ETH

ETH

ቲክቫህ ኢትዮጲያ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሰላማዊ የመማር ማስተማር እንቅስቀሴ በተሞክሮነት ሊወሰድና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው እንደሆነ ተገለጸ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብትና ቴክኖሎጅ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰሞኑን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ባደረገው ምልከታ በዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር እንቅስቀሴ በተሞክሮነት ሊወሰድና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው እንደሆነ ገልጿል፡፡

የዩኒቨሲቲው ፕሬዘዳንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የተቋሙን የስራ እንቅስቃሴ አስመልክተው ለቋሚ ኮሚቴው ገለጻ ባደረጉበት ወቅት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራውን ማስፈን ትኩረት የተሰጠው ተግባር እንደሆነ አስታውሰው ይህንንም ማሳካት የቻልነው ከአካባቢው ማህበረሰብ፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከጸጥታ አካላትና ከተማሪዎች አደረጃጀቶች ጋር ተቀራርበን በመስራታችን ነው ብለዋል፡፡

ለተማሪዎች የሚሰጡ አገልግሎቶችን ከማሟላት አኳያ ዩኒቨርሲቲው ተገቢውን ጥረት እያደረገ መሆኑን የገለጹት ፕሬዘዳንቱ ነገር ግን ለአንድ ተማሪ ቀለብ ተብሎ በቀን የተመደበው 15 ብር የወቅቱን የገበያ ሁኔታ ግምት ውስጥ ያላስገባና ፍትሃዊ ያልሆነ በሆመኑ የሚመለከተው አካል ትኩረት ሰጥቶ ሊፈታው ይገባል በማለት ተናግረዋል፡፡

ውጤታማ ጥናትና ምርምር ከማካሄድና የማህበረሰቡን ህይወት ከማሻሻል አኳያ በእንስሳት በሽታ፣ በደጋ ፍራፍሬና በአሳ እርባታ እንዲሁም ቴክኖሎጅዎችን በማሸጋገር ረገድ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ዳምጠው በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና በቴክኒክና ሙያ ማስልጠኛ ኮሌጆች ላይም ሙያዊ ድጋፍ እየተደረገ እንደሆነም አመላክተዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ በማጠቃላያ አስተያየቱ እንዳለው የዩኒቨርሲቲው አመራር የመማር ማስተማር ስራው ሰላማዊ ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ ከአካባቢው ማህበረሰብ፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከጸጥታ አካላትና ከተማሪዎች አደረጃጀቶች ጋር ተቀራርቦ መስራቱ በጥንካሬ የሚወሰድ ተግባር መሆኑን አንስቶ የተማሪዎች አገልግሎትን በማሟላት ትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ለማድረግ እተከናወነ ያለው ተግባር በተሞክሮነት የሚወሰድና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው እንደሆነም አስገንዝቧል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ላብራቶሪና የወርክ ሾፖች አደረጃጀቶች ዘበናዊና ለአገር እድገት ተስፋ የሚጣልባቸው መሆኑን የገለጸው ቋሚ ኮሚቴው መንግስት የዚህን ተቋም እምቅ አቅም አሟጦ ሊጠቀምበት ይገባል በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

የዩኒቨርሲቲ-ኢንዱስትሪ ትስስሩ የተጠናከረ መሆኑ ተማሪዎች በንድፈ-ሃሳብ ያገኙትን እውቀት በተግባር እንዲያጠናክሩት ከማስቻሉም ባሻገር እንዱስትሪዎችም የሰለጠነ ባለሙያ ፍላጎታቸውን ማሟላት እንዲችሉ እና ተወዳዳሪነታቸውን እንዲያሳድጉ ስለሚያግዝ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበትና በመተሞክሮንት ሊወሰድ የሚገባው ተግባር እንደሆነም አስገንዝቧል፡፡

መረጃው የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ነው

Report Page