GE

GE

Greatful-Ethiopia

በአዲስ አበባ ልዩ የመሬት ኦዲትና ምዝገባ እንደሚጀመር ምክትል ከንቲባው አስታወቁ!

በ2013 ዓ.ም. ዓብይ ትኩረት ከሚሰጣቸው ጉዳዮች ዋናው በከተማዋ የመሬት ይዞታ ላይ ልዩ ኦዲት ማካሄድና የመሬት ምዝገባ ማከናወን እንደሚሆን፣ የአዲስ ከበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢ/ር) ይፋ አደረጉ። ም/ል ከንቲባው ይህንን ይፋ ያደረጉት ከሐምሌ 27 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ቀናት በተካሄደው የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት ሰባተኛ ዓመት ሦስተኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ ነው። የከተማ አስተዳደሩ ትልቅ ሀብት መሬት እንደሆነ የተናገሩት ምክትል ከንቲባው፣ በሚከናወነው የመሬት ኦዲት ከዚህ ቀደም ያላግባብ የተወሰዱና ለረዥም ጊዜ ጥቅም ላይ ያልዋሉ ይዞታዎች እንዲመለሱ እንደሚደረግ ገልጸዋል። 


በሚደረገው የመሬት ኦዲትና ምዝገባ ተለይተው ለከተማ አስተዳደሩ እንዲመለሱ የሚደረጉት ይዞታዎች፣ ለሌላ ልማት እንደሚውሉ አስታወቀዋል። በኦዲት እንዲመለሱ የሚደረጉት ይዞታዎች፣ በተለይም የከተማዋ ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለል ጥቅም ላይ እንዲውሉ ቅድሚያ እንደሚሰጥ አስረድተዋል። 

‹‹የጋራ መኖሪያ ቤት ለማግኘት ተመዝግበው ለበርካታ ዓመታት እየተጠባበቁ የሚገኙ ነዋሪዎች፣በማኅበር ተደራጅተው የራሳቸውን የጋራ መኖሪያ ሕንፃ እንዲገነቡ ይደረጋል፤›› ብለዋል። በአሁኑ ወቅትም የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን የመኖርያ ቤት ጥያቄ ለመመለስ 125 ሺሕ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እየተገነቡ መሆኑን የተናገሩት ም/ል ከንቲባው፣እየተገነቡ ከሚገኙት ቤቶች መካከል 96 ሺሕ የሚሆኑት በ28/80 የቤቶች ግንባታ ፕሮግራም ሥር የተያዙ ሲሆን፣ቀሪዎቹ ሁለት ሺሕ ቤቶች ደግሞ በ40/60 የመኖሪያ ቤት ግንባታ ፕሮጀክት ሥር የተያዙ መሆናቸውን አስረድተዋል።


በሌላ በኩል ደግሞ ከወሰን ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎች የቤት ልማት ፕሮጀክቱን ያጋጠመው ተግዳሮት መሆኑ ተጠቅሷል። የከተማ አስተዳደሩ ኮዬ ፈጬ ተብሎ በሚጠራው የግንባታ ሳይት ላይ በተነሳበት የወሰን ጥያቄ ምክንያት፣ ገንብቶ ያጠናቀቃቸውን ዘጠኝ ሺሕ መኖሪያ ቤቶች ለነዋሪዎች ለማስተላለፍ ከሁለት ዓመታት ገደማ በፊት ዕጣ ቢያወጣም፣ ቤቶቹን እስካሁን ለነዋሪዎች ማስተላለፍ እንዳልቻለ ይታወቃል። ምክትል ከንቲባው የቤቶች ልማት ፕሮጀክቱ ከባንክ ዕዳ ጋር ተያይዞ የገጠመውን ችግር ለመፍታት የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ገልጸው፣ ከወሰን ጋር ተያይዞ የሚነሳ ጥያቄም ዳግም ችግር በማይፈጥርበት መንገድ ዕልባት እንደሚያገኝ አስታውቀዋል። 


በ2013 ዓ.ም. የከተማ አስተዳደሩ ዓብይ ተግባር ይሆናል ባሉት የመሬት ኦዲት ምዝገባ ላይም፣ ለመሬት ወረራ ምክንያት የሆነውን መሠረታዊ ችግር ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግ አስታውቀዋል። 

ለመሬት ወረራ ተጋላጭ ከሆኑት ይዞታዎች መካከል የከተማ አርሶ አደሮች ይዞታ እንደሆነ የተናገሩት ምክትል ከንቲባ ታከለ፣ በዚህ አካባቢ ሥርዓት ለማበጀትም ለከተማዋ አርሶ አደሮች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንደሚሰጥ ገልጸዋል። 

የከተማ አስተዳደሩ ለ2013 በጀት ዓመት ያቀረበውን 61 ቢሊዮን ብር በጀት ምክር ቤቱ ተቀብሎ አፅድቋል፡፡ ምክትል ከንቲባ ታከለ ወደ ኃላፊነት ከመጡበት ጊዜ አንስቶ ላከናወኗቸው ስኬታማ ተግባራት የዕውቅና ሽልማት አበርክቶላቸዋል።


የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ምክትል ከንቲባው በተለይ የሚከናወኑ ሥራዎች የከተማዋ ነዋሪዎችን ያማከለ እንዲሆን በማድረግ፣ ውጤታማ ሥራ በማከናወናቸው ሽልማቱን እንደተበረከተላቸው ተገልጿል።

በተለይም አስታዋሽ አጥተው ለዘመናት የተዘነጉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ማዕከል ያደረጉ ሥራዎችን በመሥራት ላበረከቱት አስተዋጽኦ፣ በተጨማሪም የከተማዋን ታሪካዊና የቱሪዝም መስህብነት የሚያጎሉ፣ እንዲሁም የነዋሪዎችን ችግር የሚፈቱና ኢኮኖሚያዊ ሚና ያላቸው ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ማስጀመራቸው በታሰበላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቅ በማስቻላቸው ለዕውቅና ሽልማቱ በምክንያትነት ተጠቁሟል።

በከተማዋ ለሚገኙ ተማሪዎች ምግብ፣ የትምህርት ቁሳቁስና ዩኒፎርም እንዲቀርብ አመራር መስጠታቸው ሥራውንም ተቋማዊ እንዲሆን ማድረጋቸው ተጠቅሷል።

በኢኮኖሚው ዘርፍም የከተማ ግብርና በስፋት በከተማዋ ባህል እንዲሆን ሐሳብ በማመንጨትና አመራር በመስጠት፣ እንዲሁም የዕደ ጥበብ ዘርፎች ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው እንዲጨምር እየሠሩ ያሉት ሥራ ስኬታማ መሆናቸው ተወስቷል።


Join us👇

Greatful-Ethiopia

Report Page