#ETH

#ETH


በአዲስ አበባ በየቦታው የሚለጠፉ ህገወጥ የስራ ማስታወቂያዎች ላልተገባ እንግልትና ብዝበዛ እየዳረጋቸው መሆኑን ስራ ፈላጊ ወጣቶች ገለፁ።የሙያ ፈቃድ ሳይኖራቸው በዚህ ሂደት እየሰሩ ያሉ 57 ህገወጥ ኤጀንሲዎች እና 237 ህገወጥ ደላሎችን ማግኘቱን የአዲስ አበባ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለጸ፤ ፈር ለማስያዝም ጠንካራ የህግ ማዕቀፍ ያስፈልገኛል ሲልም ጠቅሷል።

 በአዲስ አበባ በተለይም አራት ኪሎና መገናኛ አከባቢ የማስታወቂያ ሰሌዳ ሲያነቡ ያገኘናቸው ስራ ፈላጊዎች እንደሚሉት፤ በርካታ ኤጀንሲዎች የስራ ልምድም ሆነ የትምህርት ደረጃ የማይጠይቁ ነገር ግን አማላይ ደመወዝ ተጠቅሶባቸው የሚለጠፉ ማስታወቂያዎች ስራ ፈላጊውን ላልተገባ እንግልትና ብዝበዛ እየዳረጉት ይገኛሉ።ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል ወጣት ምንዱ ገዛኸኝ እንደሚለው፤ በተለያዩ ስራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች አማላይ ማስታወቂዎች በየቦታው ይለጠፋሉ።

እነዚህ ማስታወቂዎች ደግሞ በርካታ የሰው ቁጥርና አጓጉ ደሞዝን ከመያዛቸው በዘለለ ለስራ ፈላጊው መፍትሄን ሳይሆን እንግልትና ብዝብዛን እያተረፉ ናቸው። ምክንያቱም ኤጀንሲዎቹ በምዝገባ፣ በኮሚሽንና በስልጠና ስም ገንዘብ ከመቀበላቸው ባለፈ፤ ስራው ባይገኝ እንኳን የወሰዱትን ገንዘብ አይመልሱም። ቢመልሱም የሚመልሱ ካሉም ከላዩ ላይ ቆርጠው ነው።

ወጣት ሳራ መኮንን በበኩሏ እንደምትለው፤ ኤጀንሲዎቹ በአማላይ ደሞዝ በርካታ የሰው ሃይል እንደሚፈለግ አድርገው የሚያወጧቸው ማስታወቂዎች ለእነርሱ ገንዘብን፤ ለስራ ፈላጊው ደግሞ እንግልትና ብዝበዛን አትርፈዋል። የሚለጥፏቸው ማስታወቂዎችም በቀለም ትምህርትና ያለስራ ልምድ ጭምር ከሶስት ሺህ እስከ አስር ሺህ ብር የሚደርስ ደመወዝ የሚጠቀስባቸው ሲሆን፤ ኤጀንሲዎቹም በእነዚህ አማላይ ማስታወቂያዎች ተስበው ከሚመዘገቡ ስራ ፈላጊዎች ገንዘብ ከሰበሰቡ በኋላ አድራሻው በውል ያልታወቀ ድርጅት ስም በመጥቀስ ስራ ፈላጊውን ወደዛ እንዲሄድ በማድረግ ያንገላታሉ። ስልክ ባለማንሳትና በመዝጋትም አድራሻቸውን ያጠፋሉ። በመሆኑም ይህ ተግባር በአግባቡ ሊፈተሽና ተገቢው እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል።

አዲስ ዘመን ጋዜጣ የሥራ ፈላጊዎችን ቅሬታ መነሻ አድርጎ ላቀረበው ጥያቄ ቢሮው በሰጠው ምላሽ፤ ችግሩን ለመከካለል እየተሰራ ቢሆንም ካለው ስፋት አንጻር አሁንም ሥራ ፈላጊው ለከፋ ብዝበዛ እየተዳረገ መሆኑን ተረድቷል። በዚህ ሂደትም የሙያ ፈቃድ ሳይኖራቸው እየሰሩ ያሉ 57 ኤጀንሲዎችና 237 ደላሎች መኖራቸው ተለይቷል። ሆኖም እነዚህ አማላይ ማስታወቂያዎች በየቦታው የሚለጠፉት የህግ ክፍተት በመኖሩ ስለሆነ ችግሩን ከመከላከል አኳያ ጠንካራ የህግ ማዕቀፍ ወጥቶ ሊተገበር ያስፈልጋል።

መረጃውን ያደረሱን በቢሮው የስራ ስምሪት ዳይሬክተር አቶ ጥላዬ አለማየሁ እንደተናገሩት፤ እነዚህ አማላይ ማስታወቂያዎች በተለያዩ ክፍለከተማዎች ይታያሉ። ማስታወቂያው ላይ በተጠቀሰው አድራሻ መሰረት ኤጀንሲዎቹን ለማግኘት ቦታው ሲኬድ እንደማይገኙና ለአጭር ጊዜ የምዝገባ ስራውን አከናውነው ከቦታው የሚጠፉ መሆኑን ተገንዝበዋል። በመሆኑም እነዚህን ህገወጥ አካላት የመለየትና መረጃ የማሰባሰብ ስራ እየተሰራ ሲሆን፤ ችግሩን ከመከላከል አኳያ በወረዳ፣ በክፍለ ከተማና በከተማ ደረጃ በፖሊስ፣ በደንብ ማስከበር፣ በንግድና በሠራተኛና ማህበራዊ ተቋማት መካከል በቅንጅት እየተንቀሳቀሱ ይገኛል።

እንደ አቶ ጥላዬ ገለጻ፤ በየቦታው የሚለጠፉ አማላይ ማስታወቂያዎችን ከመከላከል አኳያ እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል። ለምሳሌ፣ በ2011 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ እነዚህን ማስታወቂዎች የማንሳት ሥራ ተከናውኗል፤ በደረሰ ጥቆማና በቀረበ መረጃ መሰረትም የካ ክፍለ ከተማ ላይ ኢ.ኤች እና እፎይታ የተባሉ ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ላይ ከሥራ ፈላጊዎች የወሰዱት ብር ተይዞ እንዲመልሱ ተደርጓል። በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በተደረገ የማጣራት ሂደትም የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ሳይዙ የሚሰሩ 57 ህገወጥ ኤጀንሲዎች፤ እና በዚህ ሂደት የሚሳተፉ አሠሪና ሠራተኛን እናገናኛለን በማለት ያለፈቃድ የሚሰሩ 237 ያህል ህገወጥ ደላሎች መኖራቸው ተለይቷል። ግኝቱም ህገወጦች እየበዙ መሆናቸውን አመላካች ነው።

ሆኖም በዚህ መልኩ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የሚሰሩ ኤጀንሲዎችን ለመቆጣጠርና ተጠያቂ ለማድረግ የሚደረገው ሥራ የሁሉንም ተሳትፎ የሚጠይቅ እንደመሆኑ ህብረተሰቡ ግንዛቤ ይዞ እነዚህን አካላት በመረጃ ላይ ተመስርቶ የመጠቆምና የማጋለጥ ሃላፊነቱን መወጣት አለበት ብለዋል። ደንብ ማስከበር፣ ፖሊስ፣ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ ንግድና ኢንዱስትሪ እና ዐቃቤ ሕግ ጠንካራ ቅንጅታዊ አሰራር ሊኖራቸው እንደሚገባና የኤጀንሲዎች ፈቃድ አሰጣጥ ሂደትም ጠንካራ ቅድመ ሆኔታዎችና መስፈርቶች ሊቀመጡለት እንደሚገባም አቶ ጥላዬ ጠቁመዋል።

ከዚህ ጎን ለጎንም አስፈላጊ የህግ ማእቀፎች ወጥተው በስራ ላይ ሊውሉ ይገባል የሚሉት አቶ ጥላዬ ይህ ሲሆን ቢሮው አስፈላጊውን እርምጃ ይወስዳል፤ ከፖሊስና የፍትህ አካላት ጋር ተቀናጅቶም ህጋዊ እርምጃን ለማስወሰድ እድል ያገኛል ብለዋል።

ኤጀንሲዎች በምዝገባ፣ በኮሚሽንና በስልጠና ስም ክፍያ እየጠየቁና ያልተገባ ጥቅም ማግኛ እያደረጉት ስለመሆኑ የሚነሳው ቅሬታ እውነት እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ጥላዬ፤ የኮሚሽን አከፋፈልን በተመለከተ የትኛውም ኤጀንሲ አንድን ሠራተኛ ከአሠሪው ጋር ሲያገናኝ ኮሚሽን ማግኘት ያለበት ከአሠሪው መሆን እንዳለበት በአዋጁ በግልጽ መቀመጡን ይገልጻሉ። ሆኖም ይህ ተግባራዊ እየተደረገ ካለመሆኑም በላይ፣ በኤጀንሲዎች በስልጠና ስም የሚፈጸም ክፍያ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል።

ይሄን ችግር መቅረፍ ካልተቻለም አሁን እንደሚታየው ሥራ ፈላጊዎች ለከፍተኛ የገንዘብ ብዛበዛ፣ እንግልትና የስነልቡና ጫና መዳረጋቸው፤ ከተማዋም በልጥፍጣፊ ወረቀቶች መቆሸሿ የሚቀጥል መሆኑን ቢሮው ስለተረዳ ትልመ ጥናት(ፕሮፖዛል) እያዘጋጀ ሲሆን፤ ማስታወቂዎች በተወሰኑ ቦታዎች ላይ ብቻ እንዲለጠፉ የሚያደርጉ መመሪያና አዋጆች እንዲወጡ የሚል ምክረ ሀሳብም ቀርቧል። እስከዚያው ግን ህገወጦችን በመለየት በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ 1156/2011 መሰረት እርምጃ እንዲወሰድ እየሰራ ይገኛል። በቅርቡም በዚህ ተግባር ላይ ተሰማርተው የተገኙ በመኖራቸው ጉዳዩ ለፍትህ አካላት እንዲተላለፍ ሆኗል። ሆኖም የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ትልቁ ሥራ ሊሆን ይገባል።

በአዲስ አበባ 392 የሙያ ፈቃድ የተሰጣቸው ሠራተኛና አሠሪ አገናኝ ኤጀንሲዎች ያሉ ሲሆን፤ ከነዚህ ውስጥ 120ዎቹ ስራን ወስደው የሚያሰሩ፤ ቀሪዎቹ ደግሞ አሠሪና ሠራተኛን የሚያገናኙ ኤጀንሲዎች መሆናቸው ታውቋል።

አዲስ ዘመን ታህሳስ 17/2012


Report Page