Moments | የሃበሻ ደርቢዎች ሁሉ እናት - በዚያች ሐሙስ

Moments | የሃበሻ ደርቢዎች ሁሉ እናት - በዚያች ሐሙስ

Mensur Abdulkeni

ሐሙስ ሐምሌ 10 ቀን 1995፡፡ ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት ገደማ፡፡

በአሰልጣኝነት ዘመኑ አመሻሽ ላይ መንግስቱ ወርቁ እንዲህ ተንሰቅስቆ አልቅሶ አያውቅም፡፡ ስዩም ከበደ በአንድ እጁ አዛውንቱን ኢንስራክተር አቅፎ በሌላ እጁ የተከፈተ የእጅ ስልኩን ይዞ ያነባል፡፡ ፊቶቻቸው ኮሶ እንደተጎነጨ ሁሉ በደስታ ለቅሶ ተሸብስቦ ተኮራምቷል፡፡ መንጌ በጨዋታው ውጣ ውረድ የስሜት መዘውር ውስጥ ተንጦ አጨራረሱ የፍጹም ደስታ ሲሆንለት እምባውን መቋጠር ሳይችል አልቃሻ ህጻን መስሏል፡፡ ከሚስማር ተራ ማዶ፣ በጅምር ግንባታ ላይ ያለው የናኒ ህንጻ ያገጠጠ ኮንክሪት ያንን ታሪክ ይታዘብ ይመስል ከጀርባቸው ቆሞ ይታያል፡፡

…በዚያች ሐሙስ ሸገር በሐምሌ ክብድ ደመና ስር ቀዝቅዛ፣ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስታዲየም በፉክክር ስሜት እንደ ዳቦ ምጣድ ግሏል፡፡
*
ዕድሜው በግምት ሰባት ዓመት የሚሆነው ልጅ አጠገቤ ወዳለው ባዶ ወንበር መጥቶ ተቀመጠ፡፡ ከጉልበቱ በታች የረዘመ 35 ቁጥር FUBU የአሜሪካ ፉትቦል ማሊያ ለብሷል፡፡ የታዳጊነት ወዝ ጀምሮታል፡፡ ሲናገር ቀልጠፍጠፍ ያለ እንግሊዝኛ ያበዛል፡፡ በተመልካች በተጨናነቁት የትሪቡን ወንበሮች ላይ በዕድሜ ትንሹ እርሱ ነው፡፡ መልከ መልካሙን ህጻን ‹‹ናቲ›› ይሉታል፡፡ ከጎኑ በዕድሜ ከፍ የምትል ሴት ልጅ ተቀምጣለች፡፡ ቆይቼ እህቱ መሆኗን ተረዳሁ፡፡ በስዎች በተጨናነቀው ትሪቡን ለሁለቱ ታዳጊዎች የሚሆን ቦታ አላጣም፡፡ አጠጋግተው ያስቀመጧቸው ህጻናት የአቶ አብነት ገብረመስቀል ልጆች ናቸው፡፡ የክለቡ ሊቀመንበር የሆኑት አባታቸው ብቻ ሳይሆኑ ቤተሰብ የዚያችን ቀን ድራማ ሊታደም፣ በቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ላይ በጊዜ ተገኝቷል፡፡

ናቲ እግር ኳስን በቅጡ ባይረዳም የዕለቱን ጨዋታ ወሳኝነት ሳያውቅ አልቀረም፡፡

‹‹የትኛውን ተጫዋች ትወዳለህ?›› ስል ጠየቅኩት፡፡

ለመልሱ አልዘገየም፡፡ በእንግሊዝኛ ቅላጼ ‹‹ኤሪክ›› ሲል መለሰልኝ፡፡ ሲናገር ‹‹ሪ››ን ዋጥ ያደርጋታል፡፡

ትንሹ ናቲ ብቻ ሳይሆን መላው የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች በኬንያዊያኑ አጥቂዎች ኤሪክ ሙራንዳና ፍራንሲስ ኦሙላኩ ብቃት ለዚያች የመጨረሻ ቀን ጨዋታ ደርሰዋልና ፍጻሜውን ያሳምሩልናል ብለው ይተማመኑባቸዋል፡፡ ክብሩን ለማስቀረት ማሸነፍ አለባቸው፡፡ አቻ ከወጡ ወይም ከተሸነፉና አርባ ምንጭ ጨርቃ ጨርቅ ድል ከቀናው ዋንጫው ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ያመራል፡፡

*

ረቡዕ ምሽት በጨዋታው ዋዜማ አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ወደ መኖሪያ ቤቱ የገባው በጊዜ ነው፡፡ ለዓይን ሳይዝ ከቤቱ ደርሷል፡፡ ባለፉት ሶስት ቀናት በማያቋርጥ ራስ ምታት ታሞ ሰንብቷል፡፡ ሐሙስ በቀረበች ቁጥር የአሰልጣኙ ጭንቀት እየጨመረ ሄዶ ከቤተሰቡ አባላት ጋር በቅጡ ወግ ይዞ መጫወት እንኳን አቅቶታል፡፡ በአካል ይገኝ እንጂ በመንፈስ በመካከላቸው አልነበረም፡፡ በቀውጢ ጊዜ ስልቱ እንደጠፋበት የጦር ጄኔራል በድኑ ብቻ ይንቆራጠጣል፡፡ እስከዚያች ምሽት ድረስ አእምሮው እንደዚያ የተወጠረበትን ቀን አያስታውስም፡፡

ባለቤቱ ስታናግረው መልሱ ከርዕስ ውጭ እየሆነባት ታዝባዋለች፡፡

የአሰልጣኙ ትውልድ ከወደ ደሴ ነው፡፡ ዘመድ አዝማድ ከወልዲያ፣ ደሴና አዲስ አበባ መጥቶ በስዩም ቤት ተሰባስቧል፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀባት ደሴ ወላጅ እናቱ እየደወሉ ‹‹አይዞህ ልጄ!›› ይሉታል፡፡ የእናቱ ጸሎት ከእርሱ ጋር እንደሆነ ያምናል፡፡ ግን ልዕለ ተፈጥሯዊ ኃይል ቢኖረውና 24ቱን ሰዓታት እንደ ቪዲዮ ፊልም ወደፊት አሩጦ የግጥሚያውን ውጤት አሁኑኑ ቢያውቀው ደስ ባለው ነበር፡፡

የጨዋታው ትርጉም ከባድ ነው፡፡ የጥሎ ማለፉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ቡና በካሳዬ አራጌ መሪነት በድጋፍ ጭፈራ የስታዲየሙን ካስማዎች ከሚያርደው ደጋፊው ጋር ታግዞ ከቅዱስ ጊዮርጊስ መንጋጋ ስር ዋንጫውን ቀምቶ ለአርባ ምንጭ ጨርቃጨርቅ ሊሰጥ ይችላል፡፡ ካልሆነም ከስዩም በፊት የነበሩ የፈረሰኞቹ አሰልጣኞች አደራውን ጠብቀው ያቆዩትን የዋንጫ ክብር በእርሱም ዘመን ተደግሞ በደስታ ማዕበል ሊንሻለሉ ይችላሉ፡፡

ሽንፈት ከመጣ ለስዩምና አብሮት ይሰራ ዘንድ ከጎኑ ለተሾመው መንግስቱ ወርቁ የሞት ያህል ነው፡፡ ስዩም ደግሞ ከሞት ዋዜማ ጦሽ ብሎ የሚተኛው ቅዱስ ጴጥሮስ አይደለም፡፡ ቤቱ ሁሉ አሸልቦ ሳለ፣ በደረቁ ሌሊት ጭንቀቱን ለማርገብ በድርጊት የተሞላውን የጄኪ ቻን ፊልም ከፈተ፡፡ ተዋንያኑ በካራቴ ጥበብ ሲንከረባበቱ ስዩም አይኑ ቲቪው ላይ ተተክሎ ያያቸዋል፡፡ ልቡ ግን አያስተውላቸውም፡፡ ከፊልሙ ሌላ ሰሞኑን የወጡትን መጽሔቶችና የስፖርት ጋዜጦች አገላብጧል፡፡ ግን አላነበባቸውም፡፡ እንዲሁ ባክኖ በዓይኑ እንቅልፍ ዝር ሳይል ጎህ ቀደደ፡፡ መከረኛዋ ሐሙስ ሰዓቷን መቁጠር ጀመረች፡፡

ከቤቱ ሲወጣ የትንሽ ልጁ ድንገተኛ ቃል ያልጠበቀው ማበረታቻ ሆነው፡፡

‹‹አባዬ! አይዞህ! ዛሬ ዋንጫ ትወስዳላችሁ!›› አለ ናትናኤል ስዩም፡፡

አሰልጣኙም ሆነ የክለቡ ሊቀመንበር ‹‹ናቲ›› ብለው የሚያቆላምጧቸው በዕድሜ ተቀራራቢ ልጆች አሏቸው፡፡ የስዩም ናቲ ወደ ስታዲየም ባይመጣም አባቱን በሞራል ደግፎ ሸኝቷል፡፡ የአብነት ናቲ ደግሞ በፍልሚያው ዳር አባቱን ካጀቡት የፈረሰኞቹ ማህበረሰብ አባላት ጋር ክፉ ደጉን፣ ደስታ ሃዘኑን ሊካፈል በትሪቡን ታዛ ስር ወንበር ይዞ ተቀምጧል፡፡

*

ሐሙስ ጠዋት በስታዲየሙ ዙሪያ እምቧይ ቢወረወር መሬት አይወድቅም፡፡ ስፍር ቁጥር የለሽ የቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ የተራራውን ጫፍ ፍልሚያ ሊታደም ቲኬት ፍለጋ ተኮልኩሏል፡፡ ቲኬት እንደ ሞት መድኃኒት የተፈለገበት፣ ከስታዲየም በሮች ጀርባ መግባት ለዕድለኞች ብቻ የተፈቀደበት ያ ቀን ይለያል፡፡ ከጨዋታው መጀመሪያ አምስት ሰዓታት በፊት የ30 ብሩ ቲኬት በጥቁር ገበያ 100 ብር ይሸጣል፡፡ ዋጋ ስም ነው፡፡ ለብዙዎቹ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች የዚያ ጨዋታ ቲኬት፣ ዋጋ የማይወጣለት፣ እጥፍ ድርብ ቢከፈልበት እንኳ የማይቆጭ ነበር፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊስ ማሊያ ከባድ ነው፡፡ አሰልጣኞችና ተጫዋቾች የደጋፊዎች የስሜት አደራ አለባቸው፡፡ አደራውን ስለመብላት ሲያስብ ስዩም ይጨነቃል፡፡ ሁለተኛነት አይበረታታም፡፡ በራሱ ውድቀት ነው፡፡ ሁለቱ አሰልጣኞች በዘመናት መካከል ማሊያውን ለብሰው ስሜቱን ተጋርተውታል፡፡ በአሰልጣኝነታቸው ደግሞ የቱታው ኃላፊነት ከብዶ ተጭኗቸዋል፡፡ ከእንግዲህ ሸክሙ የሚቀለው ዋንጫውን ሲያሸንፉ ብቻ ነው፡፡

*

ስዩም ማልዶ ወደ ቤተክርስቲያን አመራ፡፡ ለመኖሪያ ቤቱ ወደሚቀርበው ቅዱስ ዑራኤል ደብር ሄዶ ለፈጣሪው የልቡን ነገረው፡፡ ‹‹የዛሬውን ብቻ! ሌላ ቀን አላስቸግርህም!›› ሲል ተማጸነው፡፡

ወትሮ በቡድኑ ሆስቴል ሁለት፣ ሶስት ተከታይ የሚመገበው ጎልማሳ በምሳ ሰዓት እህል ውሃ ማለት አቃተው፡፡ እንደ ምንም አንድ ዳቦ ጨርሶ ለጨዋታው ተሰናዳ፡፡ ጭንቀቱ ግን ውሃን አልከለከለውም፡፡ ሶስት የታሸጉ ውሃዎች ይዞ ወደ ክፍሉ ገባ፡፡

ለቅድመ-ጨዋታ ስብሰባ ታክሲ ተሳፍሮ ወደ ስታዲየም ሲመጣ ከተሳፋሪዎቹ መካከል የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችም ነበሩ፡፡ ሹፌሩም የፈረሰኞቹ ደጋፊ ነው፡፡ ሹፌርና ተሳፋሪ ስዩምን በአደራ ወጠሩት፡፡ ‹‹የዛሬን…፣ የዛሬን አደራ!›› ይሉታል፡፡

ሹፌሩ በአደራ ብቻ አላበቃም፡፡ ቀጠለ፡፡


Report Page