#ETH

#ETH


“አሜሪካ በሕዳሴው ግድብ ውይይት ላይ የአደራዳሪነት ሚና አልነበራትም”--- ኢንጂነር ስለሺ በቀለ

የውኃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ አሜሪካ በሕዳሴው ግድብ ውይይት ላይ የአደራዳሪነት ሚና እንዳልነበራት አስታውቀዋል። 

በኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን መካከል እየተካሄደ ያለውን ውይይት "በአሜሪካ እያደራደሪነት" እየተካሄደ ስለመሆኑ ግብፅ ብትገልፅም ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ ግን እውነታው ሌላ ነው ይላሉ። 

በሦስቱ ሀገራት መካከል እየተካሄደ ያለውን ውይይት አሜሪካ እና የዓለም ባንክ እንዲሳተፉበት የተደረገበት ምክንያት ምንድን ነው የሚል የቀረበላቸው ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ፣ ሦስቱ ሀገራት እ.አ.አ በ2015 በተፈራረሙት የመርህዎች መሠረት በየሀገራቱ መሪዎች የበላይ ጠባቂነት ቴክኒካዊ ውይይት እያካሄዱ መሆኑን ተናግረዋል። 

የመርህዎች መግለጫው የዓባይ ውኃን በፍትሐዊነት መጠቀም የሚቻልበትን፣ በሌሎች ሀገራት ላይ ተጨባጭ ጉዳት እንዳይደርስ እንዴት እንከላከል እንዲሁም ሁሉም ወገን ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሁኔታ እንዴት መፍጠር አለብን የሚሉትን ጨምሮ የተለያዩ 10 አንቀፆችን የያዘ መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል። 

ምናልባት በሕዳሴ ግድብ አሠራር ዙሪያ መግባባት ላይ የማይደረስባቸው ጉዳዮች ሲኖሩ አደራዳሪዎች እና ገላጋዮች እንዲገቡ እና ተደራዳሪዎች ጉዳዩን ለየሀገሮቻቸው መሪዎች እንዲያሳውቁ የመርህዎች መግለጫው ላይ ሰፍሯል ያሉት ሚኒስትሩ፣ እሁን እየተካሄደ ባለው መሰል ቴክኒካዊ ውይይት ላይ አደራዳሪ ወይም ሦስተኛ ወገን ማስገባት እንደማይቻል ገልጸዋል። 

ይሁን እንጂ የአሜሪካ መንግሥት ሦስቱ ሀገራት በጋራ እንዲወያዩ ግብዣ በማቅረቡ እና ከሀገራቱም አዎንታዊ መልስ በማግኘቱ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ በተደረገው ውይይቱ ላይ እንደ ታዛቢ ሊገኝ ችሏል ብለዋል። 

ግብፅ አሜሪካን እንደ አደራዳሪ አካል የወሰደችው መጀመሪያውኑ በጉዳዩ ላይ አደራዳሪ አካል እንዲገባ ካላት ፅኑ ፍላጎት ሊሆን እንደሚችል ነው የተናገሩት። 

ቴክኒካዊ ውይይቱ በሚፈለገው ደረጃ መሄድ ባለመቻሉ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ተገናኝቸው ጉዳዩን ወደ ፊት ማስኬድ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል። 

የተጀመረው ቴክኒካዊ ውይይቱ እስከ ፍፃሜው እንዲሄድ መመሪያ በመሰጠቱም በጉዳዩ ላይ አደራዳሪ አካል እንዲገባ አለመደረጉን እና አደራዳሪ አካል የሚያስፈልግበት ምክንያት አለመኖሩን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ የዓለም ባንክ እና የአሜሪካ መንግሥት እስካሁን ባለው ሂደት ከታዛቢነት በዘለለ ምንም ዓይነት የአደራዳሪነት ሚና አለመጫወታቸውን አስምረውበታል።

(EBC)

Report Page