#ETH

#ETH


•በሚዲያ መገልገያ መሣሪያዎች ላይ የሚጣለው ኤክሳይዝ ታክስ በዘርፉ ላይ ጫና እንዳያደርስ ተጠየቀ

•ያገለገሉ አውቶሞቢሎች ላይ የሚጣለው ኤክሳይዝ ታክስ እስከ 500 ፐርሰንት ይደርሳል

በሥራ ላይ የሚገኘውን ኤክሳይዝ ታክስ እንዲተካ ለፓርላማ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ፣ የግብርና ዘርፉ መገልገያ የሆኑ ያገለገሉ ትራክተሮች ላይ እስከ 400 ፐርሰንት ኤክሳይዝ ታክስ የሚጥል አንቀጽ መያዙ ታወቀ፡፡

አዲሱ የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ባገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ፣ እንዲሁም በቢራና በትምባሆ ምርቶች ላይ የሚጥለውን የኤክሳይዝ ታክስ መጠን በቅርቡ ማስነበባችን የሚታወስ ሲሆን፣ ሙሉ ረቂቅ አዋጁ ማክሰኞ ታኅሳስ 7 ቀን 2012 ዓ.ም. ለፓርላማ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበት ለዝርዝር ዕይታ ለበጀትና ለፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡

ይህ ረቂቅ አዋጅ ካካተታቸው የታክስ ምጣኔዎች በእጅጉ የተጋነነ የተጣለው በተሽከርካሪ ምርቶች ላይ ሲሆን፣ የግብርና ዘርፉ መገልገያ የሆኑ ያገለገሉ ትራክተሮች ላይ እስከ 400 ፐርሰንት ኤክሳይዝ ታክስ የሚጥል ረቂቅ ድንጋጌን ይዟል፡፡ ያገለገሉና ዕድሜያቸው ከአራት ዓመት ያልበለጠ የእርሻ ትራክተሮች ላይ የ100 ፐርሰንት ኤክሳይዝ ታክስ እንዲጣል ይጠይቃል፡፡

ከአራት እስከ ሰባት ዓመት ባገለገሉት ላይ 200 ፐርሰንት፣ እንዲሁም ከሰባት ዓመት በላይ ባገለገሉት ላይ 400 ፐርሰንት ኤክሳይዝ ታክስ እንዲጣልባቸው በረቂቁ ድንጋጌ ተካቷል፡፡

ከላይ የተገለጸው የአገልግሎት ዕድሜን መሠረት ያደረገ የኤክሳይዝ ታክስ ምጣኔ በባለ አንድ አክስል ትራክተሮች ላይ፣ እንዲሁም ከ18 ኪሎ ዋት እስከ 130 ኪሎ ዋት ድረስ ጉልበት ባላቸው ትራክተሮች ላይም የሚጣል እንደሚሆን በረቂቁ ተመልክቷል፡፡

አንድ የፓርላማው አባል ያገለገሉ የግብርና መሣሪያዎችን እንኳን መጠቀም ባልጀመረው፣ አሁንም ሞፈርና የበሬ ጉልበትን ዋነኞቹ መገልገያዎቹ ባደረገው የእርሻ ዘርፍ ላይ ይህንን ያህል ኤክሳይዝ ታክስ ለመጣል የታቀደበትን ምክንያት ለመረዳት አለመቻላቸውን ገልጸው፣ ረቂቁን በዝርዝር የሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ በአጽንኦት ይህንን ጉዳይ እንዲመረምር አሳስበዋል፡፡

ባገለገሉ ትራክተሮች ላይ እንዲጣል የቀረበው ኤክሳይዝ ታክስ ምጣኔ አመክንዮን የተመለከተ ለብቻው የቀረበ ማብራሪያ ባይኖርም፣ የግብርና ሚኒስቴር በሺዎች የሚቆጠሩ የእርሻ ትራክተሮችን ከቀረጥ ነፃ ለማስገባት ሒደት ላይ እንደሆነና የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) አምርቶ ገበያ ያላገኘላቸው ከሰባት ሺሕ በላይ ትራክተሮች በመጋዘን እንደሚገኙ የሰነድ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በሥራ ላይ በሚገኘው የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ቁጥር 307 እና በዚህ አዋጅ ማሻሻያ የእርሻ ትራክተሮች ላይ ምንም ዓይነት ኤክሳይዝ ታክስ አልተጣለም፡፡

ሌላ የምክር ቤቱ አባል በበኩላቸው ረቂቅ አዋጁ ገና ደካማ አቅም ባለው የሚዲያ ዘርፍ መገልገያ መሣሪያዎች ላይ ለመጣል ያቀደው ታክስ በዘርፉ ዕድገት ላይ ጫና እንዳያሳድር ሥጋት እንዳላቸው ገልጸው፣ ረቂቁን በዝርዝር የሚያየው ቋሚ ኮሚቴ ይህንንም ጉዳይ ትኩረት እንዲያደርግበት ጠይቀዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ የቪዲዮ መቅረጫና ማስተላለፊያ መሣሪያዎች፣ እንዲሁም የቴሌቪዥንና የሬድዮ ድምፅ ሥርጭት መቀበያ መሣሪያዎች ላይ አሥር በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ እንዲጣል ድንጋጌ ይዟል፡፡ በሥራ ላይ የሚገኘው የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ቁጥር 307 የቴሌቪዥንና የቪዲዮ ካሜራዎች ላይ የሚጥለው ኤክሳይዝ ታክስ 40 በመቶ ነው፡፡

በቅርቡ በተሽከርካሪዎች ላይ እንደሚጣል ከተገለጹ የኤክሳይዝ ታክስ ምጣኔ ባለፈ፣ ባገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ ለመጣል የታቀደው የታክስ መጠን እስከ 500 ፐርሰንት እንደሚደርስ ከረቂቅ አዋጁ ዝርዝሮች ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡

ለአብነት ያህል ከ1,300 ሲሲ በላይ ጉልበት መጠን ኖሯቸው ከሰባት ዓመት በላይ ያገለገሉት ላይ 460 ፐርሰንት፣ እንዲሁም ከ1,800 ሲሲ በላይ ጉልበት ኖሯቸው ከሰባት ዓመት በላይ ባገለገሉት ላይ 500 ፐርሰንት ኤክሳይዝ ታክስ እንዲጣል በረቂቁ ድንጋጌዎች ተካተው ቀርበዋል፡፡


Report Page