#YAK

#YAK



"… እሳቱም፣ ዱቄቱም፤ ቂጣውም፣ ሃሳቡም፣ ምጣዱም፣ ምድሪቱም ለሁላችንም የምትበቃ ሆና ሳለ፤ እንዳትበቃ የምንጣላ፤ እንዳትበጀን የምንባጅ፣ ለምን እንደምንሆን ግራ ያጋባኛል" - አገልጋይ ዮናታን አክሊሉ

• ምንም እንኳን ግራ አጋቢ ሁኔታ ላይ ብንሆንም፤ ጭጋጋማው መሬት ነገሮችን አጥርተን እንዳናይ ቢጋርደንም፣ ፍርሃት አዛማች ነገሮች እዚህና እዚያ እንደ አስቀያሚ የቆርቆሮ ከበሮ ቢንኳኩም በሀገራችን ተስፋ አንቆርጥም።

• አፈናና ጭቆና በበረታበት ዘመን ድምጻቸው እጅግም ያልተሰሙ አካላት የነፃነት አየር በሚነፍስበት በዚህ ወቅት አየሩን በጥላቻ ትንፋግ ሞልተውት እዚህና እዚያ እያፈናቀሉና እያቃጠሉ ነው፤ የሚታዩት።

• በኢትዮጵያ ምድር ያለውን የጥላቻ እሳት የሚለኩሱት ሰዎች ነበልባሉ ወደእነርሱ የሚደርስ አይምሰላቸው እንጂ ጊዜ ምስክር ነው፤ የሚንቀለቀል ሰደድ ይገጥማቸዋል።

• የሚገርመው «ነፍሰ ገዳይ ሰው በቅድሚያ የገደለው ራሱን ነው» የሚል ብሂል ቀድሞም አለ፤ ምነው ከተባለ ለራሱ ክብር ያለው ሰው ሌላውን አያዋርድም፤ ለራሱ ፍቅር ያለው ሰው ሌላውን ለመጥላት ልበ ብርቱ አይሆንምና።

• እኛ በከፊል ወይም ከከፊል በበለጠ ያጣን የሚመስለኝ የርህራሄና የፍቅር ጀግንነት ነው። ፍቅር በልባችን ኖሮ መላዋ ምድር በደስታ ስትጠበን የሚሰማን መልካም እውነት፣ መገለጫው እርሱ ነው።

• ፍቅር የሌላቸው ሰዎች በጎ ህልም የላቸውም፤ ፍቅር የሌላቸው ሰዎች በቀቢጸ ተስፋ የሚራመዱ ናቸውና ሜዳውን ሲረግጡ እንኳን ገደል ነው፤ ብለው ይፈራሉ፤ ፍቅር የሌላቸው ሰዎች ከሌሎች ህብረት ማድረግን አይወዱም፤ ፍቅር የሌላቸው ሰዎች አቋራጭ መንገድን ለድላቸው መግቢያነት ይመርጣሉ።

• ስለዚህ አቋራጩ መንገድ፣ ደም የሚያፋስስና ጥፋት የሚያስከትልም ቢሆን ይመርጡታል እንጂ፤ በትዕግስትና በታሰበበት መንገድ መጓዝን የሰነፍ ሥራ አድርገው ነው፤ የሚያስቡት። ስለዚህ «ሁሉንም ወይም ምንም» ዋና መፈክራቸው ነው። ተስፋ በቆረጠ ሰው ፊት መገኘት ደግሞ ጭዳነት ነው።

• ከመካከላችን በሃሳብ ሞገድ የበረታ፣ ሌላ አብዲሳ አጋ፣ ሌላ አገኘሁ እንግዳ፣ ሌላ ባልቻ ሳፎ፣ ሌላ ሃብተጊዮርጊስ ዲነግዴ፣ ሌላ ደስታ ዳምጠው፣ ሌላ አሊቶ ሔዋኖ፣ ሌላ ገረሱ ዱኪ፣ ሌላ አቢቹ፣ ሌላ አሉላ አባ ነጋ፣ ሌላ አቡነ ጴጥሮስ፣ ሌላ የአርበኝነትና የቀለም ቀንዶች ማውጣትና ለሀገር በረከት ማብቃት አለብን።

• ክፉዎች፣ የጣሉን ሲመስላቸው እየተነሳን፤ የዘረሩን ሲመስላቸው እያንሰራራን ወደፊት እንራመዳለን እንጂማ ተሳልቀውብን አንቀርም፤ በተባበረ ክንዳችን፣ ጠባቡን የገበያ ደረታችንን እያሠፋንና የኢኮኖሚ ደዌያችንን እየፈወስን፣ በህብረት እንጠናከራለን እንጂ፤ እንደሚመኙት ተነጣጥለን ተሸመድምደን አንቀርም።

• እንነሳለን፤ እንቀጥላለን እንጂ አንቋረጥም፤ አናቋርጥም፤ ችግኞችን በመትከል የልምላሜ ባለቤቶች፤ እኩልነትንና አንድነትን በመዝራት የሰላምና የብልጽግና ጌቶች እንሆናለን!!!

Via የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

Report Page