EU

EU

https://t.me/feleginfo

ኢትዮጵያ በአውሮፓ ሕብረት አቅራቢነት የጸደቀውን የውሳኔ ሐሳብን ተቃወመች፦

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የአውሮፓ ሕብረት በኢትዮጵያ የትግራይ ክልልን በተመለከተ ለተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት አቅርቦ ያጸደቀውን የውሳኔ ሐሳብ ተቃወመ።

ዛሬ በተካሄደው 47ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት ሰብሰባ ላይ የአውሮፓ ሕብረት ከትግራዩ ግጭት ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንደሚያሳስበውና የኤርትራ ሠራዊት አባላት ከትግራይ በአስቸኳይ እንዲውጡ በመጠየቅ ያቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ተቀባይነት አግኝቷል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ ይህ የሕብረቱ የውሳኔ ሃሳብ ጊዜውያን ያልጠበቀ እና በፖለቲካ ፍላጎት የተላለፈ ነው ሲል ተቃውሟል።

መንግሥት በትግራይ ተፈጸመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመመርመር የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን በጥምረት የሚያደርጉትን ምርመራ በቀጣይ ወር እንደሚያጠናቀቁ አስታውሶ የውሳኔ ሐሳቡ ጊዜውን ያልጠበቀ ነው ብሏል።

ከዚህ በተጨማሪም የሕብረቱ የውሳኔ ሃሳብ በሁለቱ አካላት እየተከናወነ ያለውን የጋራ ምርመራ ተዓማኒነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል ብሏል።

የውሳኔ ሐሳቡን ይዘው የቀረቡት በተባባሩት መንግሥታት የአውሮፓ ሕብረት ልዑክ ኃላፊ አምባሳደር ሎቴ ኑደሰን "በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል እየሆነ ያለው ነገር አስደንጋጭ ነው" ስለማለታቸው ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት 47 አባል አገራት ያሉት ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ላይ የተላለፈውን የአውሮፓ ሕብረት የውሳኔ ሐሳብ የ20 አገራት ድጋፍን ሲያገኝ 14 አገራት ተቃውመውት 13 ደግሞ በድምጸ ታቅቦ አልፈውታል።

የዚህ ምክር ቤት አባል የሆነችው ኤርትራ የውሳኔ ሐሳቡን ተቃውማለች። ከኤርትራ በተጨማሪ የውሳኔ ሃሳቡን ከተቃወሙ አገራት መካከል ቻይና እና ቬንዙዌላ እንደሚገኙበት ሮይተርስ ዘግቧል።

ኢትዮጵያ የምክር ቤቱ አባል አገር ባትሆነም በአምባሳደር ማህሌት ኃይሉ ተወክላ የተገኘች ሲሆን፤ አምባሳደሯ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና በተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን የሚደረገውን ምርመራ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያሳድር በማሳሰብ የውሳሄ ሐሳቡን ተችተዋል።

መንግሥት ሕብረቱ ይህን የውሳኔ ሐሳብ "የማስተላለፍ የሕግም ሆነ የሞራል መሠረት የለውም" ያለ ሲሆን ኢትዮጵያ የአውሮፓ ሕብረት የውሳኔ ሐሳብን እንደማትቀበል አስታውቋል።

መንግሥት ጨምሮም ወንጀል ፈጽመው የሚገኙ አካላት ከሕግ ፊት ቀርበው ቅጣታቸውን እንደሚቀበሉ አስታውቆ፤ ኢትዮጵያ የአገር ውስጥም ሆነ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ግዴታዎቿን ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን አረጋግጣለሁ ብሏል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ።

ከስምንት ወራት በፊት በተቀሰቀሰው የትግራይ ክልል ጦርነት ውስጥ በርካታ ሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን የመብት ተሟጋቾችና የተለያዩ ተቋማት ሪፖርት ማድረጋቸው ይታወቃል።

ለዚህም በግጭቱ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ኃይሎች ግድያንና ጾታዊ ጥቃትን ጨምሮ የተለያዩ የመብት ጥሰቶችን መፈጸማቸው ተነግሯል።(BBC)

Report Page