#ETH

#ETH


- ያላግባብ ከሥራ ታግደናል የሚሉ የአየር መንገዱ ሠራተኞች ቅሬታቸውን ገለጹ። 

- አየር መንገዱ በዲሲፕሊን ግድፈት ምክንያት አስተዳደራዊ ዕርምጃ ተወስዷል ብሏል። 

ያላግባብ ከሥራ ገበታችን ታግደናልና ተባረናል ያሉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኞች በተወካያቸው በኩል ቅሬታቸውን ገለጹ፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ዕግድ የወጣባቸው አሥር የአየር መንገዱ ሠራተኞች፣ የታገዱበትንና የተባረሩባቸውን ደብዳቤዎች አያይዘው ለሪፖርተር ልከዋል፡፡

መደበኛ ያልሆነ የመገናኛ መድረክ ተጠቅመው የተቋሙን ማኔጅመንት ስም የሚያጎድፍ መልዕክት ለሠራተኞች በማስተላለፋቸው፣ ይህም ተቋሙ የሚተዳደርበትን የሥነ ምግባር መርህ የሚጥስ በመሆኑ ጉዳያቸው እስኪጣራ ድረስ ከሥራ መታገዳቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ መስከረም 24 ቀን 2012 ዓ.ም. የደረሳቸው ካፒቴን አዲሱ ወልደ ሚካኤል ናቸው፡፡ ድርጊቱ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2019 መሠረት የሥራ ውል እስከማቋረጥ የሚደርስ ቅጣት የሚያሰጥ ቢሆንም፣ ውሉ ሳይቋረጥ ምርመራ እንዲደረግበት መወሰኑን በደብዳቤው ተገልጿል፡፡

አቶ ወንድማገኝ ፍቅሩ የተባሉ ሌላው የአየር መንገዱ ሠራተኛ መንጃ ፈቃድ ሳይዙ፣ የተቋሙን መኪና በኤርፖርቱ ቅጥር ውስጥ አሽከርክረዋል ተብለው የሥራ ውላቸው መቋረጡን የሚገልጽ ደብዳቤ የተጻፈላቸው ሰኔ 24 ቀን 2011 ዓ.ም. ነው፡፡ ደብዳቤው ድርጊታቸው በአየር መንገዱ ደንብና በሠራተኛ ሕጉ መሠረት ያለ ምንም ማስጠንቀቂያ የሥራ ውላቸው መቋረጡን ያትታል፡፡ ደብዳቤው የተጻፈላቸው ሰኔ 24 ቀን ሲሆን፣ ውሳኔው የፀናውም ከሰኔ 27 ቀን በኋላ እንደሆነ ሰነዱ ያስረዳል፡፡

አየር መንገዱ ያላግባብ ከሥራ አግዷቸዋል የተባሉት ሦስተኛው ግለሰብ ካፒቴን ያየህይራድ አበራ ሲሆኑ፣ የተቋሙን ማኔጅመንት ቡድን ስም የሚያጎድፍ መልዕክት ለሠራተኞች አስተላልፈዋል ተብለው ከሥራ መታገዳቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ የደረሳቸው መስከረም 26 ቀን 2012 ዓ.ም. ነው፡፡

የአየር መንገዱን ማኔጅመንት አካል በጽሑፍ ሰድበዋል ተብለው የሥራ ዕግድ የወጣባቸው አቶ ኃይለ ሚካኤል ደመና የተባሉ የተቋሙ ሠራተኛ፣ ያላግባብ ከሥራ ታግደዋል ከተባሉት ውስጥ ናቸው፡፡ ድርጊታቸው ተጨማሪ ምርመራ የሚያስፈልገው በመሆኑ ጊዜያዊ ዕግድ እንደተጣለባቸው የሚገልጸው ደብዳቤ የተጻፈው ኅዳር 5 ቀን 2012 ዓ.ም. ሲሆን፣ የፀናውም ከኅዳር 8 ቀን ጀምሮ ነው፡፡

የሠራተኞቹን ቅሬታ ለሪፖርተር ያደረሱት ካፒቴን የሺዋስ ፋንታሁን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ መሠረታዊ የሠራተኛ ማኅበር ሊቀመንበር ናቸው፡፡ በአየር መንገዱ ሠራተኞች ላይ እየደረሰ ያለው በደል ከማኅበሩ ጋር ያላቸውን ግንኙነት መሠረት ያደረገ መሆኑን ሊቀመንበሩ ይናገራሉ፡፡

ሪፖርተር ካፒቴን የሺዋስን ካነጋገረበት ዕለት አንድ ቀን ቀደም ብሎ የማኅበሩን ፎርም ይዛ የተገኘች የአየር መንገዱ ሠራተኛ ወዲያው ሥራ አቁማ እንድትወጣና መባረሯን የሚገልጽ ደብዳቤ፣ ሰኞ ኅዳር 6 ቀን 2012 ዓ.ም. እንድትወስድ እንደተነገራት ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ከተቀላቀሉ በኋላ የተመሠረተው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ መሠረታዊ የሠራተኞች ማኅበር፣ ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ዕውቅና ተሰጥቶት ሥራ የጀመረው በዚህ ዓመት ጥቅምት ወር ላይ እንደሆነ ሊቀመንበሩ ገልጸዋል፡፡

አየር መንገዱ ግን የማኅበሩን መቋቋም እንደማይፈልግ የገለጹት ካፒቴን የሺዋስ፣ በመቋቋም ሒደት ላይ ሳለ ጠንካራ ተሳትፎ የነበራቸውን ሰዎች ከሥራ ማገዱንና ማባረሩን፣ ማኅበሩ ከተመሠረተም በኋላ አባል ሆነው ንቁ እንቅስቃሴ በሚያደርጉ ሠራተኞች ላይ በየምክንያቱ ዕርምጃ እየወሰደ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የማኅበሩ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ማርቆስ የሱወርቅም ሰኔ 26 ቀን 2011 ዓ.ም. በተጻፈ የጊዜያዊ ዕግድ ደብዳቤ ለሁለት ወራት ከሥራ መታገዳቸውን፣ ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ ሲደረግም የሁለት ወራት ደመወዝ መቀጣታቸውን ገልጸዋል፡፡ የዕግድ ደብዳቤ የወጣባቸውም የአየር መንገዱን ኢሜይል በመጠቀም በሥራ ኃላፊዎች ላይ ሥጋት የሚፈጥርና ዝቅ የሚያደርጋቸው ስም የማጥፋት ድርጊት ፈጽመዋል በሚል ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የማኅበሩ ሊቀመንበር ካፒቴን የሽዋስም እንዲሁ ተመሳሳይ ዕጣ እንደ ደረሳቸው፣ እንደ ሌሎቹ ከሥራ መታገዳቸውን ወይም መባረራቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ባይደርሳቸውም፣ ከሥራ ገበታ ከተለዩ ሁለት ወራት ከ15 ቀናት ማለፋቸውንና ደመወዛቸውም መቆሙን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ጉዳዩን በንቃት ሲከታተል የነበረው የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ለሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በሐምሌ 2011 ዓ.ም. ደብዳቤ ልኮ ነበር፡፡

‹‹የማኅበሩ አባላት ለምክር ቤት አባልነት የተመረጡና ንቁ ተሳታፊዎች መሆናቸውን ተከትሎ ለማሸማቀቅ ሲባል፣ ከድርጅቱ ለማሰናበትም ሆነ ጊዜያዊ ዕግድ ለመስጠት ሥልጣኑ በሌላቸው የሥራ ኃላፊዎች ዕርምጃ እየተወሰደ ነው፡፡ በማኅበራት ጉዳይ ጣልቃ መግባትና በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ (1) ፊደል (ሀ እናመ)፣ እንዲሁም በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 26(2) ፊደል (ሀ፣ ለ፣ ሐ እናመ) የተጠቀሱትን በመተላለፍና ኢትዮጵያ ተቀብላ ካፀደቀቻቸው ኮንቬንሽን ቁጥር 87 እና 98 ጋር በቀጥታ የሚቃረን በመሆኑ በሠራተኞቹ ላይ የሚደርሰውን ወከባ፣ ዕግድና ስንብት መታረምና መቆም አለበት፤›› ብሏል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ ጥያቄ የቀረበለት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በጽሑፍ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ‹‹እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ጠንካራ የሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የዳበረ የሰው ሀብት ልማት ደንቦችና መመርያዎች ያሉት ድርጅት ሲሆን፣ የተጠቀሱት ሠራተኞች በተለያየ የዲሲፕሊን ጥፋት ምክንያት አስተዳደራዊ ዕርምጃ የተወሰደባቸው ናቸው፡፡ ዕርምጃውም ከመወሰዱ በፊት በድርጅቱ አሠራር መሠረት ጉዳያቸው በዲስፕሊን ኮሚቴ ታይቶ ተመጣጣኝ አስተዳደራዊ ዕርምጃ መሆኑ ተረጋግጦ እንደተከናወነ ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡ በተጨማሪም አስተዳደራዊ የዕርምት ዕርምጃዎቹ በምንም መልኩ ከአባልነታቸው ጋር እንደማይያያዝ ለማሳየት፣ ዕርምጃው ሲወሰድ ከተጻፈላቸው ደብዳቤ መገንዘብ ያስችላችኋል ብለን እንገምታለን፡፡ በተጨማሪም ሠራተኞቹ የታገዱበትን ቀንና የሠራተኛ ማኅበሩ ምርጫ የተደረገበት ወይም ሕጋዊ ሆኖ የተመዘገበበትን ጊዜ ማመሳከርም የክሱን መሠረተ ቢስነት ሊያስረዳ ይችላል ብለን እናምናለን፤›› ሲል አስረድቷል፡፡

‹‹አየር መንገዳችን የአገራችን የአሠሪና ሠራተኛ አዋጁን በአግባቡ ተከትሎ ከመሥራቱም በላይ፣ የማንኛውንም የሠራተኛ ማኅበር ጉዳዮች በዚሁ አግባብ እያስተናገደ የሚገኝ ሲሆን፣ በማንኛውም የሠራተኛ ማኅበር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባ ማረጋገጥ እንወዳለን፡፡ በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት በድርጅቱ ውስጥ ሁለት ማኅበራት የሚገኙ ሲሆን፣ የአሠሪና ሠራተኛ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ከ50 በመቶ በላይ አባል ካለውና ከ57 ዓመት ዕድሜ ካስቆጠረው ቀዳማዊ የሠራተኛ ማኅበር ጋር በሠራተኞች ጉዳይ ላይ በቅርበትና በጋራ በመሥራት ላይ እንደምንገኝ መግለጽ እንወዳለን፡፡ በዚህ አጋጣሚ ችግር አለኝ የሚል ግለሰብም ሆነ ማኅበር በድርጅቱ የውስጥ አሠራር መሠረት ተወያይቶ መፍታት እንደሚቻል እየታወቀ፣ ወደ ሚዲያ መሄድ አስፈላጊ አልነበረም፤›› ብሏል፡፡ 

(Reporter Newspaper)


Report Page