኞትና ተስፋ እንደሚጎዳን ሲናገር ኖሯል፡፡ እርግጥ ቀደምቱ ቱባ ወግና ባህል በትክክል ተወርሷል ወይ የሚለው ነጥብ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ቢሆንም ከሞላ ጎደል በኛ ባህሎች ውስጥ ቁማር እንደመጥፎ ሙከራ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ከመቆመር ይልቅ በእቁብ በመቆጠብ የላቡን የሚበላ ማኅብረሰብ ነበረን፡፡ ይሁንና ሰባ በመቶ ወጣት ባጥለቀለቃትና ስራ-አጥነት በተንሰራፋባት አገራችን ቁማር ተጫውቶ ብር ለማግኘት ጉጉ የሆነ ሰው ማግኘት አዳጋች አይደለም፡፡ እነዚህ የቱርክ፣ ቻይናና እንግሊዝ… ትርፋማ ካምፓኒዎች ባደጉት አገራት ሲከለከሉ አልያም የራሳቸውን ወጣት ዜጋ መጉዳት ሳይፈልጉ ሲቀሩ የኛ አፍሪካውያን ምስኪን (ያልነቁ) ወጣቶች ላይ ማነጣጠራቸው እሙን ነው፡፡ አክሱም፣ አቢሲኒያ፣ ላሊበላ ወዘተ… እያሉ በቤተኛ፣ በምንወዳቸውና በምናከብራቸው ስሞች ተሸፍነው እየመጡ በኢትዮጵያ ቅርንጫፋቸውን የከፈቱት ዓለም አቀፍ አቋማሪዎች፤ በብዙ የአፍሪካ አገራት የወጣቱን ህይወት ያመሰቃቀሉት ናቸው።


እነሆ እኛም ጋር ይሄ አዲስ ሱስ ወጣቱን ጠልፎ፣ ከትምህርት፣ ከእቅድና ከሥራ እያራቀ ላም አለኝ በሰማይ የሚል ኮበሌ እየበዛልን ነው፡፡ በግምት የሚኖር፣ በምኞት ጤፍ፣ በህልም የተጋገረን የተስፋ እንጀራ የሚቃርም ወጣት እየበዛልን ነው፡፡


ቁማር፣ ‹ቤቲንግ› ከሐይማኖት አንጻር) 

የሐይማኖት ሰባኪ ባልሆንም ከ99 በመቶ በላይ ሐይማኖተኛ ባለባት አገር እንዲህ አይነት ማኅብረሰባዊ አንቅኆት የሚሹ ጉዳዮች ላይ ሐይማኖትን ማካተቱ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ 

ከክርስትና አንጻር 

እንግዲህ የቁማር ትልቁ ‹ሞቲቭ› ወይም ገፊ ኃይል ብር ማግኘት (መብላት) ነው፡፡ ክርስትና ደግሞ ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነው ብሎ የሚያስቀምጥ ሲሆን ብዙ የሐይማኖቱ ሊቃውንት ከቁማር ጋር አያይዘው የሚጠቅሱት ይሄ ጥቅስ የሚከተለው ነው፡፡ 

9፤ ዳሩ ግን ባለ ጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ።


10፤ ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፥ አንዳንዶች ይህን ሲመኙ፥ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ።


11፤ አንተ ግን፥ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ከዚህ ሽሽ፤ ጽድቅንና እግዚአብሔርን መምሰል እምነትንም ፍቅርንም መጽናትንም የዋህነትንም ተከታተል።)


....(1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ ምዕራፍ 6፤ 9-11) 


ከእስልምና አንጻር 

(እናንተ ያመናችሁ ሆይ! የሚያሰክር መጠጥ ቁማርም ጣዖታትም አዝላምም ከሰይጣን ሥራ የኾኑ እርኩስ ብቻ ናቸው፡፡ (እርኩስን) ራቁት፣ ልትድኑ ይከጀላልና፡፡) 

(ቅ.ቁርዓን፤ ሱረቱል ማዒዳ 5 - 90) 

> ከላይ በሁለቱም ቅዱሳን መፅሐፍት እንደጠቀስኩት ቁማር ከባድ ኃጥያት ነው። እልፍ የክርስትና ሃይማኖት አባቶች ቁማርን ተቃውመው ጽፈዋል፣ ሰብከዋል። በእስልምና ደግሞ በግልፅ የተከለከለ ነው። 

ኢኮኖሚያዊ ኪሳራው በአገርና በህዝብ ላይ 

‹ቤቲንግ› ከእግር ኳስ መሰረታዊ ሃሳብ፣ ከኛ ባህል ጋር መጋጨቱንና ሐይማኖታዊ ኃጢያትነቱን ባንቀበል እንኳን ይህንን ወጣት በቁማር ሱስ ጠመዶ የሕዝብና የአገርን ገንዘብ እየበዘበዘ መሆኑን መካድ አንችልም። ሲጀመር አንድ ቢዝነስ አዋጭ ካልሆነ የትኛውም ካምፓኒ ኢንቬስት አድርጎ፣ ሠራተኞች ቀጥሮ አያሰራም፡፡ ሞኝ ካምፓኒ የለም! ይልቁንም ይሄ ስራ ለካምፓኒዎቹ እጅግ አዋጭ ነው፡፡ ቁማሩ የኢትዮጵያን ከተሞች ጨምሮ በበርካታ ቦታዎች በከፍተኛ ፍጥነት እየተንሰራፋ መሆኑ ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው። በአገራችንም ከ20 ብር ጀምሮ እስከ ብዙ ሺህ ብሮች በማስያዝ እየተካሄደ ለኛ እዚህ ግባ ከማይባል ጠቀሜታው ይልቅ የውጭ ባለሐብቶችን ገንዘብ በማዛቅ ላይ ይገኛል። ምስኪኑን ወጣት እያረሱት ነው ብል ማጋነን አይሆንብኝም። ወጣቶች ከስንት አንዴ ብልጭ የሚሉ አሸናፊዎች መካከል አንዱ እሆን ብለው በተስፋ የሌላቸውን ብር ይገብራሉ።


ምናልባት "አታካብድ! 20 ብር ባወጣና ብገምት ምን ሃጃ አለው?" ልትለኝ ትችላለህ፤ ነገር ግን

Part 2


...ሚስጥሩ ሌላ ነው፡፡ ካምፓኒዎቹ ቀመሩን የሚጫወቱት በግለሰብ ደራጃ ባሉ ተስፋ የማድረግ፣ የአሸናፊነት ፍላጎት፣ የእልህና የመርሳት ተፈጥሯዊ የሰውኛ ባህሪዎች ነው፡፡ በትንሽ ትንሹ ዓመቱን በሙሉ 10.000 ብር መበላትህን ሳይሆን በዓመት አንዴ 5000 መብላትህን ብቻ እንድታስበው ይቀርጹሐል፡፡ አሸንፎ ብር ስላገኘው አንዱ ሰው እንጂ ተሸንፎ ብሩን ስላጣው ሚሊዮን አይወራም/ አይነግሩህም፡፡ ነገር ግን የግምቶችንና የቁማር ማስያዣውን ሒሳብ የሚሰራው የቤቲንግ ቀመር ‹አልጎሪዝም› ስርዓቱ የተዋቀረው በዋናነት የካምፓኒዎቹን ጥቅም ለማስጠበቅ ነው፡፡ የሚገርመው ነገር ቁማር ያስያዙ ሰዎች እርስ በርስ ተበላልተው፣ ታክስ ተከፍሎበት የተጣራው ትርፍ ወዳካውንታቸው ይገባል እንጂ ካምፓኒዎቹ አንዳችም ወጪ የለባቸውም፡፡ እናም አንድ ሰው በቤቲንግ የፈለገውን ያህል ብር ቢበላ ከካምፓኒው አካውንት ወጥቶ ሳይሆን ከሌሎች ከተበሉ ቆማሪዎች ተወስዶ ነው የሚሰጠው፡፡ ለምሳሌ በቢ.ቢ.ሲ ጥናታዊ ፊልም መሰረት የኡጋንዳ ቆማሪዎች በአማካይ በወር እስከ አንድ ሚሊዮን ዶላር ብር የሚያሲዙ ሲሆን ከዚህ ውስጥ በአማካይ 300000 ዶላሩ አንዳችም ብር ወዳላወጡት ካምፓኒዎች ሒሳብ ገቢ ይሆናል፡፡ ታዲያ ይሄንን ሒሳብ ለበርካታ የአህጉራችን አገራት ስንመታው አፍሪካና ወጣቶቿ በየወሩ ብዙ ሚሊዮን ዶላር ለአውሮፓና እስያ ባለሐብቶች እየገበሩ መሆኑን እንረዳለን፡፡ ለመቀበል የሚከብድ መራራ እውነታ ነው፡፡ ነገሩን ይበልጥ ውስብስብ የሚያደርገው ደግሞ የመንግስት ባለስልጣናት ከካምፓኒዎቹ በሚቀበሉት ጥቅማ ጥቅምና ጉቦ ምክንያት የነርሱ ጠበቃ ሆነው መገኘታቸው ነው፡፡ ቤቲንግን ለማቆም ሲታገል የነበረው የኡጋንዳው ሚኒስትር ከስልጣን መባረርና ወኅኒ መውረድ ለዚህ በቂ ማሳያ ይመስለኛል፡፡ እናም ይሄንን ጉልበቱን አፈርጥሞ የመጣ ደዌ መመከተ ከባድ ፈተና እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡ 


ታዲያ ቤቲንግ ጉዳቱ እንዲህ ዘርፈ ብዙ ነው ካልን ምን እናድርግ? 

መፍትሔ - ከማን ምን ይጠበቃል? 

ከማኅብረሰብ - ወላጆች ለልጆቻቸው ጠንካራ ተግሳጽ መስጠት አለባቸው፣ ሽማግሌዎች ይህ ነገር ውስጥ የሚሳተፉ፣ በአካባቢያችሁ ያሉ ወጣቶችን ከዚህ እንዲወጡ መምከር፤ ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያሻል፤ 

ከሚዲያ አካላት - ለዚህ ችላ ለተባለ አደጋ በቂ ትኩረት መስጠት፣ በየሬዲዮና በቴሌቪዥን መስኮቶች፣ በመጽሔትና ጋዜጣዎች ማኅብረሰቡን ማንቃት፣ በተለይም የስፖርት ጋዜጠኞች ይህንን መልዕክት የማዳረስ ትልቅ የዜግነት ኃላፊነት አለባቸው። 

ከሐይማኖት ተቋማት - ቤቲንግ ቁማር ስለመሆኑ ማስተማርና የሚቆምር ሰው ኃጢያት ውስጥ እንደገባ ማሳሳበ ያሻል፤ 

ከመንግስት - ከተቻለ እነዚህን ካምፓኒዎች ሙሉ ለሙሉ ከስራ ማገድ፣ ካልተቻለ ግን የሚከፍሉትን ታክስ ከ30 ፐርሰንት በላይ ማድረግ፣ በዚህ በ‹ቤቲንግ› ውስጥ የሚሳተፉ ሰዎች መታወቂያ እንዲያሳዩና ከ25 ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶች እንዳይቆምሩ የእድሜ ገደብ ማስቀመጥ (ከዚህ በታች ሲያስቆምሩ የተገኙ ካሉ በሕግ ማገድ)፣ እነዚህ ቢዝነሶች ማኅብረሰቡ ላይ ያላቸውን እውነተኛ ተጽእኖ በሚገባ በማስጠናት ውጤቱ ላይ የተመሰረተ እርምጃ መውሰድ፤ 

ከወጣቱ (ቤቲንግን ከሚጫወተው) - ይሄ ትውልድ ብዙ ፈተናዎች የተሸከመ ቢሆንም በስራ ማጣትና መሰል ችግሮች ነገው የጨለመበት ቢመስለውም እጅ ሳይሰጥ፣ በማያዛልቁ፣ በማይጨበጡ የውሸት ተስፋዎች ሳይሸወድ በእምነት፣ በእውቀትና በጽናት ያለመውን የሚያሳካ ወጣት እንዲሆን እመክራለሁኝ። እነሆ በጊዜ ንቁ! ዙሪያችሁ ላይ ያሉትንም አንቁ! 


ሻሎም!

Join our telegramm channel!!

@NATIONALEXAMSRESULT

@NATIONALEXAMSRESULT

Report Page