#ETH

#ETH


መንግሥት ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ከገቡ በኋላ ለምደባ ይሰራበት የነበረውን ለተፈጥሮ ሳይንስ 70 በመቶ እንዲሁም ለማህበራዊ ሳይንስ 30 በመቶ የምደባ ስርዓት ለተፈጥሮ ሳይንስ 55 በመቶ እንዲሁም ለማህበራዊ ሳይንስ 45 በመቶ እንዲሆን መወሰኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬከተር አቶ ደቻሳ ግርማ ለኢትዮጵያ ሄራልድ እንደገለጹት ከዘንድሮው የትምህርት ዘመን ጀምሮ መንግሥት ለዓመታት ሲሰራበት የቆየውን የተፈጥሮ ሳይንስና ማህበራዊ ሳይንስ የተማሪዎች ድልድል ከ70/30 ወደ 55/45 ቀይሯል።

መንግሥት ቀደም ሲል ለዓመታት ሲሰራበት የቆየው የ70/30 የድልድል ስርዓት በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ የታሰበውን የሥራ ዕድል መፍጠር ባለመቻሉ፤በርካታ ተማሪዎች ያለፍላጎታቸው የተፈጥሮ ሳይንስን እንዲመርጡ የሚያስገድድና በዚህም ምክንያት ተማሪዎች ውጤታማ መሆን አለመቻላቸው፤የዩኒቨርስቲዎች የመቀበል አቅምን በማገናዘብና የሀገሪቱን የሰው ሀብት ፍላጎት ከግምት ውስጥ በማስገባትና በመሳሰሉት ምክንያቶች የምደባ ስርዓቱን መቀየር አስፈልጓል።

በዘንድሮ ትምህርት ዘመንም በሀገሪቱ በሚገኙ 45 ዩኒቨርሲቲዎች 142ሺህ 900 ተማሪዎች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ ሲሆን አዲስ በተዘረጋው የምደባ ስርዓትም ሁሉም ተማሪዎች የሚፈልጉትን የትምህርት መስክ መርጠው ለመማር ምቹ እድል እንደሚፈጠር አቶ ደቻሳ ተናግረዋል።

አሁን ሀገሪቱ ውስጥ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ከተፈጥሮ ሳይንስ መስክ ይልቅ ከማህበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ተመርቀው ለሚወጡ ዜጎች የተሻለ የሥራ ዕድል ማቅረብ የሚችሉ ተቋማት እንዳሉ ዳይሬክተሩ ገልጸው ይህንኑም ከግምት ውስጥ በማስገባትም 200 የሚደርሱ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከተፈጥሮ ሳይንስ ይልቅ ማኅበራዊ ሳይንስን መርጠው በማስተማር ላይ ይገኛሉ።

ድልድሉ ከ70/30 ወደ 55/45 መቀየሩም በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ የሥራ ዕድሎችን አሟጦ ለመጠቀምና ዜጎችም በፍላጎታቸው በተማሩበት መስክም ሥራ ለመያዝ የሚያስችላቸው እንደሚሆንም አቶ ደቻሳ አስረድተዋል።

(EPA)

Report Page