ETHIOPIA

ETHIOPIA


የአዲስ አበባ ኤርፖርት ጉምሩክ የገቢ ዕቃዎች ክልከላና የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ምላሽ !

ባለፉት ሁለት ቀናት የግል መገልገያ እቃዎች መመሪያ ቁጥር 51/2010 አፈጻጸም መታገድን የሚያትት ደብዳቤና ለተመላላሽ ነጋዴዎች ደግሞ ምንም አይነት እቃ (አልባሳትና ጫማን ጨምሮ) ወደ ሀገር ይዞ መምጣት መከልከሉን የሚያሳስብ ማስታወቂያ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ሲሰራጫ ነበር።

በአዲስ አበባ ኤርፖርት ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ድንበኞች ትምህርት ቡድን አባል የሆኑትን አቶ ምትኩ አበባዉ ያናገረ ሲሆን እርሳቸዉም “ደብዳቤዎቹ ከኛ ነዉ የወጡት፤ ትክክለኛ ናቸዉ” ብለዋል።

የዚህ ክልከላ ምክንያትም ለንግድ የማይዉሉ የግል መገልገያ ዕቃዎችን ዝርዝር ለመወሰን የወጣዉን መመሪያ 51/2010ን በመጠቀም በተመላላሽ መንገደኞች ከቀረጥ ነጻ የሚገቡ ነገር ግን ለንግድ አላማ እየዋሉ የሚገኙ ዕቃዎች በህጋዊ ነጋዴዎች ላይ ጫና በመፍጠራቸዉ መሆኑን ተናግረዋል።

“አንድ መንገደኛ ሁሌ የሚመላለስ ከሆነ ያለቀረጥ ሁሌም እየተመላለሰ የሚያመጣ ከሆነ በህጋዊ መልኩ በኮንቴነር የሚያስጭኑና ግብር የሚከፍሉ ነጋዴዎችን ኪሳራ ዉስጥ የሚያስገባና ተጽዕኖ የሚያሳድር በመሆኑ ይህ ደብዳቤ ወጥቷል” ብለዋል። 

የግል መገልገያ ዕቃዎች መመሪያ ቁጥር 51/2010 ስራ ላይ መዋሉን ተከትሎ በተለይም አልባሳትና ጫማዎች በብዛት ወደ ሀገር ዉስጥ መግባት መጀመራቸዉና ከህጋዊ ነጋዴዎችም አቤቱታና ተቃዉሞ ሲቀርብ መቆየቱን አቶ ምትኩ አበባዉ አብራርተዋል።

“ንግድ ፍቃድ ያለዉ ሁሉ እየዘጋ በዛ እስከማምጣት ድርሷል። ምክንያቱም ቤት ተከራይቶ፤ ቀረጥ ከፍሎ፤ ግብር ከፍሎ አላዋጣዉም። ስለዚህ በመንገደኛ ያለቀረጥ እያስገባ ንግድ ፍቃዱን እያዘጋ በዛ እስከማምጣት የደረሰበት ሁኔታ ነዉ ያለዉ” ብለዋል። 

ስለዚህም በአዲሱ ዉሳኔ መሰረት “ማንኛዉም መንገደኛ ማንኛዉንም አልባሳትም ሆነ የንግድ ባህሪ ያለዉ ዕቃ ይዞ ከመጣ ቀረጥና ታክስ መክፈሉ እንደተጠበቀ ሆኖ በወንጀል ምርመራ ህግም እስከ ማስጠየቅ ድረስ የሚደርስ ነዉ” ብለዋል። 

ነገር ግን ከሀገር ዉጪ ከአንድ ወር በላይ የቆዩና ተመላላሽ ያልሆኑ የመጀመሪያ መንገደኞች፤ ቱሪስቶች እና ዲፕሎማቶች ፓስፖርታቸዉና ማህደራቸዉ ታይቶ የንግድ ባህሪ የሌለዉ ዕቃ የያዙ ከሆነ ለጊዜዉ በመመሪያ 51/2010 መሰረት የሚስተናገዱ መሆኑን አቶ ምትኩ አበባዉ ነግረዉናል። 

“ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ማንኛዉም መንገደኛ ከቀረጥ ነጻ ይዞ እንዲገባ የተፈቀዱ ዕቃዎችን (የተዘጋጁ አልባሳትና ጫማዎችን ጨምሮ) ተገቢዉን ቀረጥና ታክስ መክፈል እንደተጠበቀ ሆኖ ለንግድ እላማ የሚዉል ነዉ ተብሎ ከታመነ ለመጀመሪያ ጊዜ በቅጣት (እጥፍ ቀረጥና ታክስ) ይስተናገዳል። ለሁለተኛ ጊዜ ይዞ የሚመጣ ከሆነ ግን በወንጀል መጠየቅ ድረስ የሚያስደርስ ነዉ” ብለዋል። 

ጠቅልለዉ ወደ ሀገር ቤት የሚመለሱ መንገደኞች ጓዞቻቸዉን ይዘዉ ቢመጡም ሆነ በካርጎ ቢልኩ በመመሪያ 51/2010 የተፈቀደና ሲገለገሉበት የቆየ ዕቃ ከሆነ ከቀረጥ ነጻ ማስገባት ይችላሉ። ይሁን እንጂ በመመሪያዉ ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ የተፈቀዱ ቢሆኑም ዕቃዎቹ አዳዲስ እስከሆኑ ድረስ ቀረጥና ታክስ እንደሚከፈልባቸዉ ተነግሯል።

ምንጭ፦ ኢትዮጵያ ቼክ

@tikvahethiopia

Report Page