#ETH

#ETH


በሞጣ ከተማ በሀይማኖት ተቋማት ላይ የደረሰውን ጥቃት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) በጽኑ ያወግዛል!

በምስራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ ትላንት አርብ ታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ/ም ከምሽቱ 1 ሰዓት አካባቢ በጥንታዊና ታሪካዊው ሞጣ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ላይ ለጊዜው ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ የእሳት ቃጠሎ የተነሳ ሲሆን፣ በቤተ ክርስቲያኑ ላይ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ በከተማው ነዋሪ ርብርብ እሳቱ በቁጥጥር ስር ውሏል። ይህንን ተከትሎ የተወሰኑ ወጣቶች በመስጊዶችና አንድ የንግድ ቤት ላይ የእሳት ቃጠሎ እንዲደርስ አድርገዋል። ሱቆችን የመዝረፍ ሙከራም ተካሂዷል። አብን በሞጣ ከተማ በሁለቱም የእምነት ተቋማትና በንብረት ላይ የተፈፀመውን ጥቃት በጥብቅ ያወግዛል። ድርጊቱም በምንም አይነት መንገድ ጠንካራ ትስስር ያለውን የሞጣና አካባቢው ህዝበ ክርስቲያንና ህዝበ ሙስሊም የሚገልጽ ሳይሆን ጥቂት በስሜት የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ድርጊት እንደሚሆን ይረዳል።

የአማራ ሕዝብ ለሺህ ዓመታት የተለያዩ ሀይማኖቶች ተከባብረው፣ ሙስሊሙ አብያተ ክርስቲያን፣ ክርስቲያኑ መስጊዶች ሲገነቡ አብሮ እየገነባ፣ በሰላም የሚኖሩበት ህዝብ ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአማራ "ክልል" በተለይ በእስልምና እምነት ተቋማት ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች መጨመራቸው አሳሳቢ ነው። የእምነት ተቋማት ላይ የሚደረግ ጥቃት የአማራን ሕዝብ እሴት የማይወክል፣ ፍፁም ህገወጥና በአስቸኳይ ሊታረም የሚገባ ተግባር ነው ብሎ ንቅናቄያችን ያምናል።

የክልሉ መንግስት በህዝባችን የእምነት፣ የትምህርትና የንግድ ተቋማት ላይ የሚደርሱ ተደጋጋሚ ጥቃቶችንም ሆነ የህዝባችን ሰላም ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ ሰርጎ ገቦችን መቆጣጠር አለመቻሉ በጣም አሳዛኝና አስቸኳይ መፍትሄ የሚያሻው ነው። መንግስት በዚህ ድርጊት የተሳተፉ አካላትን በአስቸኳይ ለህግ እንዲያቀርብ እየጠየቅን፣ የዕምነት ተቋማቱም የእነዚህን ጥቃቶች ቀስቃሾችና ተሳታፊዎችን በቀላሉ በመለየት ለህግ ማቅረብ እንዲቻል የተሻለ የደህንነት መጠበቂያ አሰራሮችን እንዲተገብሩ፣ በዘመናዊ የሲሲቲቪ ካሜራዎች ጭምር የታገዘ ጥበቃ እንዲኖራቸው አብን በዚህ አጋጣሚ ያሳስባል።

የሞጣና አካባቢው ወጣቶችም እንደትላንቱ አይነት ችግር ሲያጋጥም በስሜት ተነሳስቶ የራሳችንንና የወገኖቻችን ሀብትና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረስ በፍፁም ተቀባይነት የሌለውና አውዳሚ ተግባር መሆኑን መገንዘብ አለብን። የከተማው ወጣቶችና ህዝቡም በቃጠሎው የተጎዱ ተቋማትን አስቸኳይ ርብርብ በማድረግ መልሶ እንዲገነባቸው ጥሪ እያቀረብን፤ መላው ሕዝባችንም በዚህ ዙሪያ የተለመደ ርብርቡን እንዲያደርግ ጥሪ እናቀርባለን።

አንድ አማራ ለሁሉም አማራ፣ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!

Report Page