FFf

FFf


ተመራቂ ተማሪዎችን ለማገዝ የሚረዳ ጥናታዊ ፅሁፍ ይፋ ሆነ

******************************

(ኢ.ፕ.ድ)

ተመራቂ ተማሪዎችን ለማገዝ የሚረዳ ነው የተባለለትና በጌጅ ኮሌጅ የተዘጋጀው ጥናታዊ ፅሁፍ ይፋ ሆነ፡፡

“ቢዝነስ፣ የስራ እድል ፈጠራና ልማት በሀገር እድገት ላይ ያላቸው ተግዳሮቶችና መልካም አጋጣሚዎች” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው ጥናት ዋና ትኩረቱ ስራ አጥነት ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።

ጥናቱን ያቀረቡት ዶክተር ፍፁም አባተ እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ ያሉ አብዛኛዎቹ የትምህርት ተቋማት ሀላፊነታቸው የሚመስላቸው ያስተማሯቸውን ተማሪዎች አስተምሮ ማስመረቅ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ ተቋማት ከዚህ ባሻገር የተመራቂዎቻቸውን የወደፊት እጣ ፋንታ ብሩህ በሚያደርግ ሀላፊነት የተሞላበት ተግባር ላይ ተሳታፊ መሆን አለባቸው፡፡

በጥናቱ በመፍትሄ ሃሳብነት የተለያዩ አማራጮች የቀረቡ ሲሆን፤ በዋናነትም የሥራ አጥነትን መጠን ለመቀነስ ተማሪዎቹን በጥናትና ምርምር መደገፍ እንዳለባቸው፣ ተቋማቱ ለተማሪዎቹ ሥራ በማፈላለግ ሂደት ተሳታፊ መሆን እንደሚገባቸው፣ ተማሪዎች ራሳቸው ከሥራ ጠባቂነት መንፈስ በመላቀቅ ስራ ፈጣሪነትን መላበስ እንደሚጠበቅባቸው ተብራርቷል።

የብዙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ችግር ተማሪዎቻቸውን በጥናትና ምርምር አለማገዛቸው ነው ያሉት ዶክተር ፍፁም፤ ከዚህ አንጻር ጌጅ ኮሌጅ ይህን ችግር በመፍታት አርአያነት ያለው ተግባር እየሰራ መሆኑን ጠቅስዋል።

ኮሌጁ በአሁኑ ወቅት 500 ተመራቂ ተማሪዎችን በቁሳቁስ እና በገንዘብ በመደገፍ ወደ ስራ ለማስገባት ዝግጅት መጨረሱን ዶ/ር ፍጹም ተናግረዋል።

ተመራቂ ተማሪዎችን ለማገዝ ትምህርት ተቋማቱ የመፍትሄው አንድ አካል መሆን አለባቸው ያሉት ጥናት አቅራቢው፤ ይህ አይነቱ ተግባር የሥራ አጦችን ቁጥር ለመቀነስ ሁነኛ መፍትሄ ነውም ብለዋል፡፡

የኮሌጁ ፕሬዝዳንት አቶ ዘሪሁን መንግስቱ በበኩላቸው፤ ኮሌጃቸው የተመራቂ ተማሪዎችን እጣ ፈንታ የተሻለ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ጥናቱ ትኩረቱን ያደረገው በተመራቂ ተማሪዎች ሥራ አጥነት፣ ለስራ አጥነቱ ምክንያት በሆኑ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ሲሆን፤ ጥናቱ ተገቢ በሆነ መንገድ ከተተገበረ ሥራ አጥነት በመቅረፍ አመርቂ የሆነ ውጤት እንደሚያመጣ በመድረኩ ተሳታፊዎች ታምኖበታል፡፡

#E

Report Page