#HG

#HG


በደቡብ ክልል ሲዳማ ዞን የተከሰተዉን ግጭት ተከትሎ ከ 470 በላይ ተፈናቃዮች በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ጉጂ ዞን ቦሬ ከተማ ተጠልለዉ እንደሚገኙ ተፈናቃዮች እና የአካባቢዉ ባለስልጣን ለጀርመንር ራድዮ ተናገሩ። ተፈናቃዮቹ ወደ ቦሬ ከተማ የተሰደዱት ከሲዳማ ወረዳ ሁላ (ሀገረ ሰላም) ወረዳ ከሚገኙት ጭሮ፣ ገላን፣ ጨልቤ እና ጋኙሬ ከተባሉ የገጠር ቀበሌዎች ነዉ።

አብዛኞቹ ከእነዚህ ቀበሌዎች የተፈናቀሉት ነዋሪዎች በእግር፤ ገሚሶቹ ደግሞ በተሽከርካሪ በመጓዝ ሕይወታቸዉን ማትረፍ መቻላቸዉን ለጀርመን ራድዮ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ አሁንም በቀበሌዎቹ የቀሩ በርካታ ነዋሪዎች በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የሚያዉቁት ነገር እንደሌለ አክለዋል። ተፈናቃዮቹ በመንደራቸዉ የተካሄደዉ ጥቃት ብሔርን መሰረት ያደረገ፣ በተደራጁ እና ስምሪት በተሰጣቸዉ ኃይሎች የተፈጸመ ነው ብለዋል። አባት እና ልጅ፣ ወጣቶችን ጨምሮ ቁጥራቸው በወል ያልታወቀ ሰዎች መገደላቸዉን፣ የመኖርያ ቤቶች እና አብያተ-ክርስትያናት መቃጠላቸዉን ገልጸዋል።

ተፈናቃዮቹ በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ጉጂ በሚገኘዉ በቦሬ ደብረ ገነት ቅድስተ ማርያም ቤተ-ክርስትያን ግቢ ዉስጥ ተጠልለዉ እንደሚገኙ የቤተክርስቲያኒቱ አስተዳዳሪ እና የአካባቢው ባለስልጣን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። የቅድስተ ማርያም ቤተ-ክርስትያን አስተዳዳሪ ቄስ አባ መላከ ገነት ተስፋማርያም እስከዛሬ ሰኞ ማለዳ ድረስ በቤተ-ክርስትያኒቱ 474 ከሀገረ ሰላም የመጡ ተፈናቃዮች በቤተ ክርስትያኒቱ ቅፅር ግቢ መድረሳቸዉን ገልጸዋል። በቤተ-ክርስትያኑ ከተጠለሉት ተፈናቃዮች መካከል በሀገረ ሰላም ቤተ-ክርስትያናቸዉ ተቃጥሎ የተሰደዱ ዲያቆናት እንደሚገኙበትም የደብሩ አስተዳዳሪ አመልክተዋል።

የቦሬ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገመዳ ጋሼ በበኩላቸዉ ከአገረሰላም የተፈናቀሉ ከ400 በላይ ነዋሪዎች ወደ ወረዳዉ መግባታቸዉን አረጋግጠዋል። በአሁኑ ወቅት የቦሬ ወረዳ አስተዳደር የከተማዋን ማኅብረሰብ በማስተባበር የዕለት ደራሽ ምግቦችን እና አልባሳቶችን ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

የሲዳማ ዞን በክልል ለመደራጀት ያቀረበዉ ጥያቄ ተግባራዊ እንዲሆን በሚጠይቁ ወጣቶች እና በፀጥታ አስከባሪዎች መካከል ባለፈው ሐሙስ ሐምሌ 11 በሀዋሳ የተቀሰቀሰው ግጭት ወደ ሌሎች የሲዳማ አካባቢዎች መዛመቱ ይታወሳል። በሲዳማ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ እና ግጭት ቢያንስ 34 ሰዎች መሞታቸዉን የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን) እና የአካባቢው ነዋሪዎች ለጀርመን ራድዮ ተናግረዋል።

Via ጀርመን ራድዮ

Report Page