#FT

#FT


"የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው"- የትምህርት ሚኒስቴር

የግል ባለሀብት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችንና ህብረተሰቡን በማሳተፍ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ትምህርት ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ትምህርት ቤቶች እንዲሰሩና መሳሪያዎች እንዲሟሉ እየተደረገ መሆኑን የሚኒስቴሩ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ወ/ሮ ሀረጓ ማሞ ለኢቲቪ ተናግረዋል፡፡

መምህራንንና ተማሪዎችን ማብቃት፣ ለትምህርት ቤቶች ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ካሪኩለሞችን በተማሪው ልክ የመቅረጽ ስራዎችን በመስራት የትምህርት ጥራት ማረጋገጫ ፓኬጆች እየተተገበሩ ይገኛሉ ተብሏል፡፡

የመምህራንን አቅም በተለያዩ መርሃ ግብሮች የማሳደግ ስራ፣ በተለይም የክረምት መርሃ ግብርና አጫጭር ኮርሶችን በመስጠት የመምህራንን አቅም የማሳደግ ስራ እየተሰራ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

ይህም የተማሪና መምህራንን ግንኙነት መልካም በማድረግ መምህሩ የተዘጋጀውን መጽሃፍ በተገቢው ሁኔታ አውቆ በማሳወቅ ለተማሪው እውቀት ለማስጨበጥ ይረዳል ነው የተባለው፡፡

የመምህራን ማህበር አደረጃጀት፣ የተማሪ ወላጅ ህብረት፣ በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲቋቋም በማድረግ ለትምህርት ጥራት መምጣት ትኩረት መሰጠቱም ተገልጿል፡፡

የትምህርት ቤቶች መስፋፋትና ለትምህርት የሚያስፈልጉ መሳሪያዎች መሟላት ለትምህርት ጥራት የራሳቸውን አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ያሉት ወ/ሮ ሀረጓ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶች እየተሰሩ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም ትምህርት ቤቶችን ምቹ የመማሪያ ቦታዎች የማድረግ ስራ እየተሰራ ሲሆን፣ ተማሪዎች በአቅራቢያቸው ውሃ፣ ቤተ መጽሃፍት፣ ላቦራቶሪ፣ አጋዥ መጽሃፍትና የኮምፒውተር ላቦራቶሪ እንዲጠቀሙና እውቀት እንዲያገኙ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን ወ/ሮ ሀረጓ ተናግረዋል፡፡

ትምህርት ቤቶችም ይህንን መሰረት አድርገው ምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ የሚለውን የማረጋገጥና ደረጃቸውን የማሻሻል ስራ ይሰራል ብለዋል ዳይሬክተሯ፡፡

በዋግህምራና ሰቆጣ አካባቢ የዳስ ትምህርት ቤቶች ደረጃቸውን እንዲጠብቁ የማድረግ ስራ መሰራቱም ለዚህ ዘርፍ ትኩረት መሰጠቱን ማሳያ ነው ተብሏል፡፡

በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ፣ ብቃቱ የተረጋገጠ፣ በስነ ምግባር የታነጸ፣ በሁለንተናዊ ጉዳዮች ተወዳዳሪ የሆነና ራዕይ ያለው ተማሪና ትውልድን መፍጠር የትምህርት ጥራት ዋናው ግብ መሆኑም ተገልጿል፡፡

Via etv

@tsegabwolde @tikvahethiopia

Report Page