#ETH

#ETH


‹‹የአማራ ሕዝብ በአማራነቱ ዋጋ የሚከፍልበት አንዳችም ምክንያት የለም፤ አማራ እንደ ሕዝብ ማንንም አልጨቆነም፤ አልበደለምም፡፡›› አቶ ጎሹ እንዳለማው

የአማራ ወጣቶች ማኅበር 5ኛ መደበኛ ጉባኤውን በባሕር ዳር እያካሄደ ነው። በጉባኤው በክብር እንግደነት የተገኙት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ልዩ አማካሪ አቶ ጎሹ እንዳላማው ለውጥና አብዮት የሚጀምረውና የሚመነጨው ከወጣቶች መሆኑን ተናግረዋል። ‹‹በኢትዮጵያ ከ1960ዎቹ ጀምሮ የተካሄዱት አብዮቶችና የለውጥ እንቅስቃሴዎች በወጣቶች ግንባር ቀደምነትና መስዋዕትነት የመጡ ናቸው›› ብለዋል አቶ ጎሹ። ሀገሪቱ አሁን ያለችበት የለውጥ ምዕራፍም እንዲመጣ ባለፉት ዓመታት የነበሩትን የሥርዓት ጉድለቶች ለማስተካከል ወጣቱ ከፍተኛ መሰዋዕት በመክፈል የለውጡ መሪ ተዋናይ እንደነበር ጠቅሰዋል። ‹‹ይህ ለውጥ እንዲመዘገብ የሀገሪቱና የአማራ ወጣቶች ያበረከታችሁት አስተዋጽኦ ሊያኮራችሁ ይገባል›› ብለዋል አቶ ጎሹ። አሁንም ቢሆን ፈተናዎች እንዳሉ የገለፁት አቶ ጎሹ ለውጡ የኢትዮጵያ መፃዒ እድል መልካም እንደሆነ የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያን መፃዒ እድል በማሳመር በኩል የወጣቶች ሚና ከፍተኛ እንደሆነም ነው የገለፁት። ባለፉት ዓመታት የተቀነቀነው የብሔር ፖለቲካ ሄዶ ሄዶ ዋልታ ረገጥና ፅንፈኛ ብሔርተኛ መሆኑንም አቶ ጎሹ አብራርተዋል፡፡ ወጣቱ ይህን ጉዳይ መልክ ለማስያዝ ዓይነተኛ ሚና መወጣት እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል። ዘረኝነት ለየትኛውም አካባቢ እንደማይጠቅምም አስገንዝበዋል። 

ወጣቱ ባለፉት ዘመናት የአማራ ሕዝብ ላይ የተዘራውን የውሸት ዘርና ትርክት በመለወጥ እውነተኛውን በማውጣት ሌሎች ስለአማራ ሕዝብ እውነታውን እንዲያውቁ በማድረግ በኩል ትልቅ ድርሻ መወጣት እንዳለበትም አሳስበዋል። ‹‹አማራነት ዋጋ የሚያስከፍልበት አንዳችም ምክንያት የለም›› ያሉት አማካሪው አማራ በተሳሰተ ትርክት እንደ በዳይና ጨቋኝ ተደርጎ ለሌሎች ሕዝቦች የፖለቲካ ልብወለድ እየተነገረ ሕዝቡ በጥርጣሬ እና በጥላቻ እንዲታይ መደረጉን አውስተዋል። 

‹‹በዚህ የተሳሰተ ትርክት ምክንያት የአማራ ሕዝብ ዋጋ ከፍሏል፤ አሁንም ዋጋ እየከፈለ ነው›› ብለዋል። ይህን ውሸት ማስቀረት የሚቻለው የአማራ ክልል ሕዝቦች ለኢትዮጵያ አንድነት ያደረጉትን ትግልና መሰዋዕትነት ኢትዮጵያ የምትባለውን ሀገር ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በመሆን እንደመሠረቱ እንዲረዱ በማድረግ እንደሆነም አስገንዝበዋል። ይህን ለማድረግ ወጣቱ ኃላፊነት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ኅብረ ብሔራዊት፣ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንድትፈጠር ከሌሎች ወንድሞቻችሁ ጋር መሥራት አለባችሁ፤ የአማራ ልጆች የአባቶቻችሁን ታሪክ በማወቅ ሌሎች እንዲያውቁት ለማድረግ መሥራት አለባችሁ›› ያሉት አማካሪው ታሪክ ማውራት ብቻ ሳይሆን ታሪክ መሥራትም እንዳለባቸው አሳስበዋል። 

ዘረኝነት ፋይዳ የሌለው እንደሆነ በመገንዘብ እርስ በእርስ በመዋደድ ታላቋን ኢትዮጵያ ለመገንባት ኃላፊነት መወጣት እንደሚገባም ተመላክቷል። 

‹‹የአማራ ሕዝብ እንደ ሕዝብ ኢትዮጵያን አልበደለም። የኢትዮጵያን ሕዝቦችም በጭቆና ሥርዓት ውስጥ አላኖረም›› ያሉት አቶ ጎሹ ጨቋኝ ገዥ መደብ ሊኖር እንደሚችል በማመላከት የአማራ ሕዝብ ማንንም የበደለ አለመሆኑን እንዲረዱና እንዲያስረዱም ከሌሎች ክልሎች የተወከሉ ወጣቶችን ጠይቀዋል። 

‹‹ሕዝብ እንደ ሕዝብ አይጣላም፤ የምናጣላቸው የፖለቲካ ነጋዴዎች ነን›› ብለዋል፡፡ ወጣቱ ዘመን ተሻጋሪ ሐሳብ በመያዝ የነገይቱን ኢትዮጵያ መልካም ማድረግ እንደሚኖርበትም አሳስበዋል፡ በዓለም ላይ ተደማጭነቷ ከፍ ያለች ሀገር እንደትኖር ከተፈለገ በአንድነት መቆም እንደሚገባም አስገንዝበዋል። 

ወጣቶቹ ከተበታተነ አደረጃጀት ወጥተው አንድ የጠነከረ አደረጃጀት መገንባት እንደሚገባቸው ያስገነዘቡት አማካሪው ተጠያቂነት ያለው መንግሥት እንዲኖር፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን መደራጀት ወሳኝ መሆኑን አሳስበዋል። የአማራ ክልል መንግሥትም አንድ የተጠናከረ የወጣት ማኅበር እንደሚፈልግና ይህን ለማድረግም ጥረት እንደሚያደርግ አማካሪው ተናግረዋል።

ከሌሎች ክልሎች የመጡ ወጣቶችም የአጋርነት መልዕክት አስተላልፈዋል። የአማራ ወጣቶች ማኅበር ሰኔ 1995 ዓ.ም ነው የተመሠረተው። 

(AMMA)

Report Page