#IN

#IN


የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመገልገል በበርካታ ተበዳዮች ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲፈጸምባቸው በማድረግ ከባድ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል በማለት ክስ በተመሠረተባቸው፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ተቋም የቀድሞ ዋና ዳይሬክተርና ሠራተኞች ላይ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮችን መስማት ተጀመረ፡፡

ዓቃቤ ሕግ እንደ ክሱ ያስረዱልኛል በማለት በምስክርነት ከቆጠራቸው 131 ምስክሮች መካከል ስንቶቹን እንዳቀረበ፣ ክሱን እየሰማ የሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት ምስክርነቱን መስማት ከመጀመሩ በፊት ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ዓቃቤ ሕጉም ለምስክሮቹ መጥሪያ እንዲያደርስ ትዕዛዝ የደረሰው ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ መልስ መስጠቱን በመጠቆም፣ ምላሹ ምን እንደሆነ ፍርድ ቤቱ እንዲነግረው እሱም ጥያቄ አቅርቧል፡፡

ፖሊስ በጽሑፍ ምላሽ መስጠቱን አስታውቆ፣ ‹‹ምስክሮቹን ባስመዘገቡት አድራሻ ልናገኛቸው ስላልቻልን፣ በግል ስልካቸው ደውለን እንዲቀርቡ ነግረናቸዋል፡፡ በቀጠሮ ቀን የማይቀርቡ ከሆነ ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠንና አፈላልገን እናቀርባን፤›› በማለት ፖሊስ ምላሽ መስጠቱን ፍርድ ቤቱ ሲናገር፣ ዓቃቤ ሕግ በራሱ ያቀረባቸው አምስት ምስክሮች እንዳሉት አስመዝግቧል፡፡ ምስክሮቹ ቀርበው ማንነታቸውን ከተናገሩ በኋላ፣ በእውነት ለመመስከር ቃለ መሃላ (እንደ ሃይማኖታቸው) ፈጽመው እንዳበቁ ዓቃቤ ሕግ ስለሚመሰክሩት ፍሬ ነገርና በማን ላይ እንደሚመሰክሩ ጭብጥ አስይዟል፡፡

የመጀመርያው ምስክር አቶ ደርበው ደመላሽ በተባሉ ተከሳሽና በእሳቸው ላይ በቀረበው ስድስተኛ ክስ ላይ እንደሚመሰክር ዓቃቤ ሕግ ገልጾ፣ ተከሳሹ ማንነታቸው ላልታወቁ ግብረ አበሮቻቸው ትዕዛዝ በመስጠት ስላስፈጸሙት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚያስረዳለት ጭብጡን አስመዝግቧል፡፡

በዕለቱ ያቀረባቸው አራት ምስክሮች ደግሞ አቶ ነጋ ካሴ በተባሉ 15ኛ ተከሳሽና በእሳቸው ላይ ባቀረበው 27ኛ ክስ ላይ የሚመሰክሩ መሆኑንና ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ማረሚያ ቤቶች ከቂሊንጦ ቀጠሮ ማረፊያ ቤት ቃጠሎ ጋር በተያያዘ ስለደረሳባቸው ድብደባና ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚመሰክሩ መሆኑን በመግለጽ፣ ጭብጡን አስይዞ ከጨረሰ በኋላ ምስክርነቱን ማሰማት ጀምሯል፡፡

የዓቃቤ ሕግ ምስክር ሆኖ የቀረበው የመጀመርያው ምስክር፣ በደል ፈጽመውብኛል ስላላቸው ተከሳሽ አቶ ድርበው ደመላሽ ለፍርድ ቤቱ እንዲያስረዳ በዓቃቤ ሕግ ተጠይቆ እንደገለጸው፣ ወቅቱ ሐምሌ 2 ቀን 2005 ዓ.ም. ነበር፡፡ የእስልምና እምነት ተከታዮች ፆም ገብቶ ስለነበር ለፀሎት ወደ ጓደኞቹ ጋ ለመሄድ ታክሲ ለመያዝ እየተጓዘ ሳለ ጨለማ ቦታ ላይ ሲደርስ ከኋላ የሆነ ሰው ስለያዘውና ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት ስለነበር ይደነግጣል፡፡ ‹‹ምንድነው የምትፈልጉት? ያለኝን ገንዘብ ውሰዱና ልቀቁኝ፤›› ሲላቸው፣ የያዘው ሰው በቦክስ መቶት፣ ‹‹ደኅንነቶች ነን፡፡ የአንተን ገንዘብ የሚፈልግ የለም ቅደም፤›› ይሉታል፡፡ ቦታው ጦር ኃይሎች አካባቢ ሲሆን ሁለት ከፊት ሦስት ከኋላ ሆነው እሱን መሀል ላይ በማድረግ ወደማያውቀውና ሊያስታውሰው የማይችለው ጫካ ውስጥ እንደወሰዱት ተናግሯል፡፡ አህመድ ከሚባል ተጠርጣሪ ጋር ግንኙነት እንዳለውና እሱ ያለበትን ቦታ እንዲጠቁም ወይም እንዲያሳይ ሲጠይቁት፣ ‹‹የማውቀው ነገር የለም፣ አላውቀውም፤›› ሲላቸው፣ ‹‹አንተን ፍርድ ቤት ለፍርድ ቤት ሲያመላልስ የሚከርም የለም፤›› በማለት የወሰዱት ጫካ ውስጥ ገድለው እንደሚጥሉት በመንገር አንደኛው ሽጉጥ ማውጣቱንም አስረድቷል፡፡ በጣም ደንግጦና ፈርቶ ስለነበር፣ ‹‹እሺ አመጣለሁ፤›› ሲላቸው፣ በአካባቢ ባለው ፖሊስ ጣቢያ እንደወሰዱትና አስመዝግበው ትተውት እንደሄዱም ምስክሩ ተናግሯል፡፡

የያዙት የደኅንነት አባላት ሌሊት ላይ ተመልሰው በመምጣት በመኪና በማያውቀውና በማያስታውሰው ቦታ ሲያሽከረክሩት አድረው ጠዋት ላይ፣ ‹‹አህመድ ጋ ደውልለትና የምትገናኙበትን ቦታ ንገረው፤› እንዳሉትም አክሏል፡፡ ግንኙነቱ ከእነ ማን ጋር እንደሆነ፣ የት እንደሚገናኙ፣ የት እንደሚሠሩና እነ ማን እንደሆኑ ‹‹ግለጽ›› በማለት እላዩ ላይ ውኃ በመድፋት ሲገርፉት እንደሚያድሩና ከተከሳሹ አቶ ደርበው ቢሮ እንደሚያቀርቡት አስረድቷል፡፡ ዓቃቤ ሕጉ ጦር ኃይሎችን እንዴት እንዳወቀ ሲጠይቀው፣ አቶ ደርበው ስልክ ተደውሎላቸው ‹‹ጦር ኃይሎች›› ሲሉ ሰምቶ መሆኑንም ተናግሯል፡፡

ምስክሩ በተጨማሪ እንደመሰከረው፣ በፌስቡክ ከአንድ ከሚያውቀው ሰው ጋር እንዲጻጻፍ በማድረግ መረጃ እንዲሰጠው እንዲያደርግ ያስገድዱት እንደነበረና በአጋጣሚ መርማሪዎቹ ዞር ሲሉ ‹‹ለፌስቡክ ጓደኛው ተገድጄ ነው›› ሲለው ጓደኛው መጻፉን ሲያቋርጥ፣ ፊቱን ሸፍነው እንደወሰዱት ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል፡፡ ለሦስት ወራት ያህል ፀሐይና ቤተሰብ አይተውት እንደማያውቁ የገለጸው ምስክሩ፣ በደሴው የሃጅ ኑሩ ገዳዮች ላይ ምስክር እንዲሆን መገደዱንም ጠቁሟል፡፡  

አቶ ደርበው ባይደበድቡትም በጥቅሻ ሌሎች እንዲደበድቡት ያደርጉ እንደነበር፣ የሚደበድቡት መርማሪዎች አቶ ደርበው ቢሮ ወስደውት ቃሉን ራሱ ጽፎና ፈርሞ እንዲሰጥ አዘውት 1፡30 ሰዓት የፈጀ ሁለት ገጽ ቃሉን ጽፎ እንደሰጠም መስክሯል፡፡ ምን ብሎ እንደጻፈ ተጠይቆ፣ ‹‹በወቅቱ የነበረውን መንግሥት ተቃውሞ፣ ብተናን በሚመለከት፣ ዓርብ ዓርብ እንዴት እንደሚረበሽ…›› የሚገልጽ ነገር እንደጻፈ ተናግሯል፡፡

ሼህ ኑሩን ገድለሃል በሚል ጭምር መደብደቡን ገልጾ፣ ነገር ግን እሳቸው የተገደሉ ጊዜ እሱ አዲስ አበባ እንደነበር አስረድቷል፡፡ ሼሁን ገድለዋል በተባሉ ግለሰቦች ላይ እንዲመሰክር ተገዶ መመስከሩንና ከዚያ በኋላ ከእስር መለቀቁንም አክሏል፡፡ ነገር ግን ተከሳሾቹም በመከላከያ ምስክርነት ቆጥረውት፣ ተገድዶ እንዲመሰክር መደረጉን ለፍርድ ቤት መናገሩንም መስክሯል፡፡ ሃያ አራት ሰዓት የሚጠብቁት ሁለት ደኅንነቶች እንደነበሩ፣ ላፕቶፕ እያቀረቡና የሚጽፈውን እየነገሩት ከፌስቡክ ጓደኞቹ ጋር እንዲያወራ ያደርጉት እንደነበርና በአጠቃላይ ጦር ኃይሎች ሁለት ወራት ከአሥር ቀንና በሌላ ቦታ ሦስት ወር ከአሥር ቀናት በአጠቃላይ አምስት ወራት ከ21 ቀናት መታሰሩን አስረድቶ ምስክርነቱን አብቅቷል፡፡

 ለምስክሩ መስቀለኛ ጥያቄ ያቀረቡት የአቶ ደርበው ጠበቃ አቶ ዮሴፍ ኪሮስ፣ ‹‹የአቶ ደርበውን ስም ያወቅከው መቼ ነው?›› በማለት ሲጠይቁት፣ ‹‹አሁን እዚህ ፍርድ ቤት ነው ያወቅሁት፤›› ብሏል፡፡ በዕለቱ ፍርድ ቤት ከመስማቱ ውጪ ስማቸውን እንደማያውቅም አክሏል፡፡ ምስክሩ ሌሊት ሲመረመርና ሲደበደብ አቶ ደርበው ስለመኖራቸው ተጠይቆ፣ ‹‹አልነበሩም፤›› ብሏል፡፡ በደኅንነቶች እየተደበደበ እንዲያምን ከተደረገ በኋላ፣ ቃሉን እንዲሰጥ አቶ ደርበው ቢሮ እንደተወሰደም ገልጿል፡፡

አቶ ደርበው በራሳቸው፣ ‹‹ሃይማኖተኛ ነህና እውነቱን መስክር፤› በማለት ሊጠይቁ ሲሉ ፍርድ ቤቱ ጣልቃ በመግባት፣ ‹‹ሃይማኖተኛ ነህ በማለት ተፅዕኖ አታሳድሩ፤›› በማለት ካስጠነቀቃቸው በኋላ ጥያቄያቸውን ቀጥለዋል፡፡

‹‹ከእኛ ጋር ደኅንነት ተቋም ውስጥ እየተከፈለው ይሠራ ነበር፣ የደኅንነት አባል ነበር፤›› ካሉ በኋላ፣ ‹‹ለስልክህ ካርድ የሚሞላልህና ደመወዝ የሚከፍልህ ማን ነበር?›› የሚል ጥያቄ አቅርበውለታል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ቢቃወምም፣ ‹‹ለትክክለኛ ፍትሕ አሰጣጥ ይረዳል›› በማለት ፍርድ ቤቱ ጥያቄውን እንዲመልስ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ምስክሩ እንዲጠቀም የተደረገው በራሱ በመንግሥት መሆኑን ገልጿል፡፡ አቶ ደርበው ግን ምስክሩ የደኅንነት አባል እንደነበረ፣ ለስልክና ለቤት ኪራይ ይከፈልለት እንደነበረና ደመወዝተኛ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ከመቼ ጀምሮ እንደሆነ ማለትም ከታሰረበት ከሐምሌ ወር ጀምሮ ወይስ ከመታሰሩ በፊት ሲላቸው፣ አቶ ደርበው መታሰሩን እንደማያውቁና እንደማያስታውሱ ገልጸዋል፡፡ ምስክሩ ለምን እንደታሰረ ሲጠየቅም፣ የነበረውን ሥርዓት ስለሚቃወም መታሰሩን አስረድቷል፡፡

ደሴ በተገደሉት ሼህ ኑሩን በሚመለከት ሥራ ተሰጥቶት ሁለት ልጆች እንዲያዙ ስለማድረጉ ተጠይቆ፣ ተገድዶ መሥራቱንና በእሱ አማካይነት ሁለት ልጆች መታሰራቸውን ተናግሯል፡፡

አቶ ደርበው አለቃ መሆናቸውን እንዴት እንዳወቀ ተጠይቆ፣ ‹‹‹የሚያወሩት እንደ አለቃ ነበር፤›› ብሏል፡፡ ከተፈታ በኋላ የት ይኖር እንደነበር ተጠይቆ፣ ከጓደኞቹ ጋር የተወሰነ ጊዜ ቆይቶ ቤት በመከራየት ከባለቤቱ ጋር መኖር መጀመሩን አስረድቷል፡፡ መጀመርያ ሲያዝ አህመድ እንድሪስ የተባለውን ምን አድርገው እንደተባለ ተጠይቆ፣ ከእሱ ጋር ቀጠሮ እንዳለው ደኅንነቶቹ ያውቁና ይከታተሉ እንደነበር ገልጾ፣ ‹‹የቀጠርከኝ ቦታ ነኝ በል›› እንዳሉት፣ የሚያውቀውን እንዲያወጣና የሚያውቃቸውን ልጆች እንዲያመጣ ይገረፍ እንደበር ተናግሯል፡፡ በዚህ ጊዜ አቶ ደርበው ስለመኖራቸው ተጠይቆ፣ ‹‹አልነበሩም›› በማለት በድጋሚ ተናግሯል፡፡ አቶ ደርበውን ስማቸውንም ሆነ እሳቸውን ካላወቀ እንዴት አለቃ እንደሆኑ እንዳወቀ ተጠይቆ፣ ‹‹ገምቼ ነው፤›› ብሏል፡፡ ቃሉን አለቃ ቢሮ እንዲሰጥ ተብሎ እሳቸው ቢሮ ገብቶ 1፡30 ሰዓት በመፍጀት ሁለት ገጽ መጻፉንም ተናግሯል፡፡ የጻፈውም ስለ ‹‹ድምፃችን ይሰማ›› እና በፌስ ቡክ ያወሩ ስለነበረው መሆኑንም አክሏል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በድጋሚ ጥያቄ ምስክሩ ለፖሊስ ጣቢያ አቶ ደርበውን በሚመለከት ስላቀረበው አቤቱታ እንዴት እንደሆነ ሲጠይቀው (ስማቸውን አውቆ በወቅቱ ማስመዝገቡን ለማስታወስና አሁን አላውቃቸውም ዛሬ ነው ያወቅኳቸው፤ ያለውን ለማፋረስ ‹‹ስማቸውን ያወቅኩት ዛሬ ነው፡፡ በመልክ ነበር የማውቃቸው፤›› ብሏል፡፡

ፍርድ ቤቱ በማጣሪያ ጥያቄ ‹‹ስለአቶ ደርበው በምናብ ሲሳልልህ ደርበው ይሆናል ብለህ ደመደምክ?›› በማለት ሲጠይቀው፣ ‹‹አልደመደምኩም›› ብሏል፡፡ በመቀጠልም በዕለቱ አሳይ ሲባል ስላወቃቸው እንዴት እንደለያቸው ሲጠየቅ፣ ‹‹የበደለኝን ስለማልረሳ ከቀረበልኝ ብዙ ፎቶ መካከል ነው የለየኋቸው፤›› ብሏል፡፡ በፌስ ቡክ ሰላምን እንደሚያወሩ ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ ጥያቄ ሲያቀርብለት፣ በዕለተ ጁማ ዓርብ ዓርብ ስለሚደረገው ሠልፍ፣ ተቃውሞ እንዴት እንደሚረግ፣ ወረቀት እንዴት እንደሚበተን መሆኑን አስረድቷል፡፡

አቶ ደርበው እሳቸው በእሱ ላይ የፈጸሙት ሰብዓዊ መብት ጥሰት ምን እንደሆነ ጠይቀውት፣ ሲደበደብ በቀጥታ ትዕዛዝ ባይሰጡም እጃቸውን ወደ ኋላ በማድረግ ዝም ብለው ማየታቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰት መሆኑን አስረድቷል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በዕለቱ ሐምሌ 23 ቀን 2011 ዓ.ም. ያቀረባቸው ምስክሮች አምስት ቢሆኑም፣ ሪፖርተር ኅትመት የሚገባበት ቀን በመሆኑና የቀሪዎቹን ምስሮች የምስክርነት ቃል ማካተት ባይቻልም፣ ምስክርነቱ ግን ከቀትር በኋላም ቀጥሎ ውሏል፡፡

Via Reporter

Report Page