#ETH

#ETH



በዋስትና የተለቀቁት የአቶ አብዲ ኢሌ የክስ መዝገብ ተጠርጣሪ እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ተሰጠ!

ፌዴራል ፖሊስ በዋስትና የለቀቃቸውን የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሐመድ ኡመር /አብዲ ኢሌ/ የክስ መዝገብ ተጠርጣሪ የሆኑትን 37ኛ ተከሳሽ እንዲያቀርብ የፌዴሬሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጠ።

በእነ አቶ አብዲ መሐመድ ኡመር የክስ መዝገብ የተጠረጠሩ ሶስት ሰዎች ዛሬ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል።

ፖሊስ ከዚህ በፊት በዚሁ መዝገብ ከተካተቱ 47 ተከሳሾች መካከል ይዣቸዋለሁ ያላቸው 37ኛ ተከሳሽ የስም ስሕተት በመኖሩ በዋስትና እንዲለቀቁ መደረጉን አስረድቷል።

ነገር ግን በዋስትና የተለቀቁትና በወንጀል የተጠረጠሩት ተከሳሽ ስም አቶ አብዲ የሬ መሆናቸውን ጠቅሶ የስም ስሕተት በመፈጠሩ በድጋሚ እንዲጠሩና ማጣራት እንዲካሔድ አቃቤ ሕግ ጠይቋል።

ፍርድ ቤቱም ፖሊስ ተጠርጣሪውን ለታሕሳስ 20 ቀን 2012 ዓ.ም እንዲያቀርባቸው ትዕዛዝ ሰጥቷል።

በሌላ በኩል በዚሁ የክስ መዝገብ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት ወይዘሮ ዘምዘም ሀሰን /ሃኒ/ ማረሚያ ቤት ሆነው የወለዱት ሕፃን በመታመሙ የዋስትና መብት እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል።

ፍርድ ቤቱ የወይዘሮ ዘምዘም ልጅ የጤና ሁኔታ በምርመራ ተረጋግጦ በተከላካይ ጠበቃቸው በኩል በጽሑፍ እንዲቀርብ ትዕዛዝ የሰጠ ሲሆን ለዋስትና ጥያቄው ምላሽ ለመስጠት ለታሕሳስ 15 ቀን 2012 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል።

ሌላው ተጠርጣሪ አቶ ሃሰን ሃሺም ደግሞ የክስ መቃወሚያ ካላቸው በተከላካይ ጠበቃቸው በኩል እንዲያቀርቡ ለነሐሴ 20 ቀን 2012 ዓ.ም ቀጠሮ ተይዟል።

የቀድሞውን የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲ መሐመድ ዑመርን ጨምሮ 47 ተጠርጣሪዎች በክልሉ በተካሔደው የነፍስ ግድያ፣ የሃይማኖትና የንግድ ተቋማት ቃጠሎ፣ የዝርፊያና ሌሎች በርካታ የወንጀል ድርጊቶች ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወቃል።

(ENA)

Report Page