ETH

ETH

ቲክቫህ ኢትዮጲያ

መረጃውን የተጠቀሙበት ግጭት ሳይከሰት መከላከላቸውን አመልክቷል

በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ብሔርን፣ ሃይማኖትንና የአስተዳደር ወሰንን መሠረት ያደረጉ፣ እንዲሁም በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚስተዋሉ ግጭቶች ሊከሰቱ እንደሚችሉ የሚጠቁሙ መረጃዎችን ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት አስቀድሞ መስጠቱን፣ የብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትን ስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሰኞ ታኅሳስ 13 ቀን 2012 ዓ.ም. በተቋሙ ተገኝቶ የገመገመ ሲሆን፣ በዚሁ ወቅት የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ደመላሽ ገብረ ሚካኤል የሥራ አፈጻጸሙን የተመለከተ መግለጫ ጥሪ ለተደረገላቸው ጋዜጠኞች ሰጥተዋል፡፡

“ብሔርን፣ ሃይማኖትን፣ እንዲሁም የአስተዳደር ወሰንን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች፣ እንዲሁም በዩኒቨርሲቲዎች እየተከሰቱ መሆኑን ተከትሎ ማኅበረሰቡ ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የት ነው ያለው የሚል ትችት አዘል ጥያቄ እንዲያነሳ እያደረገው ነው፤” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ተቋማቸው ግን ችግሮቹ ከመከሰታቸው አስቀድሞ ግጭቶቹ ሊከሰቱ እንደሚችሉ የሚጠቁሙ መረጃዎችን ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ማድረሱንና አሁንም እያደረሰ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

“እኛ ቀድመን መረጃዎችን ሰጥተናል፤” ያሉት አቶ ደመላሽ፣ “መረጃውን ፈጥኖ የተጠቀመበት አስቀድሞ ውጤት አግኝቶበታል፣ የዘገየው ደግሞ ችግሮቹ ተከስተውበታል፤” ብለዋል፡፡ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎቱ አስቀድሞ ያቀረበው መረጃ ሰፊ ጥናትን መሠረት አድርጎ የተጠናቀረ በመሆኑ፣ ችግሮቹ ከተከሰቱ በኋላም ድርጊት ፈጻሚዎቹን ለይቶ ለሕግ ለማቅረብ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲዎች የሚከሰቱ ግጭቶችን በተመለከተ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ጉዳይ ከሚከታተሉ ሚኒስትሮች ጋር አስቀድሞ ሲሠራ እንደነበር፣ አሁንም ችግሮቹን ለመፍታት በልዩ ትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ብሔር ተኮርና ከአስተዳደር ወሰን ጋር የተያያዙ ግጭቶችን በተመለከተም ለክልል መንግሥታት አስቀድሞ መረጃዎች እንደተሰጡ፣ በአሁኑ ወቅትም በልዩ ትኩረት ከእነዚሁ የመንግሥት አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡ የመከላከያ ሠራዊቱን ጨምሮ ሁሉንም የሕግ አስከባሪና የፀጥታ ተቋማት በማሳተፍ ብሔራዊ የፀጥታና ደኅንነት ጥናት አዘጋጅቶ ባለፉት ስድስት ወራት ተግባራዊ እደረገ እንዲገኝ ያወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በቀጣይ ተግባራዊ የሚደረግ የብሔራዊ የደኅንነት ሥጋት ትንተናና ምደባ አሠራር ጥናት መከናወኑንም ገልጸዋል፡፡

ከእንግሊዝ ከመጡ የደኅንነት ባለሙያዎች ጋር በመተባበር የተዘጋጀው ይህ ጥናት በቅርቡ ለብሔራዊ የፀጥታና ደኅንነት ምክር ቤት ቀርቦ ሲፀደቅ ተግባራዊ እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡ ይህ ሰነድ የአገሪቱን የፀጥታና ደኅንነት ሥጋቶች በየጊዜው በመለየት፣ የሥጋት ደረጃዎችን የያዘ መረጃ በየጊዜው ለኅብረተሰቡ ይፋ የሚደረግበትን አሠራር የሚያበጅ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኝ አሠራር መሆኑን ያመለከቱት አቶ ደመላሽ፣ አገሮች የፀጥታና ደኅንነት ሥጋቶችን ቀይ፣ ቢጫና አረንጓዴ ብለው በቀለማት ደረጃ በመስጠት ለሕዝባቸው ይፋ በማድረግ ቀድመው መከላከል እንዳስቻላቸው ጠቁመዋል፡፡ ይህንን አሠራር ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መንገድ በኢትዮጵያ ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚያስችልና በዚህም የአገሪቱ የፀጥታ ደረጃ ምን ላይ እንደሚገኝ፣ የተደቀኑ ሥጋቶች ዓይነትና ደረጃን ቀድሞ ለኅብረተሰቡ በማሳወቅ ማኅበረሰቡ ራሱን ለመከላከል እንዲችል፣ እንዲሁም ሥጋቱ ከተከሰተም ምን ማድረግ እንደሚገባ የሚያስገነዝብ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት ከተከናወኑ ተግባራት መካከል ዓለም አቀፍ ዕውቅናን ለተቋሙ ያስገኘ ነው ያሉትንም አቶ ደመላሽ ገልጸዋል፡፡ ይኸውም በ2012 ዓ.ም. አዲስ ዓመት መቀበያ አካባቢ፣ ዓለም አቀፍ የሽብር ቡድኖች በአዲስ አበባና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሊያደርሱት የነበረውን የሽብር ተግባር ተቋሙ ማምከን የቻለበት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

የሽብር ተግባር ዕቅዱን ለማክሸፍ ጎረቤት አገር ሶማሌላንድን የሸፈነ ኦፕሬሽን መከናወኑን፣ እንዲሁም ከ16 አገሮች አቻ ተቋማት መረጃ ልውውጥ ታግዞ መፈጸሙን አመልክተዋል፡፡ በዚህም ሥራ በሶማሌላንድ ሐርጌሳ የሚገኝ የአሸባሪው አልሸባብ ከፍተኛ የፈንጂ ባለሙያዎች ቡድን በቁጥጥር ሥር እንዲውል መደረጉን፣ የሽብር ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ 17 ቡድኖችም በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ያስቻለ ተግባር በተቋሙ መፈጸሙን ገልጸዋል፡፡

በቁጥጥር ሥር የዋሉት ቡድኖች ጥቃት ለማድረስ ያቀዱባቸውን አካባቢዎች የሚያመለክቱ ፎቶግራፎችና ጥቃቱን ለመፈጸም የሚያስችሏቸው ቁሳቁሶችም መያዛቸውን አስረድተዋል፡፡ ጥቃቱን ሊፈጸምባቸው ከነበሩ አካባቢዎች ዋነኛው አዲስ አበባ እንደነበርና በድሬዳዋ፣ በጅግጅጋና በሞያሌ የተለያዩ አካባቢዎች ጥቃቱን ለማድረስ ታቅዶ እንደነበርም አመልክተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሊቃጣ ታቅዶ ከነበረው የሽብር ጥቃት ጋር የተያያዙ መረጃዎችን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አቻ ለሆኑ 16 አገሮች መላኩን ያስታወቁት አቶ ደመላሽ፣ ይህንን መረጃ መሠረት በማድረግ የጣሊያን መንግሥት 14 የአልሸባብ ሽብር ቡድን አባላትን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን፣ በተመሳሳይም አሜሪካ፣ ፈረንሣይና ህንድ መረጃውን መሠረት አድርገው የመለየት ሥራ በማከናወን ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በስኬት አጠናቀቅኩት ባለው በዚህ የፀረ ሽብር ኦፕሬሽን የተደነቁት ሲአይኤ በሚል ምህፃረ ቃል የሚታወቀው የአሜሪካ መንግሥት የመረጃ ተቋም ዋና ዳይሬክተር፣ “ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች ምሳሌ የሚሆን ኦፕሬሽን ነው፤” ሲሉ የአድናቆትና የምሥጋና ደብዳቤ መላካቸውን አቶ ደመላሽ ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት ከተከናወኑ ተግባራት አንዱ በስኬት ባይጠናቀቅ ኖሮ፣ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የማድረስ አቅም የነበረው ተመሳስሎ የተሠራ ሐሰተኛ (ፎርጅድ) ዶላርና ብር አትሞ በገበያ ውስጥ የማሠራጨት ሙከራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ይህንን ተግባር ለመፈጸም ወደ ኢትዮጵያ በመግባት እንቅስቃሴ ላይ የነበሩ ስምንት የካሜሩን ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች ሐሰተኛ የገንዘብ ቅጠሎቹን ለማተም ጥቅም ላይ ሊያውሉት ከነበረው ማተሚያ ማሽን ጋር በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ከፍተኛ የሙስና ወንጀሎችን የተመለከተ ሰፊ ጥናትና መረጃ የማሰባሰብ ተግባር ተቋሙ ማጠናቀቁን የገለጹት ኃላፊው፣ በዚህ ጥናት መረጃ ላይ መንግሥት በቀጣዮቹ ጊዜያት ውሳኔ ሲያሳልፍ የሚመለከተው ሕግ አስከባሪ አካል ወደ ወንጀል ምርመራ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ባለፉት ስድስት ወራት በአፋር የጨው ምርትና ንግድ ሒደት ላይ ተቋሙ ያካሄደውን ሰፊ ጥናትና መረጃ መሠረት በማድረግ፣ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተጠርጣሪዎችን ለሕግ ማቅረቡን አስታውሰዋል፡፡ በግብር ማጭበርበር ተግባር ላይ ባከናወነው ጥናትም ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ተጠያቂነትን የሚያስከትል መረጃ ለገቢዎች ሚኒስቴር ማቅረቡን ጠቁመዋል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከፍተኛ ተቋማዊ ሪፎርም ላይ እንደሚገኝ የተናገሩት አቶ ደመላሽ፣ ተቋሙን በድጋሚ ለማቋቋም የሕግ ማዕቀፍ ተሰናድቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መላኩን ገልጸዋል፡፡

የማቋቋሚያ አዋጁ ሲፀድቅ የተቋሙ መጠሪያ ስያሜ ብሔራዊ የመረጃ ማዕከል (ኤንአይሲ) እንደሚሆን፣ ከፖለቲካም ሆነ ከማንኛውም ዓይነት ወገንተኝነት የፀዳ ሙያዊ ተግባሩን ብቻ የሚወጣ ተቋም እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ ሪፖርተር የተመለከተው ይህ ተቋም እጅግ ዘመናዊ ሕንፃ ሲኖረው፣ በአረንጓዴ ተክሎች የተዋበ እንዲሁም ፀጥታ የተሞላበት ግቢ ሆኖ አግኝቶታል፡፡

በሕንፃው ውስጥ ጥቂት ሰዎች ብቻ ፕሮቶኮል በጠበቀ አለባበስ ሲንቀሳቀሱ የተስተዋሉ ሲሆን፣ ከተወሰኑ የመሰብሰቢያ አዳራሾች ውጪ መጎብኘትም ሆነ ፎቶግራፍ ማንሳት የተከለከለ ነው፡፡ ዋና ዳይሬክተሩንም ፎቶ ማንሳት የሚቻለው ሲፈቀድና ሚዲያዎች እንዲከታተሉት ከተፈቀደው ሁነት ጋር ብቻ የተገናኘ እንደሆነ ነው፡፡

በአገሪቱ እየተስተዋሉ ያሉ ግጭቶችን በተመለከተ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለሚመለከታቸው አካላት ቀድሞ እንደቀረበ የተናገራቸውን መረጃዎች ባለመጠቀም፣ ችግሮቹ እንዲከሰቱና ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉ ተቋማትን በመለየት ተጠያቂነትና ክትትል እንዲደረግባቸው በፓርላማው ሕጋዊ አሠራር መሠረት ለአፈ ጉባዔው እንደሚያቀርቡ የፓርላማው የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በጥቅሉ ግን ባዩት ነገር መደሰታቸውን፣ በተለይም ሕዝብ የሚቀርበውና የሚያግዘው ተቋም ለማድረግ እየተካሄዱ ባሉ ተግባራት መደነቃቸውን አቶ ተስፋዬ አክለዋል፡፡

Report Page