#ETH

#ETH


የመከላከያ ሰራዊታችን የፈለገ የሚንደው የእንቧይ ካብ አይደለም!

ሰሞኑን አንዳንድ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመከላከያ ሰራዊታችን ውስጥ መከፋፈል እንደተፈጠረ በማስመሰል መረጃዎችን ሲያሰራጩ ይስተዋላሉ፡፡ በተለይ ደግሞ የሰራዊታችን ከፍተኛ መኮንኖች ስለ ብልጽግና ፓርቲ ፕሮግራም እንዲወያዩ መገደዳቸውንና አልወያይም የሚል ካለም ከተቋሙ እንደሚሰናበት ስለመወሰኑ ከፍተኛ የተቋማችን አመራርን ፎቶ በመለጠፍና ስም በመጥቀስ ጭምር የስም ማጥፋት ዘመቻቸውን ተያይዘውታል፡፡

ሃቁ ግን ሌላ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ተቋማችን መከላከያ በማካሄድ ላይ ከሚገኘው ሪፎርም መካከል ተግባሩን ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ወገንተኝነት በጸዳ መልኩ የሚያከናውን ሰራዊትን መገንባት ነው፡፡ 

ለዚህ ደግሞ ቀደም ሲል ይሰራበት የነበረውን የነአዲስ ራዕይ መጽሄት ውይይትም ይሁን የአብዮታዊ ዲሞክራሲ የሰራዊት የግንባታ አቅጣጫን በመተው ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ወገንተኝነት ነጻ የሆነ ሰራዊት መገንባት መቻል በሪፎርሙ ከተመዘገቡት ድሎች መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡ የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊታችን የየትኛውም ፖለቲካ ፓርቲ ደጋፊም ሆነ ተቃዋሚ እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ በተለይ ደግሞ የተቋሙን ስምና ዝና ለማጠልሸት የሚደረገው ሙከራ መላው ሰራዊታችን የሚያውቀውን እውነታ ‘እኔ አውቅልህ‘ ከሚል የአዞ እንባ አይነት የዘለለና ህዝብን ለማሳሳት ከመሞከር ባሻገር ምንም ሚና አይኖረውም፡፡ ስለዚህ በሰራዊታችን ውስጥ ይህ አይነቱ የመከፋፈልም ይሁን የማንኛውም ፓርቲ ፕሮግራም ውይይት የማካሄድ ድርጊት ፈጽሞ እንደሌለና ወደፊትም እንደማይኖር በእርግጠኝነት እንገልጻለን፡፡

ታዲያ “ ከብት ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ” እንዲሉ በመመሪያና ደንብ የሚመራና የማንኛውንም ፖለቲካ ፓርቲ ፕሮግራም መወያየት የሚከለክል ህግ ባለበት ተቋማችን ውስጥ እንዲወያዩ ተገደዱ ብሎ የሃሰት መረጃ የማሰራጨት ጥረቱ እኩይ ተግባርና ራሱን የቻለ ሌላ አላማ ያለው መሆኑን ከማንም የተሰወረ አይሆንም ፡፡ 

ለዚህም የሚስጥሩ መጋረጃ ሲገለጥ በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ዓላማው አንድና አንድ ነው፡፡እርሱም የመከላከያ ሰራዊታችንን ጠንካራ አንድነት የመሸርሸር ከንቱ ጥረትና ባዶ ቅዠት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ይህ ከንቱና ርካሽ ዓላማ ግን መቼም ሊሳካ አይችልም፡፡ ምክንያቱም የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊታችን በጽኑ ህዝባዊ መሰረት ላይ የተገነባ፣ህገ መንግስታዊ ተልዕኮውን በታማኝነት፣በቅንነትና በፍጹም ጀግንነት የሚፈጽም ውስጣዊ አንድነቱ እንደ ብረት የጠነከረ ሰራዊት እንጂ እነዚህ ወገኖች እንደሚያስቡት በፌስ ቡክ የሚገነባና በመሰረተ ቢስ የፌስ ቡክ መረጃዎች የሚናድ የእንቧይ ካብ አይደለምና፡፡

 በመሆኑም እነዚህ ወገኖች ሊያውቁት የሚገባው ነገር ቢኖር የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት እንኳንስ ስላሉት ጉዳይ ሃሰትነት እውነታውን እያወቀ ቀርቶ የውሸት ሱሰኞቹ ስለሚሉት ነገር ምንም መረጃ ባይኖረው እንኳን መቼምና በማንኛውም ሁኔታ የፍላጎታቸው ማራገፊያ ሊሆን እንደማይችል ነው፡፡

(የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት)

Report Page