GM

GM

ገራዶ ሚዲያ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሱዳንን አየር ክልል በመተው ሌሎች የበረራ መስመሮችን እየተጠቀመ ነው? 

ሞሃናድ የተባለ ከ1,700 በላይ ተከታዮች ያሉት የትዊተር ተጠቃሚ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሱዳንን አየር ክልል በመተው ሌሎች የበረራ መስመሮችን መጠቀም መጀመሩን የሚጠቁም መልዕክት ለጥፏል። ይህ በትዊተር ገጽ የተለጠፈ መልዕክት በአጠቃላይ 136 ጊዜ ተጋርቷል። መልዕክቱን ካጋሩት መካከል ከ100 ሺህ በላይ የትዊተር ተከታይ ያላቸው ግለሰቦች ይገኙበታል። 

ሞሃናድ መልዕክቱን ከፍላይት ራዳር 24 (flightradar24) መገልገያ በተወሰዱ ሁለት የስክሪን ቅጅዎች (screenshots) አስደግፏል። በስክሪን ቅጅዎቹ ላይ ንብረትነታቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆኑ ከጣሊያን ሮም ከተማ ወደ አዲስ አበባ እና ከፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ ወደ አዲስ በአበባ የሚያመሩ የበረራ ቁጥር ETH703 እና ETH705 አውሮፕላኖች የቀይ ባህርን መስመር ተከትለው በኤርትራ የአየር ክልል ወደ ኢትዮጵያ ሲያመሩ ይታያል።  

ኢትዮጵያ ቼክ የፍላይት ራዳር 24 መገልገያን በመጠቀም ባደረገው ማጣራት ከላይ የተጠቀሱት በረራ ቁጥር ETH703 እና ETH705 ከዚህ በፊትም ከሱዳን የአየር ክልል ይልቅ የቀይ ባህርን መስመር እንደሚጠቀሙ አረጋግጧል። ለዚህም ኢትዮጵያ ቼክ ፍላይት ራዳር 24 በጥር፣ በየካቲት እና በመጋቢት ወራቶች የሰበሰባቸውን የበረራ መረጃዎች ተጠቅሟል።  

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ቼክ የፍላይት ራዳር 24 መገልገያን በመጠቀም ባደረገው ማጣራት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላኖች በዛሬው ዕለት የሱዳንን አየር ክልል ሲጠቀሙ ተመልክቷል። በዛሬው እለት የሱዳንን የአየር ክልል ሲጠቀሙ ከተመለከታቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላኖች መካከል ከአዲስ አበባ ወደ ስፔን ዛራጎዛ ከተማ እና ከሱዳን ካርቱም ከተማ ወደ አዲስ አበባ የሚያመሩ የበረራ ቁጥር ETH3417 እና ETH345 አውሮፕላኖች ይገኙበታል። 

ፍላይት ራዳር 24 መቀመጫው በስዊድን አገር ያደረገ የበረራ መከታተል አገልግሎት ሰጪ ሲሆን በመላው አለም የሚደረጉ የንግድ በረራዎችን ይከታተላል። በፍላይት ራዳር መገልገያ የአውሮፕላኖችን መነሻና መድረሻ፣ የአውሮፕላኖችን አይነት፣ የበረራ ቁጥር፣ የበረራ ከፍታና ፍጥነት እንዲሁም ሌሎች መረጃዎችን በቀጥታ መከታተል ይቻላል። 

ኢትዮጵያ ቼክ ጉዳዩን በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የኢትጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳሬክተር ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛውን ያናገረ ሲሆን "የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሁንም የሱዳንን የአየር ክልል እየተጠቀመ ነው፣ የተቀየረ ነገር የለም። በትዊተር የተሰራጨው መልዕክት መቶ ፐርሰንት ውሸት ነው" የሚል ምላሽ አግኝቷል።

Report Page