ETH

ETH

ቲክቫህ ኢትዮጲያ

የመጀመሪያ ዓመት የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ለማስተማር በተዘጋጀው የአፍሪካ ቀንድና የኢትዮጵያ ታሪክ መማሪያ ሞጁል ግምገማ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡

በዝግጅቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት ተማሪዎቻችን የአገራቸውን ታሪክ መማር እንዳይችሉ እንደአገር የታየው ዳተኝነት ውሎ አድሮ ትርክቶች የታሪክን ቦታ ይዘው አለመግባባቶችና ጥርጣሬዎች እንዲያድጉ እድል ፈጥሯል፡፡ 

ታሪክ ስላለፈው ነው፣ ስለሰው፣ ማህበረሰብ፣ ብሔር፣ ህዝብ፣  በአንድ ወቅት በተወሰነ ቦታ ስለተፈፀመ ጉዳይ አንደመሆኑ አስተማሪውን ታሪክ ነቅሶ ማውጣት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ 

ኢትዮጵያ ታሪክ ሞልቶ የሚፈስባት አይነት አገር ናት  ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ታሪክ ስለባለፈው ቢሆንም ከዚያ ተምረን ዛሬ በአግባቡ ለመረዳትና ቀጣዩን ለመተለም ካልጠቀመ ታሪክ ማወቃችንም ይሁን መማራችን ጥያቄ ያስነሳል ብለዋል፡፡

አክለውም የየትኛውም አገር ታሪክ ብዙ መልካም፣ ውስን መልካም  እንዲሁም ጥቂት የታሪኩ አካል ባይሆን የሚመረጥ ጉዳዮችን የያዘ ነው ብለው ይህን መረዳት፣ በሚዛኑ መያዝና በልኩ ማስተናገድ ታሪክን ተጠቅመን ለማሳካት ለምንፈልገው ግብ መሰረት ይጥላል ብለዋል፡፡

በያዝነውና በጨበጥነው እውቀት ሌላ ቁስል መፍጠር ወይም ቁስሉን በመነካካት ሌላ ቁርሾ የሚሻ የለም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ይልቅስ  የትናንቱን ጉዳት በእርቅና በይቅርታ ተሻግሮ ወደ ብልፅግና የሚደረገው ጉዞ ማፋጠን ይገባል፡፡ ለዚህም ቅራኔና ጥርጣሬ በቀላሉ የሚፈጥሩ  ይዘቶችን በየትኛውም መመዘኛና ምክንያት የሞጁሉ አካል አይሆንም ብለዋል።

በተጨማሪም የታሪክ ማስተማሪያ መነሻ ሞጁሉን ለመገምገም የተዘጋጁት የታሪክ መምህራንና ተመራማሪዎች የኢትዮጵያን አንድነት የህዝባችንን አብሮነትና የግንኙነተቻው አምድ የሆኑትን ባህልና እምነት ተገቢውን ክብር በሚሰጥ ደረጃና ቋንቋ መፃፉን ማረጋገጥ ግዴታ እንዳለባችውም አስግንዝበዋል፡፡

አክለውም ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የታሪክ ሞጁሉ ላይ የተሰጡትን አስተያየቶች ይዘው የተሰባሰቡት ምሁራን ሞጁሉ ተጠናቅቆ ለማስተማሪያት ዝግጁ እስከሚሆን ድረስ በከፍተኛ ኃላፊነት፣ የዜግነት ግዴታና የሙያ ክብር ስሜት እንዲንቀሳቀሱ አደራ ብለዋል፡፡ 

በሞጁል ግምገማው ከሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ የታሪክ መምህራን፣ የታሪክ ተመራማሪዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት እየተሳተፉ ሲሆን በዩኒቨርስቲዎቻቸው ተወያይተው ያመጧቸው አስተያየቶች ላይ እስከ ነገ ድረስ በመወያየት ቅዳሜ የጋራ ያደረጉትን ሞጁል ያጸድቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

Report Page