ሐምሌ ገብርኤል(፲፱)

ሐምሌ ገብርኤል(፲፱)

ዘ ልዑል Ⓜዲያቆን ዘልዑል ምናሉ

​​ ቅዱስ ገብርኤል


✝💚💛❤✝💚💛❤✝💚💛❤✝💚💛❤✝

በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን።

ስዕለ መላኩ ቅዱስ ገብርኤል በዘልኡል


እንኳን ለታላቁ መልአክ ለቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል አደረሳችሁ አደረሰን!!!


በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት ሐምሌ 19 የቅዱስ ገብርኤል አመታዊ በአል ነው፡፡ ይህ ቀን ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ቅድስት እየሉጣንና ልጇን ቅዱስ ቂርቆስን ከሞት አደጋ እንደታደገበት የሚታሰብበት ዕለት ነው። የሐምሌ 19 ስንክሳርና የሐምሌ ወር ድርሳነ ገብርኤል እንዲህ ተርከውታል፡፡


በዘመነ ሰማእታት ከሐድያን ነገሥታትና መኳንንት በክርስቲያኖች ላይ መከራ አጽንተውባቸው ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ብዙዎች ሰማእትነትን ሲቀበሉ የተቀሩት አገር ጥለው ተሰደዱ። እየሉጣም የሦስት ዓመት ህፃን የነበረውን ቅዱስ ቂርቆስን ይዛ ሸሸች በዚያም የሸሸችውን መኮንን አገኘችው ሰዎችም ነገር አሰሩባት ወደእርሱ አስቀረባት እና ስለ አምልኮ ጠየቃት እርሷም መኮንን ሆይ ዕድሜው ሦስት አመት የሆነው ህፃን አለ አማልክቶችህን ማምለክ መልካም እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ያስረዳን ዘንድ እሱን ጠይቅ አለችው፡፡ 


ህፃኑም ወዳለበት ጭፍራውን ልኮ ወደእርሱ አስመጣው ህፃኑም ፊቱ ብሩህና ደስተኛ እንደሆነ አየውና አንተ ደስተኛ ህፃን ሆይ እንዴት ነህ አለው፡፡ ህፃኑም መልሶ አዎ ለኔ ተጠብቆልኛል ላንተ ግን ሐዘንና ለቅሶ ጥርስ ማፋጨትም ነው፡፡ መጻሐፍ ለዝንጉዎች ተድላ ደስታ የላቸውም ብሏል እና አለው፡፡ እግዚአብሔር ኃይልና ንግግርን ሰጥቶታልና ብዙ ተናገረ በዚያም ያሉትን እስካስደነገጣቸው ድረስ ንጉሱን መኳንንቱንና ጣኦታቱን ረገማቸው፡፡ከብርታቱም የተነሳ አደነቁ፡፡ 


መኮንኑም በአፈረ ጊዜ በያይነቱ በሆነ ስቃይ ታላላቆች የማይችሉትን ታላቅና አስጨናቂ የሆነ ስቃይን አሰቃየው እናቱንም ከእርሱ ጋር አሰቃያት፡፡ እግዚአብሔርም ያለ ምንም ጉዳት ያነሳቸው ነበር፡፡ ብዙዎች አህዛብም ይኸንን አይተው አደነቁ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስም አምነው በሰማእትነት አረፉ፡፡ የሰማእትነትንም አክሊል ተቀበሉ፡፡ በህፃኑም ላይ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ አደረበት፡፡ ታላላቅ ድንቆችና ተአምራቶችንም አደረገ ብዙዎች በሽተኞችንም አዳናቸው፡፡ 


መስፍኑም በውስጡ ሰም፣ ጨው፣ ባሩድ፣ ሙጫ የዶሮ ማር፣ እርሳስ፣ ብረት፣ ቅንጭብ፣ ቁልቋል ጨምራችሁ ታላቅ የብረት ጋን አንጡልኝ ብሎ ጭፍሮቹን አዘዛቸው፡፡ ጭፍሮቹም እንዳዘዛቸው ካአደረጉ በኋላ ያዘዝከንን ሁሉ ፈጽመን እሳቱ ነዶ ፈልቷል፡፡ ድምፁ እንደነጐድጓድ ይጮኸል ወላፈኑም እንደጸሐይ ነጸብራቅ በሩቁ ይጋረፋል፡፡ የፍላቱም ኃይል በ14 ክንድ ያኽል ከፍታ ወደ ላይ ይዘላል፡፡ እንግዲህ በውስጡ የሚጣሉትን እዘዝ አሉት በዚህ ጊዜ ህፃን ቂርቆስና እናቱ እየሉጣ በክርስቶስ ስም ስለሚያምኑ አስረዋቸው ነበርና ከፍላቱ ሊጨምሯቸው ከእስር ቤት አወጧቸው፡፡ 


በዚያም ፍላቱ ወደላይ በሚዘል ብረት ጋን ውስጥ ለመጨመር ሲወስዷቸው የነዚህን ቅዱሳን አሟሟት ያዩ ዘንድ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲሰበሰቡ አዘዛቸው፡፡ በዚህን ጊዜ ቅድስት እየሉጣ የፍላቱን ጩኸት በሰማችና ባየች ጊዜ ተሸበረች፡፡ ተዘጋጅቶላት ከነበረው ክብር ልታፈገፍግ ሞከረች፡፡ ልጇ ቅዱስ ቂርቆስ ግን እናት ሆይ ከዚህ የብረት ጋን ግርማ የተነሳ አትፍሪ ድንጋጼም አይደርብሽ አናንያንና አዛርያን ሚሳኤልንም እግዚአብሔር ከእቶነ እሳት እንዳወጣቸው ሁሉ እኛንም ከዚህ ከብረት ጋን ሊያወጣን ችሎታ ያለው መሆኑን አትጠራጠሪ፡፡ 

ስዕለ ህፃን ወእሙ ቅድስት እየሉጣ


እናት ሆ ከዚህ ከሚያልፈው ዓለም ጭንቅና መከራ ለመዳን ስትይ በማያልፈው ዘላለማዊ እሳት ለመቀጣት ትመርጫለሽን ይኽስ አይሆንም ይቅርብሽ፡፡ በአሁኑ ጊዜ እግዚአብሔር በመካከላችን አለና ይረዳናል፡፡ እናት ሆይ ሶስናን ከእደ ረበናት /መምህራነ አይሁድ/ ዳንኤልን ከአፈ አናብስት ያዳነ እርሱ እኛንም ከጋን ፍላት ያወጣናል፡፡ ይልቁንም እግዚአብሔር በዚህ የብረት ጋን ውስጥ ግዳጃችንን ልንፈጽም ፈቅዶ ከሆነ ኢዮብ ንብረቱንና ገንዘቡን ልጆቹንና ሚስቱን በመጨረሻም የተፈጥሮ አካሉን ባሳጣው ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ እግዚአብሐር ሰጠ እግዚአብሔር ነሳ እግዚአብሔርም እንደወደደ አደረገ ከማለት በስተቀር ምንም የተናገረው ነገር እንደሌለ ሁሉ እኛም የሱን ዓላማ በመከተል ይኽንን መከራ ልንታገስ ይገባናል፡፡ 


ነገር ግን እናቱ በዚህ ምክር ልትጽናና ባለመቻሏ ቅዱስ ቂርቆስ ዐይኑን ወደ ሰማይ አቅንቶ አቤቱ አምላክ ሆይ ይችን ባሪያህን ከርስትህ የምትለያት ከሆነ ከባለሟልነትህ መጽሐፍ ፋቀኝ፤ አቤቱ አዝመራውን አቃጥለ ፍሬውን ልትባርክ ትወዳለህን ይኽን እንዳታደር ግን ቸርነትህ ትከለክልኸለች አቤቱ እንጨቱን ቆርጣችሁ አንድዱት ቅጠሉን ግን ጠብቁት ብለኽ ልታዝ መለኮታዊ ባሕሪህ አይደለም፡፡ ነገር ግን እንጨቱንም ቅጠሉንም በአንድ ጠብቁት ብለኽ ታዝዛለኽ እንጂ፡፡ እንግዲህ በዚህ ምክንያት ይኽንን ያየ ሁሉ ማዳን የሚችል አምላክ ቢኖራቸውስ ኖሮ ከእሳት ባልሸሹም ነበር ብሎ አይጠራጠር፡፡ 


አቤቱ ዲያብሎስም ከባለስልጣኑ ይልቅ እኔ በረታሁ ቅዱሳኖቹንም ድል ነሳኋቸው ብሎ እንዳይመካ ከመንጋውም አንድ በግ ቀማው በማለት እንዳይደነፋ ለእናቴ ጽኑ የሆነ ኃይለ መንፈስ ቅዱስን ስጣት ብሎ በጸለየ ጊዜ ዲያብሎስ ከእየሉጣ አጠገብ ብን ብሎ ጠፋ፡፡ ከዚህ በኋላ ቅድስት እናቱ በሰማያዊ መንግሥት አባት የሆንከኝ ልጄ ሆይ ጌታኽ ኃይልን ሰጥቶኛልና የሚጠብቀንን ገድላችንን ፈጽመን ድል እናድርግ እነሆ በብረት ጋን ውስጥ የሚነደውን እሳት በማይበት ጊዜ በለምለም /በምንጭ/ ላይ እንደሚወርድ ጠል ሆኖ አይቸዋለሁና አለችው።

​​እኒኽም ቅዱሳን ይኽንን በሚነጋገሩበት ጊዜ በውስጡ አንገትን የሚቆለምም ልብንም የሚያቀልጥ ሆድን የሚሰነጥቅ ሥርን የሚበጣጥስ መሳሪያ ካለበት የብረት ጋን ውስጥ ጨመራቸው፡፡ ከዚህ በኋላ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ከሰማይ ወረደና የብረቱን ጋን እሳት አጠፋው፡፡ ከቅዱሳኑም አንዳቸውንም ሳያቃጥላቸው የብረቱ ጋር ማቃጠሉና መፍላቱ ጸጥ አለ፡፡ 



ወንድሞቻችን ሆይ እንግዲህ በጭንቃቸው ጊዜ ገድላቸውን እስኪፈጽሙ ድረስ ይህ መልአክ ከሰማእታትና ከጻድቃን ጐን እንደማይለይ እወቁ ለኃጥአንም ኃጢአታቸውን ይቅር ይላቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ይጸልይላቸዋል፡፡ እኛም የዚህ የሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል በዓሉን እያከበርን አማላጅና ወዳጅ እናድርገው። በዚህም በሚመጣውም ዓለም ሊረዳን ይችላልና፡፡ 


ዳግመኛም መስፍኑ ሐሳቡ ሳይሳካለት ስለቀረ 14 የሾሉና የጋሉ የብረት ችንካሮች አምጥተው ሰባቱን በእናቱ በኢየሉጣ አካል ሰባቱን በራሱ በቂርቆስ አካል ማለት ሁለቱን በጆሮዎቹ ሁለቱን በዐይኖቹ ሁለቱን በአፍንጫዎቹ አንዱን በልቡ ይቸነክራቸው ዘንድ ጭፍሮቹን አዘዘ፡፡ ዳግመኛም የህፃኑን የእራስ ቆዳ ገፈው እሳት ውስጥ ይጨምሩ ዘንድ አዘዘ፡፡ 


አሁንም መልአኩ መጥቶ ይህንን መከራ ከእርሱ አራቀለት፡፡ ቀጥሎም በመቃን ውስጥ ጨምረው በገመድ እንዲጎትቱት አዘዘ፡፡ በዚህም ጊዜ መልአኩ አዳነው፡፡ ሕዝቡም ይህንን ሁሉ ተአምር ባዩ ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገኑት ቅዱስ ገብርኤልንም አከበሩት፡፡ ቅዱስ ቂርቆስና ቅድስት እየሉጣ ብዙ መከራ ከተቀበሉ በኋላ ጥር 15 በሰይፍ ተመትተው ስማትነትን ተቀብለዋል። 


የሊቀ መላእክት የቅዱስ ገብርኤል ፣ ቅዱስ ቂርቆስና የእናቱ የቅድስት እየሉጣ ተራዳኢነት ጸሎት አይለየን። ከዚህ በኋላ ሕፃኑን አስፈልገው ቢጠይቁት ነቢዩ ዳዊት የተናገረው ኃይለ ቃል መንፈስ ቅዱስ ተገልጾለት፤ ‹‹የአሕዛብ ጣዖታት የወርቅና የብር የሰው እጅ ሥራዎች ናቸው፡፡ የሚታመኑባቸውም ሁሉ እንደ እነርሱ ይሁኑ›› መዝ. ፻፴ በማለት ሲዘልፏቸው አገር ገዥው ሰምቶ ተቆጣና የብረት ጋን አስመጥቶ ውኃ ሞልቶ ከዕቶን እሳት ላይ ጥዶ ልዩ ልዩ ማገዶዎች በመጨመር ነበልባሉ ከመጠን በላይ ሆነ፡፡ የብረት ጋኑም ድምፅ እንደ ክረምት መብረቅና ነጎድጓድ እስኪያስፈራ ድረስ አስነድዶ ሕፃኑን ከነእናቱ ወስዳችሁ ጨምሩአቸው ብሎ አዘዘ፡፡ 


በዚህ ጊዜ ቅድስት ኢየሉጣ በጣም ፈራች፡፡ የእግዚአብሔር ሥራ እፁብ ድንቅ ግሩም ረቂቅ ነው፡፡ ገና አፉን ያልፈታ የሦስት ዓመት ሕፃን ‹‹እናቴ ሆይ! ገድላችን እንፈጽም ዘንድ ጨክኝ በርቺ›› አላት፡፡ ቅድስት ኢየሉጣም ‹‹ልጄ የነፍስ አባት ሁነኝ›› አለችው፡፡ ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስም ከዘመናቸው ሳይደርስ፣ ታሪካቸውን ሳይማር የሠለስቱ ደቂቅን ታሪክ መንፈስ ቅዱስ ገልጾለት ‹‹አናንያን፣ አዛርያንና ሚሳኤልን ያዳነ አምላክ ያድነናል›› ቢላት ፍርሃቱ ሊለቃት ባለመቻሉ፣ ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ጸለየ፡፡ 


‹‹ጌታ ሆይ! የወይኑን ፍሬ ስትሻ ግንዱን ታጠፋለህን? እንደዚህስ ሁሉ እኔን አድነህ እናቴን ታጠፋታለህን?›› ብሎ በጸለየጊዜ መንፈስ ቅዱስ አደረባትና መንግሥተ ሰማያትን በዓይነ ሥጋ እንድታይ አደረጋት፡፡ ከዚህ በኋላ ፍርሃቱ ለቀቃትና ‹‹ልጄ ሆይ! ከዛሬ ጀምሮ መምህሬ፣ አባቴ፣ መካሪዬ እልሃለሁ እንጂ ልጄ አልልህም›› ብላ በጭካኔ ከልጅዋ ጋር ወደ ፈላው የብረት ጋን ገባችበት፡፡ 


በዚህ ጊዜ ሕፃኑ ቂርቆስ አናንያን፣ አዛርያንና ሚሳኤልን ያዳነ አምላክ ያድነናል ያለውን ቃል ለመፈጻም እግዚአብሔር አምላክ መልአኩ

ቅዱስ ገብርኤልን ላከላቸው፡፡ መልአኩም በትእምርተ መስቀል እሳቱን ቢባርከው እንደ በረዶ ቀዝቅዞላቸዋል፡፡ በመልካቸውም እንደ ፀሐይ አበራ፡፡ ከእግር ጥፍራቸው እስከ ራስ ጠሩራቸው አንድም ሳይጎዳቸው በደህና ወጡ፡፡


በመጨረሻም ሕፃኑ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስ እንዲህ አለ፡፡ ይህን ያህል ገድል ተጋድዬ ምን ዋጋ ትሰጠኛለህ ቢለው፣ ጌታ በልብህ ያለውን ሁሉ እሰጥሃለሁ አለው፡፡ ዳግመኛም ሥጋህ በምድር ላይ እንዳይፈርስ እንዳይበሰብስ በኤልያስ ሠረገላ ላይ አኖርሃለሁ አለው፡፡ 


ስለሆነም በዚህ ዕለት ቤተክርስቲያናችን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ለእናታችን ለቅድስት ኢየሉጣ እና ለሕፃኑ ለቅዱስ ቂርቆስ ያደረገውን ይህን ታላቅ ተአምር ድንቅ ሥራ በማሰብ ከዋዜማው ጀምራ እግዚአብሔርን ስታመሰግን ትውላለች ታድራለች፡፡


የመልአኩ የቅዱስ ገብርኤል በረከት ተራዳኢነት ከሁላችን ጋር ይኑር አሜን።

 አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ የአጋንንትን ተንኮላቸውን ግለጥባቸው፤ በሚያገለግሉህ ባሮችህ አሳፍራቸው፤ በእውነት ያለ ሐሰት ይሁን ይደረግልን "

 ✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝       

      ወስብሐት ለእግዚአብሔር  

               ይቆየን 


የቻናላችን ፕሮፋይል ፎቶ በዲ.ን ዘልዑል


ቻናላችንን ይቀላቀሉን ለሌሎችም ሼር ያድርጉ 👇👇👇👇

✤ፍኖተ አበው ዘተዋሕዶ✤ https://t.me/Finote_Abew1 https://t.me/Finote_Abew1 

🕹 የእናተ አስተያየትና ጥያቄ ከዚህ የበለጠ ለመትጋት ይረዳልና መልእክት ይተውሉኝ፤ የተሳተውን፤ የተረሳው፤ የተገደፈውን፤ የነጠፈውን በቀና መንፈስ አቃንታቹ አንብቡት ቸሩ መድኃኔዓለም ማስተዋሉን ያድለን፤ በፀሎታቹ አስቡኝ አትርሱኝ የተለያየ ጽሁፍ ያላቹ፣ መተረክ እንችላለን የምትሉ ቻናሉንና ግሩፑን በተለያየ አገልግሎት ማገዝ የምትፈልጉ በውስጥ መስመር አናግሩኝ። 

  📩Coment- Telegram ላይ👇

       @Kibreleul

 @Mesikel_bot @Channals_Admin

  አዘጋጅ ዲያቆን ዘልዑል ምናሉ 

✥••┈┈┈••●◉ ✞ ◉●••┈┈┈••✥

Report Page