#ETH

#ETH


መረጃ ስለ ኤክሳይዝ ታክስ!

ኤክሳይዝ ታክስ የቅንጦት ዕቃዎች ሆነው ዋጋቸው ጨመረም አልጨመረ መሠረታዊ በመሆናቸው ምክንያት የገበያ ተፈላጊነታቸው በማይቀንስ ዕቃዎች ላይ እንዲሁም የኅብረተሰቡን ጤና የሚጎዱ እና ማህበራዊ ችግሮችን የሚያስከትሉ ዕቃዎችን አጠቃቀም ለመቀነስ ሲባል የሚጣል ነው፡፡

በሥራ ላይ የቆየው የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ቁጥር 307/2002 አዋጅ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ እና ከሌሎች ሀገራት ልምድ አኳያ መሻሻል ስለሚገባው ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡት እና ሀገር ውስጥ በሚመረቱት በተለያዩ ምርቶች ላይ ለውጥ ለማድረግ ረቂቅ ወጥቶ ታኅሣሥ 7/2012 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከቀረበ በኋላ ለዝርዝር እይታ ወደ ፋይናንስና ገቢ ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡

ረቂቅ አዋጁ የተዘጋጀው በገንዘብ ሚኒስቴር ሲሆን ቀጣይ የኮሚቴው ምርመራ እና የሕዝብ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ፀድቆ ወደ ገቢዎች ሚኒስቴር የሚመጣው ለተግባር ብቻ ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ የታክሱን ረቂቅ በማዘጋጀት የመወሰን ስልጣን ላለው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚያቀርበውና የሚያስወስነው የገንዘብ ሚኒስቴር ነው ማለት ነው፡፡

ረቂቅ አዋጁ ካሰፈራቸው በርካታ የማሻሻያ አይነቶች በተጨማሪ አዳዲስ ምርቶችም ወደ ኤክሳይዝ ታክስ ውስጥ የገቡ ሲሆን በርካታ ምርቶችን ያካተተ ለውጥ ቢኖረውም በዋናነት እያነጋገረ ያለው የመኪና ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ በፊት በነበረው አዋጅ መኪኖች ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ ይከፈል የነበረው ኤክሳይዝ ታክስ በአዋጅ ቁጥር 307/2002 መሠረት እንደ ሲሲያቸው መጠን ነበር፡፡ ይኸውም፤ እስከ 1ሺ300 ሲሲ 30 በመቶ፣ ከ1ሺ 301 እስከ 1ሺ 800 ሲሲ 60 በመቶ እና ከ1ሺ801 በላይ 100 በመቶ ነበር፡፡ ይህ አመዳደብ ለአዳዲስም፣ ላገለገሉትም ተሽከርካሪዎች ተመሳሳይ ስለነበር በርካታ አሮጌ መኪኖች ወደ ሀገር እየገቡ ችግር አስከትለው ነበር፡፡

ችግሮቹም፤ አሁን እየተበራከተ ለመጣው የትራፊክ አደጋ አንድ መንስኤ መሆን፣ ለአየር ብክለት አስተዋጽኦ ማድረግ፣ ከፍተኛ የነዳጅ ፍጆታን መጠቀም፣ በተደጋጋሚ ቴክኒክ ብልሽት መለዋወጫን መጠቀም እና ሀገር ውስጥ በሚመረቱት ላይ የገበያ ጫና ማሳደር ናቸው፡፡

ለዚህ ረቂቅ አዋጅ መነሻ የሆነው ጥናት እንደሚያመከለክተው በኢኮኖሚ ዕድገታቸው ወደ ኋላ የቀሩ አገሮች ተሽከርካሪዎችን በአገር ውስጥ የሚያመርቱ ሳይሆኑ ከውጪ የሚያስገቡ ናቸው፡፡ ከውጪ ከሚያስገቧቸው ተሽከርካሪዎች ውስጥ ደግሞ አብዛኞቹ ያገለገሉ ናቸው፡፡ ዲሏት (Deloitte) የተባለው ኩባንያ በኢትዮጵያ፣ በኬንያ እና በናይጄሪያ ባደረገው ጥናት፤ ወደ እነዚህ ሀገራት ከሚገቡ አስር ተሽከርካሪዎች ውስጥ ስምንቱ ያገለገሉ ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2017 የሀገራችን ጉምሩክ መረጃ መሰረት ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ከሚገቡ ተሽከርካሪዎች ውስጥ 88 በመቶዎቹ ያገለገሉ ናቸው፡፡

በዓለም ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ወደ 1.2 ቢሊዮን የሚጠጉ ተሽከርካሪዎች እንዳሉ ይገመታል፡፡ ከነዚህ ተሽከሪካሪዎች አብዛኞቹ በአሮጌነት ተገዝተው በማደግ ላይ ወደሚገኙ ሀገሮች የገቡ ናቸው፡፡ በብዙ ሀገሮች የትራንስፖርት ዘርፍ በከተሞች ለሚከሰተው የአየር ብክለት ዋና ምክንያት ሲሆን በአንዳንዳንድ ከተሞች እስከ 80 በመቶ ለሚሆነው የአየር ብክለት አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ ለአየር ብክለቱ ዋነኛ ምንጭ ደግሞ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ናቸው፡፡

ከሁሉም በላይ የሚያስጨንቀው ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ከአዲሶቹ ይልቅ ወደ አካባቢ አየር ከፍተኛ መጠን ያለው ብክለት ሲለቁ ህይወት ባላቸው ፍጡራን ላይ የሚስከትሉት ጉዳት ነው፡፡ ለአብነትም፡-

 የመተንፈሻ አካል በሽታን (እንደ አስምና ብሮንካይትስን) ያባብሳል፣ ተክሎችን ይጎዳል፤

 የአሲድ ዝናብ ያስከትላል (ሰልፈር ዳይኦክሳይድ)፤

 ከፍተኛ ልቀት ባለው ጭስ የሚወጣው ካርቦንሞኖኦክሳይድ በደም ውስጥ የኦክሲጅን ዝውውርን በማወክ ለከፍተኛ ጉዳት፤ በተለይ የልብ ሕመም ላለበት ሰው የከፋ ጉዳት ያስከትላል፤

 በቀጥታ የሰውን ጤንነት ባያውክም የግሪን ሐውስ ኢፊክት በመፍጠር ለአካባቢ አየር መሞቅ እና ለአየር ንብረት መለወጥ ምክንያት ነው (ካርቦንዳይኦክሳይድ)፤

 በታችኛው የከባቢ አየር ክፍል ኦዞን እንዲፈጠር ምክንያት በመሆን የዐይን መቆጥቆጥ እና የመተንፈስ ችግር ይፈጥራል (ናይትሮጂን ኦክሳይድ)፤

 በጣም ደቃቅ የሆኑ ብናኞች ወደ ሳንባ ውስጥ ዘልቀው ሳንባን በመጉዳት የመተንፈሻ አካል ሕመምን ያባብሳሉ (ተናኝ ኦርጋኒክ ውህዶች)፤

 በተለይ ሕጻናትን የሚጎዳ ሲሆን የነርቭ እና የአእምሮ ሥርዓትን ያቃውሳል፡፡

በዓለም የጤና ድርጅት መረጃ መሰረት በዓለማችን በየዓመቱ 1.25 ሚሊዮን ሰዎች በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን ያጣሉ፤ ከ20 እስከ 50 ሚሊየን ያህሉ ደግሞ የአካል ጉዳት ይደርስባቸዋል፡፡ ከዚህ አደጋ ውስጥ እስከ 90 በመቶ የሚሆነው በማደግ ላይ በሚገኙ ሀገራት የሚከሰት ሲሆን በኢትዮጵያ በ100ሺ ተሽከርካሪዎች 5ሺ የሞት አደጋዎች በመድረስ በአደጋው ከፍተኛነት ከዓለም የአምስተኛ ደረጃን አስይዟታል፡፡ የአገልግሎት ዘመናቸው ከእስከ 12 ዓመት ከሆናቸው ተሽከርካሪዎች 25 በመቶ እና ከ13 ዓመት በላይ ባገለገሉ ተሽከርካሪዎች 50 በመቶ አደጋዎች የሚደርሱት በቴክኒክ ብልሽታቸው ነው፡፡

ሌላው፤ ከውጪ ሀገር በሚገቡ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች እና በአዳዲሶቹ መካከል የታሪፍ ልዩነት ባለመኖሩ የሀገር ውስጥ አምራቾችን ማበረታታት አልተቻለም፡፡ ስለዚህ፤ የሀገር ውስጥ አምራቾችን የገበያ ችግር ለመፍታትም የአዋጅ ማሻሻያው አስፈላጊ ነው፡፡

የሀገራችን ተሽከርካሪ መገጣጠሚያ ፋብሪካዎች በዓመት 11ሺ 600 ተሽከርካሪዎችን የመገጣጠም አቅም ቢኖራቸውም ከነርሱ በሦስት እጥፍ በበለጡና ከውጪ በሚገቡ ያገለገሉ ተሸከርካሪዎች ምክንያት በሙሉ አቅማቸው ማምረት እና ገበያውን መቆጣጠር አልቻሉም፡፡

ይህ ሁሉ ተጽዕኖ እያለ ሀገራችን ከ54ቱ የአፍሪካ ሀገራት ወደ ሀገራቸው በሚገቡ ያገለገሉ ተሸከርካሪዎች ላይ ገደብ ካልጣሉት 27 ሀገራት አንዷ ሆናለች፡፡

Report Page