#ETH

#ETH


የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ መሰረታዊ የሰራተኞች ማኅበር ”አባላቱን ለማደራጀትና ለመንቀሳቀስ በአሰሪው ድርጅት ጫና እየተደረገብኝ ነው” በሚል ቅሬታ አሰማ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በበኩሉ ”ቅሬታው የተሳሳተና ከእውነት የራቀ ነው” ብሏል።

ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት የተመሰረተው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኞች ማኅበር በ2009 ዓ.ም. አየር መንገዱ ከኢትዮጰያ ኤርፖርቶች ድርጅት ጋር ሲዋሃድ የማኅበሩ አደረጃጀት አከራካሪ ሆኖ ቆይቷል።

በተመሳሳይ ዓመት ሁለቱ ድርጅቶች ‘የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ’ በሚል ሲዋሃዱ የሁለቱን ድርጅቶች የቀድሞ ሰራተኛ ማኅበራት በማጣመር አዲስ ማኅበር ለማቋቋም እንቅስቃሴ ተጀምሮ፣ የአመራር ምርጫ ተደርጎ እንደነበር አባላቱ ያስረዳሉ።

ነገር ግን አየር መንገዱ ”ምርጫው ህጋዊና ትክክል አይደለም” በሚል ጣልቃ መግባቱን ፣ ከዚህም ባለፈ ”ዋና አብራሪዎች በሰራተኛ ማኅበር አባል መሆን አይችሉም” በሚል ከልክሎ እንደነበርም ያወሳሉ።

አየር መንገዱ አዲስ ማህበር ለመመስረት ጫና ቢያደርግም ከረጅም ክርክር በኋላ ግን የሚመለከታቸው ተቋማት ተወካዮች በተገኙበት አብራሪዎች አባል መሆን እንደሚችሉ ስምምነት መደረሱን ይገልጻሉ።

በዚህ ሂደት መስከረም 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ነባሩ የሰራተኛ ማኅበር ከማኔጅመንቱ ነጻ እንዳልሆነ በመግለጽ ‘የኢትዮጵያ አየር መንገድ መሰረታዊ የሰራተኞች ማኅበር’ በሚል ስያሜ በአዲስ ተመስርቶ መስከረም 30 ቀን 2012 ዓ.ም ከሰራተኛ ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የዕውቅና የምስክር ወረቀት ተሰጥቶታል።

የማኅበሩ ሊቀ መንበር ካፒቴን የሺዋስ ፋንታሁን ለኢዜአ በሰጡት ማብራሪያ የሁለቱን ድርጅቶች የቀድሞ ሰራተኛ ማኅበራትን በማቀፍ እየተንቀሳቀሰ እያለ፤ ከ60 የማይበልጡ የቀድሞው የአየር መንገድ ሰራተኞች ማኅበር አባላት ‘አመራር ቀየርን’ በሚል ለሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ማመልከታቸውን ይጠቅሳሉ።

በዚህም ‘የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቀዳማዊ መሰረታዊ የሰራተኛ ማኅበር’ በሚል ስያሜ መመስረቱን ገልጸው፤ አየር መንገዱም ከዚህ ማኅበር ጋር እንደሚሰራና ሌላ ማኅበር እንዳይንቀሳቀስ ዘርፈ ብዙ ተጽዕኖ እያደረገበት መሆኑን ተናግረዋል።

በአዲስ የተመሰረተው ማኅበር ከሚደርስበት ተጽዕኖዎች መካከል ማኅበሩ እንዳይንቀሳቀስ፣ በአየር መንገድ ተሽከርካሪዎች ውስጥም ሆነ አየር መንገዱ በተከራያቸው የውጭ አገር ሆቴሎች ምዝገባ ማካሄድ፣ በድርጅቱ ቅጥር ግቢ ስብሰባ ማድረግ መከልከሉን አውስተዋል።

ማኅበሩ ”አባላቱ ከደመወዛቸው ለማስቆረጥ የአባላቱ የፈረሙበትን ዝርዝር ለአየር መንገዱ ቢያስገባም፣ አባል መሆናቸውን እየመጡ ይፈርሙ በሚል ለማሸማቀቅ መሞከር፣ ደብዳቤ አልቀበልም የማለትና ሌሎች ጫናዎች እያደረገብኝ ነው” ሲል ማኅበሩ ቅሬታዎች ገልጿል።

በማኅበሩ አባላትና አመራሮች ላይ ማስፈራሪያ፣ መሸማቀቅ፣ መቅጣትና ከስራ ማገድ እየተፈጸመበት መሆኑም ተናግረዋል።

ማኅበሩ ከቅድመ ምስረታ ጀምሮ ጫና ቢደረግበትም ሰራተኛው ከማኔጅመንቱ ተጽዕኖ ነጻ የሆነ፣ መብትና ጥቅም የሚያስከብር ማኅበር ተመስርቷል በሚል ከፍተኛው የሰራተኛ ቁጥር በአባልነት መመዝገቡን ይጠቅሳሉ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ 17 ሺህ ሰራተኛች እንዳሉት የሚገልጹት ካፒቴን የሺዋስ፤ ከዚህ ውስጥ ሰራተኛ ማኅበሩ ሲሶ የሚሆነውን ሰራተኛ አባል ማድረጉንና በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ መሰረትም የህብረት ድርድር የማድረግ መብት እንዳለው ይናገራሉ።

ከነባሩን ማኅበር ቢያንስ በአንድ ሺህ የሚበልጥ አባል ያለውን ማህበር አየር መንገዱ ‘የእንጀራ ልጅ’ አድርጎ በማየት ጫና እያደረሰበት መሆኑን ገልጸዋል።

ድርጅቱ በሰራተኛ ማኅበሩ ላይ የሚያደርገው ጫና ለኢንዱስትሪው ሰላም የማይፈጥርና ሰራተኛውን ወደ ጽንፍ የሚወሰድ በመሆኑ አየር መንገዱ በማኅበሩ ላይ የሚያደርገውን ተጽዕኖ እንዲያቆም ጠይቋል።

ኢዜአ የሰራተኛ ማኅበሩን ቅሬታ ይዞ አየር መንገዱ ግሩፕን የጠየቀ ሲሆን አየር መንገዱ በጉዳዩ ላይ የጽሁፍ ማብራሪያ ብቻ እንደሚሰጥ ገልጾ፣ በአየር መንገዱ የህዝብ ግንኙነትና ኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን በኩል ማብራሪያውን ልኮልናል።

በማብራሪያው መሰረትም አየር መንገዱ በቅርቡ የተመሰረተ መሰረታዊ የሰራተኞች ማኅበር መኖሩን ገልጾ፣ “ማኅበሩ የሚሰጣቸው መግለጫዎች በጣም የተሳሳቱና ሙሉ በሙሉ ከእውነት የራቁ ናቸው” ብሏል።

ድርጅቱ በ1955 ዓ.ም የተመሰረተና ህልወናውን ጠብቆ የቆየ ነባር የአየር መንገድ ሰራተኛ ማኅበር እንዳለ በመጥቀስ፣ ማኅበሩ ከ50 በመቶ በላይ ሰራተኛውን አቅፎ የያዘ፣ ከድርጅቱ ጋር በሰራተኛ ጉዳይ ላይ በመግባባት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።

በአዲስ የተመሰረተው የሰራተኛ ማኅበርም የመደራጀት መብቱ ተጠብቆ ካለምንም ተጽዕኖ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን በመግለጽ፣ የማኅበሩን ቅሬታ አስተባብሏል።

”ጥቂት የማኅበሩ አመራሮች ግን በህግ ከሚፈቀድላቸው ተግባራትና አካሄዶች ውጭ እየተንቀሳቀሱ ቢሆንም ድርጅቱ ለኢንዱስትሪው ሰላም ሲል በትዕግስት እየተከታታልኩ ነው” ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

አየር መንገዱ ነባር የሰራተኛ ማኅበር እንዳለ ቢጠቅስም፣ አየር መንገዱ ከኤርፖርቶች ድርጅት ጋር ከተዋሃደ በኋላ የሰራተኛ ማኅበሩ አደረጃጀቱ በምን መልኩ እንደቀጠለ አልገለጸም።

ኢዜአ አየር መንገዱ ከሰራተኛ ማኅበሩ ጋር የተለዋወጣቸውን ደብዳቤዎች ላይ እንደታዘበው በማኅበሩና በአየር መንገድ ግሩፑ መካከል አለመግባባት የቆዬ እንደሆነ ያስረዳል።

ከኢትዮጵያ ሰራተኞች ኮንፌደሬሽን የተጻፉ ደብዳቤዎችም ይህን የሚያጠናክሩ ናቸው።

ለአብነትም ማኅበሩ በአዲስ ለመመስረት በመገናኛ ብዙሃን ጥሪ ማድረጉን ተከትሎ አየር መንገዱ ለሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ፤ አየር መንገዱ ነባር የሰራተኛ ማኅበር እንዳለውና ከዚህ ውጭ የሚደረግ እንቅስቃሴ የማይቀበለውና ህገ ወጥ መሆኑን ገልጿል።

ማኅበሩ ከተመሰረተ በኋላም በግቢው ስብሰባ ለማድረግ በጠየቀው የፈቃድ ማመልከቻ አየር መንገዱ ህዳር 8 ቀን 2012 ዓ.ም በሰጠው ምላሽ ማኅበሩ የሚወያይበትን ጉዳይ ማሳወቅ እንዳለበት፣ ከስብሰባው በፊትም የማኅበሩ እንቅስቃሴ ከአሰሪና ሰራተኛ መርህ የወጣ፣ የድርጅቱንም ስም የሚያጠለሽ በመሆኑ በሚዲያ በአስቸኳይ ይቅርታ እንዲጠይቅ ያስገድዳል።

ጥቅምት 17 እና 20 ቀን 2012 ዓ.ም በአየር መንገዱ በተሰጠ ማሳሰቢያ ጥቂት ሰራተኞች በድርጅቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የድርጅቱን ንብረት በመጠቀም በግንኙነት አማራጮች የድርጅቱን አመራሮችና ሰራተኞች ስም የሚያጎድፉ መልክቶች እያስተላለፉ እንደሆነ፣ ሰራተኞችን አባል እንዲሆኑ እያስገደደ መሆኑን፣ ድርጅቱም እርምጃ መውሰድ መጀመሩን በመጥቀስ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ያስጠነቅቃል።

የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማኅበራት ኮንፌደሬሽን በሃምሌና ነሃሴ ወራት 2011 ዓ.ም ለሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በጻፋቸው ደብዳቤዎች አየር መንገዱ ከኤርፖርቶች ድርጅት ጋር ከተዋሀደ በኋላ የሰራተኛ ማህበራቱ አዲስ ማህበር ለመመስረት ጥረት እያደረጉ መሆኑን ገልጾ፣ ዳሩ ግን አየር መንገድ ግሩፕ ጣልቃ እየገባ መሆኑን፣ የመስራች አመራሮችን ስም በመጥቀስ ወከባ እየፈጸመባቸው እንደሆነ ቅሬታውን አሳውቋል።

(ENA)

Report Page