ETH

ETH

ቲክቫህ ኢትዮጲያ

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ከማደሪያ ክፍላቸው ውጪ የሚኖራቸው ቆይታ ከምሽቱ አራት ሰዓት እንዳያልፍ ይህም በተቆታጣሪዎች (ፕሮክተሮች) በየዕለቱ ክትትል እንዲደረግ መገለፁ ተሰምቷል።

እንዲሁም ዩኒቨርስቲዎቹ ተማሪዎች ከንጋት 12:00 ሠዓት በፊትና ከምሽት 1:00 ሰዓት በኋላ ከግቢ ውጪ እንዳይገኙ የተወሰነ ሲሆን፤ ይህንንም በግቢዎቹ ጥበቃ የፈረቃ ኃላፊዎች፣ የፌደራል እና የክልል ፀጥታ አካላት በዚህ ላይ መረጃ ተሰጥቷቸው እንዲያስፈፅሙ መወሰኑን በትናንትናው ዕለት የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቀወል።

በሚኒስቴሩ የኮሙኑኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ደቻሳ ጉርሙ ይህ ውሳኔ "ጊዜያዊ ነው" በማለት ችግር ያጋጠማቸው የትምህርት ተቋማት ሰላም ከተረጋጋ እንደሚነሳ ለቢቢሲ ተናግረዋል::

ሚኒስቴሩ ያስቀመጠው የሰዓት ገደብ ለጥንቃቄ የተደረገ ነው ያሉት አቶ ደቻሳ ጉርሙ፤ በደብረ ብርሃንና በወለጋ ዩኒቨርስቲዎች የተገደሉ ሁለት ተማሪዎች ከዩኒቨርስቲዎቹ ቅጽር ግቢ ውጪ መሆኑን ያስታውሳሉ።

ወለጋ ዩኒቨርስቲ ሞቶ የተገኘው ተማሪ የተገደለው አሳቻ ሰዓት መሆኑን በመጥቀስ፤ ጥፋተኛ ተብለው ከዩኒቨርስቲው የሚታገዱ ወይም የሚባረሩ ተማሪዎች ሌሎች አማራጮችን እንዳይጠቀሙ በሚቻለው አቅም ሁሉ ለተማሪዎቹ ሕይወት ሙሉ ጥንቃቄ ለማድረግ በሚል የተወሰነ መሆኑን ለቢቢሲ አብራርተዋል።

በዚህ ዓመት በዩኒቨርስቲ ውስጥ በተነሳ ግጭት ከሞቱት ተማሪዎች መካከል አብዛኞቹ በግቢው ውስጥ እንዲሁም በማደሪያ ክፍላቸው አካባቢ መሆኑን የተጠየቁት አቶ ደቻሳ "ግቢ ውስጥ ያሉ ችግሮችን ለማሻሻል የፀጥታውን ሁኔታ አጠናክረናል፤ ውጪ ደግሞ እንዳይከሰት የተሻለ ጥንቃቄ ለማድረግ ይህ ውሳኔ ተወስኗል" ሲሉ መልሰዋል።

በዩኒቨረስቲ ግቢ ውስጥ የተሻለ ጥበቃ አለ የሚሉት አቶ ደቻሳ የዩኒቨርስቲዎችን ሰላም ለማረጋገጥ በዩኒቨርስቲዎች በፌደራል ፖሊስ የሚካሄደው ጥበቃ ለውጥ እያመጣ ነው በማለት ለዚህም በአስረጅነት አዳዲስ ግጭቶች እየተነሱ አለመሆኑን ይጠቅሳሉ።

በአማራና በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎችን ሰላም ለማጠናከር የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የሚያስተባብረው የዩኒቨርስቲ የቦርድ አመራሮችና ባለስልጣናት ከአካባቢ ኃላፊዎችና የአገር ሽማግሌዎች የተካተቱበት ኮሚቴ ተዋቅሮ ሁሉንም የሚመለከታቸውን አካላት በማወያየት በዩኒቨርስቲዎች ዘላቂ ሰላም ማምጣት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን ሰላሙን ማስጠበቅና ጸጥታውን አስተማማኝ በማድረግ ተማሪዎችም ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ በሚል የፌደራል ፖሊስ ወደ ዩኒቨርስቲዎች መግባቱን አስታውሰው አሁን ያለው ሁኔታ ጥሩ መሆኑን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

"ግቢ ውስጥ ያለውን የፀጥታ ሂደት ስናጠናክር ከግቢ ውጪ እንዳይከሰትና የተኘው ሰላም እንዳይደፈርስ ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው" ብለዋል።

በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ በየትኛውም ደረጃ ያለ ግለሰብ የፀጥታ ችግርና ተጠያቂ የሚሆን ከሆነ ተጠያቂ እናደርጋለን ያሉት አቶ ደቻሳ፤ ሰላማዊ የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ አባላት ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ከዩኒቨርስቲ ለቅቀው ወደቀያቸው የሄዱ ተማሪዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ነበሩባቸው ተቋማት እንዲመለሱ እንፈልጋለን ሲሉ ገልፀዋል።

አክለውም ተማሪዎች ተመልሰው ትምህርታቸውን እንዲጀምሩ ጥሪ ቀርቧል ያሉት አቶ ደቻሳ፣ በሚኖሩበት አካባቢ በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ረብሻ ለማነሳሳት መሞከር ወንጀል ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የፀጥታ ችግር የታየባቸው 22 ዩኒቨርስቲዎች ተለይተው እየተሰራ ነው ያሉት አቶ ደቻሳ በእነዚህ ዩኒቨርስቲዎች የተወሰዱ የማስተካከያዎች እርምጃዎችን በተመከለተ የተጠቃለለ መረጃ እጃቸው ላይ እንደገባ እንደሚያስታውቁ ተናግረዋል።

በተያያዘ ዜናም በግጭቶች ምክንያት ተቋርጦ የነበረው ትምህርት በሁሉም የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ከሚቀጥለው ሳምንት አንስቶ ይጀመራል ተባሏል።

በሚኒስትሩ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ደቻሳ ጉርሙ ከግጭቶች ጋር ትምህርት ተቋርጦባቸው ከነበሩት ዩኒቨርስቲዎች አብዛኞቹ ትምህርት ጀምረዋል፤ ቀሪዎቹ ደግሞ ከሚቀጥለው ሳምንት አንስቶ ሙሉ በሙሉ ወደመደበኛ ትምህርት ይመለሳሉ ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

Report Page