GM

GM

ገራዶ ሚዲያ

ፓርቲዎች ለምረጡኝ ቅስቀሳው ምን ዝግጅት እያደረጉ ነው?

6ኛውን ሃገር አቀፍ ምርጫ በማስመልከት ፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ ማድረግ ጀምረዋል፡፡ ቅስቀሳው ሰኞ የካቲት 8 ቀን 2013 ዓ/ም ነው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የተጀመረው፡፡

ቅስቀሳው ከ2 ዓመታት በፊት በጸደቀው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነምግባር አዋጅ 1162/2011 መሰረትም ግንቦት 23 ቀን 2013 ዓ/ም ድረስ ይካሄዳል፡፡

ፓርቲዎች በአዋጁ በተቀመጠው መሰረት ምርጫው አራት ቀናት እስከሚቀሩት ድረስ የመቀስቀስ መብት አላቸው፡፡

ይህ ከአስተዳደሩም ሆነ ከማዘጋጃ ቤት ፈቃድ መጠየቅ ሳያስፈልገው፣ በጽሑፍ በማሳወቅ ብቻ የሚፈጸም ነው፡፡

ሕጋዊ ግዴታዎቻቸውን በማክበር በራሳቸውም ሆነ በደጋፊዎቻቸው አማካኝነት የድጋፍ ስብሰባዎችን የመጥራት ወይም ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ የማደራጀት መብት እንዳላቸውም በአዋጁ ተከትቦ ይገኛል፡፡

ይህን ታሳቢ በማድረግም አል ዐይን አማርኛ ፓርቲዎች መቀስቀስ ጀምረዋል ወይ? ከጀመሩስ እንዴት ባለ መንገድ እየሄዱበት ነው? በሚል ከተወዳዳሪ ፓርቲዎች መካከል የተወሰኑትን ጠይቋል፡፡

“የወረዳ መዋቅሮቻችንን ተጠቅመን በምንወዳደርባቸው የምርጫ አካባቢዎቻች ሁሉ እንቀሰቅሳለን” ያሉት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ናትናኤል ዘለቀ ይፋዊ የቅስቀሳ ማስጀመሪያ ክንውን ለማድረግ በሚያስችል እንቅስቃሴ ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡

ለዚህም የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ጭምር በተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ እና የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከነዋሪው ጋር ተወያይተዋል፡፡ በመርሃግብሩ እንዲገኙ ሲጋብዙ እንደነበርም ፓርቲው አስታውቋል፡፡

ኢዜማ ከክንውኑ ዋዜማ የፓርቲ ኮንፍረንሱን እንደሚያካሂድ የካቲት 04 ቀን 2013 ዓ.ም በኤልያና ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል።

አደራጅቻቸዋለሁ ካላቸው 435 የምርጫ ወረዳዎች መካከል 406ቱን ሊወክሉ የሚችሉ እጩዎችን መምረጡን ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡

የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን)ም በምወዳደርባቸው የሃገሪቱ አካባቢዎች ሁሉ የምርጫ ቅስቀሳዎችን አደርጋለሁ ብሏል፡፡

ቅስቀሳው የአደባባይ ሰልፎችን፣ የአዳራሽ ስብሰባዎችን እና ማህበራዊ ሚዲያን ጨምሮ በተለያዩ የብዙሃን መገናኛ መንገዶች የሚካሄድ ነው፡፡

ይህን የሚያቀላጥፉ፣ የሚያደራጁ እና ስልት የሚነድፉ “የቅስቀሳ ስትራቴጂስቶች” አሉኝም ብሏል አብን፡፡

ከአል ዐይን ጋር የስልክ ቆይታ ያደረጉት የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጣሂር መሃመድ “አብን ሃገር አቀፍ ፓርቲ እንደመሆኑ መጠን ቅስቀሳውን ዋና መስሪያ ቤቱ ከሚገኝበት ከአዲስ አበባ ይጀምራል” ብለዋል፡፡

የተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች እና አካባቢዎችን ጨምሮ “እንደየ አካባቢው ሁኔታ” ቅስቀሳ ሊያደርግ እንደሚችልም ነው የገለጹት፡፡

ሆኖም በኦሮሚያ እና በደቡብ የሃገሪቱ አካባቢዎች ሊያደርግ የሚችለው ቅስቀሳ “በሁኔታዎች እና በህግ አከባበር አዝማሚያዎች ላይ” ይመሰረታል እንደ ኃላፊው ገለጻ፡፡

በክልሎቹ የሚገኙ የፓርቲው የማስተባበሪያ ቢሮዎች ከተዘጉ መቆየታቸውን የሚናገሩት ኃላፊው ኦሮሚያ ክልልን እንደማሳያ በማንሳት “በመሪው ፓርቲ (ኦሮሚያ ብልጽግና) ጭምር ሳይቀር በአደባባይ ተፈርጀን በምንወገዝበት አሁናዊ የፖለቲካ ሁኔታ ለመቀስቀስ የሚቻል አይደለም” ብለዋል፡፡

አቶ ጣሂር ሁኔታውን “ተስፋ አስቆራጭ ነው” ሲሉ ነው የሚያስቀምጡት፡፡ ይህንንም ለምርጫ ቦርድ ደጋግመን አሳውቀናል ብለዋል፡፡

ሆኖም “ምርጫውን ትተን ልንወጣ የምንችል አይደለንምና ሁኔታዎች ባይስተካከሉ እንኳን ልናሳካ በምንችለው ልክ እንንቀሳቀሳለን” ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በቅርቡ ለውጡንና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ለመደገፍ በሚል በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በተካሄዱ ሰልፎች አብን እና ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ (ባልደራስ) እንዲሁም የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)ን መሰል ፖለቲካ ፓርቲዎች ቦርዱ ከተሰረዘው ህወሓት እኩል ተፈርጀው በአደባባይ ሲወገዙ ነበር፡፡

ይህንንም ቦርዱ “የፓርቲዎችን በእኩልነት የመወዳደር መብት ችግር ላይ የሚጥል ነው” በሚል በየደረጃው ያሉ የፓርቲው አመራሮች እና የመንግስት ኃላፊዎች በተመሳሳይ ተግባራት ከመሳተፍ እንዲቆጠቡ ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)ም በምርጫው እንደሚሳተፍ አስታውቋል፡፡ ሆኖም በምርጫው የሚኖረው ተሳትፎ የታሰሩ አመራሮቹ መፈታታቸውን ጨምሮ ተዘግተውብኛል የሚላቸውን ቢሮዎች መከፈትን በቅድመ ሁኔታ የሚያስቀምጥ ነው፡፡

ያለበለዚያ በምርጫው መሳተፉ ትርጉም እንደሌለው ነው ሰሞኑን ከአል አይን ጋር ቆይታ የነበራቸው የፓርቲው ሊቀመንበር መረራ ጉዲና (ፕ/ር) የገለጹት፡፡

“ምርጫን ምርጫ የሚያደርገው ፖለቲካዊ ከባቢው ነው” የሚሉት ሊቀመንበሩ “መንግስት ላቀረብናቸው መሰረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ ከሰጠን በሙሉ ልብ ወደ ምርጫው ለመግባት ዝግጁ ነን”ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ይህ ከሆነ ለምርጫው መዘጋጀት እንደማይቸግራቸውና አራት እና አምስት ቀናት ሊበቋቸው እንደሚችሉ ነው መረራ የገለጹት፡፡

አል ዐይን ገዢው ፓርቲ ብልጽግና ከቅስቀሳ እና ከተያያዥ የምርጫ ተግባራት ጋር በተያያዘ እያከናወናቸው ያሉ የቤት ስራዎችን ለማወቅ ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

ፓርቲው የፖለቲካ ፕሮግራሙን (ማኒፌስቶ) እና የምርጫ ምልክቱን ባለፈው ሰኞ የፓርቲው ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በሸራተን አዲስ በይፋ አስተዋውቋል።

Via AlAin

https://t.me/geradomedia

Report Page