HOPE

HOPE

Henok Tsegaye

✝እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ 

   

@yerkgebeta

   

ለመንጋው ሁሉ በጎ እንደሚመኝ እንደ መልካም እረኛ እግዚአብሔር ለፍጥረቱ በሙሉ ያለምንም ጥርጥር በዝምታ ይሠራል ። ይሁን እንጂ ሰዎች በመከራ ውስጥ ሆነው የእግዚአብሔር መልስ ከዘገየባቸው እንደማይሠራ አድርገው ያስባሉ ።

እነርሱ እግዚአብሔር አይሠራም ብለው በሚያስብበት ሰዓት ሁሉ እርሱ ግን ለእነርሱ በጥልቅ እየሠራ ነው ። ሰዎች ይህንን ስለማይገነዘቡ የእግዚአብሔርን ሥራና የሥራውን ውጤት ፈጥነው ለማየት ይፈልጋሉ ። እነዚህ ሰዎች ግን በእምነታቸው ያመኑትን በዓይናቸው እስኪመለከቱ ድረስ ሊቆዩ ይገባቸዋል ። " እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ ፤ በርታ ልብህም ይጽና ፤ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ ። " [መዝ 26፥14 ] ። 


እግዚአብሔርን እንዴት እንጠብቅ?


እግዚአብሔርን የሚጠብቅ ሰው እርሱን በተስፋ ፤ በእምነት ፤ በተሞላ ሙሉ ልብና ያለምንም ድካም ይጠብቀዋል ። ይህ በመሆኑም እንደዚህ ዓይነቱ ሰው እግዚአብሔር በመካከል ገብቶ እንደሚሰራና ሁሉም ነገር ለበጎ እንደሚሆን ያምናል ። " እግዚአብሔር ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን ።" [ ሮሜ 8፥28] ። " እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ ፤ ይሮጣሉ አይታክቱም ይሄዳሉ አይደክሙም " [ኢሳ 40፥31] ። ኃይላቸው በመከራ የተናወጠባቸው ሁሉ እግዚአብሔርን በተስፋ በመጠባበቅ ኃይላቸውን ያድሳሉ ማለት ነው ። " ጎልማስነትሽን እንደ ንስር ያድሳል " የሚል ቃል ተጽፋል [ መዝ 102፥5] ። ስለሆነም ማንም ቢሆን እግዚአብሔር እምነት በተሞላ ብርቱ ልብና በእርሱ ላይ በመተማመን ይጠብቀዋል ።


ነገር ግን አንድ ሰው እግዚአብሔር እርምጃ እንደሚወስድና እርምጃውም ግልጽና ኃያል እንደሆነ መተማመን አለበት ። ከዚሁ ጋር እርምጃው በተመቻቸ ሰዓት ፍሬያማ በሆነ መንገድ የሚከናወን ነው ። እግዚአብሔር አንድ የሆነ እርምጃ ለመውሰድ ከወደደ ምንም የሚጠባበቀው ሰዓት አይኖርም ። ኢየሱስ ክርስቶስ " ... አብ በገዛ ሥልጣኑ ያደረገውን ወራትንና ዘመናትን ታውቁ ዘንድ ለእናንተ አልተሰጣችሁም አላለምን ? /ሐዋ 1፥7/ ። አንተ ችግርህን እግዚአብሔር እንደሚያቃልልህ በማመን መቼ ለችግርህ መፍትሔ እንደሚሰጥህ ሳታስብ በእርሱ እጅ ላይ ብቻ ጣለው ።

7፤ እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት። 1 ጴጥሮስ 5


ሔኖክ ጸጋዬ

http://t.me/yerkgebeta

Report Page