GE

GE

Greatful-Ethiopia

ለሚቀጥሉት 4 ወራት ለጤና ተቋማት ብቻ 130 ሚሊየን የአፍ እና አፍንጫ ሜዲካል ጭንብሎች እንደሚያስፈልጉ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ተናገሩ።

የጤና ሚኒሰትር ዶክተር ሊያ ታደሰ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የመከላከል ስራን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፥ የቫይረሱን ስርጭት ለመቀነስ የሚያስችሉ ግብአቶችን የሟሟላት ስራ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በተለይም በጤና ተቋማት ላይ ለሚገኙ የጤና ባለሙያዎች የሚሆኑ የሜዲካል ማስኮች አለማቀፋዊ እጥረት መኖሩን በመግለፅ፤ እንደ ሀገርም በዙ ክፈተቶች መኖራቸውን አንስተዋል።

ወረርሽኙ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ እንደ ሀገር 4 ሚሊየን ማስክ ብቻ እንደነበር የተናገሩት ዶክተር ሊያ፥ ከዛ በኋላ በተሰሩ ስራዎች ከ7 ሚሊየን በላይ ማስኮችን ለጤና ተቋማት ማሰራጨት ተችሏል ብለዋል።

እንደ ሀገርም የቫይርሱን ስርጭት ለመከላከል በሚሰራው ስራ በሚቀጥሉት 4 ወራት ለጤና ተቋማት ብቻ 130 ሚሊየን ሜዲካል ማስክ እንደሚያስፈልግ መለየቱን ነው ሚኒሰትሯ የተናገሩት።

የማስክ እጥረትን ለመፍታት ሲባል ከውጭ ሀገር ከማስመጣተ እንዲሁም በእርዳታ ከማግኘት በተጨማሪም በሀገር ውስጥ ጥራቱን የጠበቀ እና መስፈርቱን ያሟላ መስክ እንዲመረት ለማደርግም ከሚመለከታቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጋር እየተሰራ መሆኑን ሚኒስትሯ ተናገርዋል።

በተጨማሪም የመተንፈሻ አካል አጋዥ መሳሪያ ወይም ቬንትሌተር በአለም አቀፍ ደረጃ እጥረት ያለበት መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር ሊያ፥ ከዚህ በፊት ለዚሁ ስራ የሚውል እንደ ሀገር 22 ቬንትሌተሮች ብቻ እንደነበሩም አንስተዋል።

በጥገና የተስተካከሉ እና በእርዳታ የተገኙትን ጨምሮ አዲስ ግዥ ተደርጎም አሁን ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ 221 ቬትሌተሮች ዝግጁ መደረጋቸውንም ተናግረዋል።

የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የኦክስጅን ምርትን በሀገር ውስጥ በስፋተ እንዲመረት ማደረግ ላይም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን እና ምርቱ የሚቀርብባቸው 3 ሺህ 600 የኦክስጅን ሲሊንደሮችም በሀገር አቀፍ ደረጃ መሰራጨታቸውን ተናግረዋል።

እንደ ሀገር አሁን ያለው የቫይርሱ ስርጭት መስፋትን ተከትሎ ግብእቶችን ከማሟላት በተጨማሪ የምርመራ አቅምን ማሳደግ ላይም ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ዶክተር ሊያ በመግለጫቸው አንስተዋል።

በተለይ ባለፉት 3 ሳምንታት የተመዘገበው ውጤት በጣም አስፈሪና ስርጭቱ በማህበረሰቡ ውስጥ መግባቱን የሚያሳይ በመሆኑ ምርመራን ማስፋትና የበሽታውን ስርጭት ምን ላይ እንደሆነ የሚያሳየውን የአንቲ ቦዲ ምርመራ ማከናወን ትልቅ መፍትሄ ነው ብለዋል።

ዶክተር ሊያ አክለውም፥ የቫይረሱን ስርጭት ለመቀነስ የሰዎችን እንቅስቅሴ ከመገደብ ይልቅ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተቀመጡ ክልከላዎችን ሁሉም መተግበር ስርጭቱ እንዲቀንስ ለማድረግ ሁነኛ መፍትሄ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ከቤት ሲወጡ ማስክ ማደርግ ከዛ በላይ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ የራስን እና የቤተሰብን ጤና ለመጠበቅ ሁነኛ መፍትሄ ነው የሚሉት ዶከተር ሊያ፥ ህብረተሰቡም ቫይረሱ በፍጥነት እየጨመረ መሆኑን በመረዳት የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

© ፋና ብሮድካስት ኮርፖሬት

@GreatfulEthiopia

 "ትክክለኛ የመረጃ ምንጭ"


Report Page